“እብደትን ከሚያባብሱ የአዲስ አበባ ስፍራዎች ውስጥ መገናኛ በቁጥር አንድ መቀመጥ ያለበት ነው። በተለይ ደግሞ በስራ መውጫና መግቢያ ሰአት እዛ መገኘት! 11ኛው ሰዓት ላይ መገናኛ ከተገኘህ የመረቀንክ እስኪመስልህ ድረስ አንተ ዝም ብለህ የኢትዮጲያ ህዝብ ግን ያወራል”
አንድ ፀሐፊ ጓደኛየ ከከተባትና ከአመታት በፊት ያነበብኳ አንቀፅ ከአእምሮየ አትጠፋም። የማውቀውን የከተማዋን የድምፅ ብክለት ፍንትው አድርጎ በፅሑፉ አስመልክቶኛል።
የድምፅ ብክለት ከአየር ብክለት ቀጥሎ ሁለተኛው የጤና ጠንቅ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት WHO ይገልፃል። ለከፍተኛ ድምፅ መጋለጥ የአካልና ስነ-ልቦና ጤንነትን ያውካል። በተለይም ከመኪኖች የሚወጣው ጫጫታ በአለም ጤና ድርጅት ለሰው ልጆች እጅግ አስከፊ ከሆኑ የአካባቢ ችግሮች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከፍ ያለ ድምፅ ባለበት የሥራ ቦታ ወይም አካባቢ መሆን ለጆሮ መስማት አቅም መድከም፣ ለደም ግፊት፣ ለልብ በሽታ፣ የባህርይ ብስጩነትና የእንቅልፍ መዛባትን ያስከትላል። የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት መዛባትና ጤናማ ያልሆነ ውልደትም ለድምፅ ብክለት ከመጋለጥ ጋር ይያያዛሉ። ለከፍተኛ ድምፅ መጋለጥ ከስኳር መጠን መጨመርና ለከፋ የልብና የደም ዝውውር ችግሮች ይዳርጋል። የሚፈጥረው ጭንቀት በሥራ ቦታ የሚከሰቱ አደጋዎችን መጠን በከፋ መጠን እንዲጨምሩ ማድረጉን ጥናቶች አመላክተዋል። በአውሮፓ ብቻ በድምጽ ሳቢያ በሚከሰቱ ችግሮች በዓመት ወደ 10,000 ሰዎች ይሞታሉ፡፡
የድምፅ ብክለት በአዲስ አበባ
የከተሜነት መስፋፋት እንደ ማኑፋክቸሪንግ፣ ትራንስፖርትና ኮንስትራክሽን ካሉ ዘርፎች ማደግ ጋር ተዳምሮ ሙያዊ ክህሎት የሌላቸው የገጠሩ ክፍል ሰዎች ወደ ከተሞች ገብተው የሥራ ዕድሎች እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በከተሞች የሚፈጠር የገቢ ማደግ አዲስ የአኗኗር ዘይቤን ይፈጥራል። መንግሥትም ጥሩ ገቢ እንዲሰበስብና ወጭውን ለልማት የሚመድበውን በጀት ከፍ ያደርጋል። ለኢኮኖሚው ማደግ የሚኖረው አስተዋፅኦም የተሻለ የኑሮ ሁኔታን ለማምጣት አጋዥ ይሆናል።
እነዚህ የከተሜነት መስፋፋት አወንታዊ ገፆች ቢሆኑም ይዘውት የሚመጡት ጣጣም አለ። በአዲስአበባ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የተጀመረው በ 1930 ዎቹ የጣሊያን ፋሺስቶች አጭር የወረራ ወቅት ሲሆን አብዛኛዎቹ አሁንም እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው፡፡ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ጊዜ ያለፈባቸው በመሆናቸው የሚረብሽ ድምፅ የሚለቁ ናቸው። የከተማዋ አብዛኞቹ የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ከ 20 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ናቸው። ቁጥር አንድ የአየርና የድምፅ ብክለት ምክንያቶችም ናቸው ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ የድምፅ ብክለት በብዙዎች ዘንድ እንደ ጤና ጠንቅ ባይቆጠርም በዜጎች ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የመንገድ እና የአየር ትራንስፖርት ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሙዚቃ ቤቶች፣ ውሾች፣ የምሽት ክለቦች ፣ የድምፅ ማስታወቂያዎች ና የሃይማኖት ተቋማት እንደ ዋና የድምፅ ብክለት ምንጭ ተደርገው ይመደባሉ።
የመዲናዋ ጫጫታ ያላማረረው የለም። ነግቶ በጧት ወደ ስራው የሚገባው በቂ እንቅልፍ ሳያገኝ ያሳልፋል። ህመምተኞች በአሰቃቂ ሁኔታ ያድራሉ፡፡ ተማሪዎች በትምህርታቸው በትክክል መሳተፍ አይችሉም ፡፡ አረጋውያኑም የሌሊት ሰዓታቸው በጭንቀት የተሞላ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2014 International Journal of Environmental Science ላይ የወጣው የመኮንን እና ለታ ጥናት እንዳመለከተው በመርካቶ ገበያ በተመረጡ 20 ቦታዎች ከፍተኛው ልኬት የሆነው 102.6 ዴሲቤል ሲሆን ከ 20ዎቹ ውስጥ 19ኙ ለንግድ ቦታዎች ከተቀመጠው 65 ዴሲቤል ገደብ አልፈው ተገኝተዋል። ይህም ጉልህ የጤና ችግር ያስከትላል ሲልም የጥናቱ ትንተና አስቀምጧል።
ሕጉ ምን ይላል? ተግባሩስ?
በኢትዮጵያ ምንም እንኳን እ.ኤ.አ. ከ 1957 ጀምሮ በህገ-መንግስቱ ጉዳዩን የሚመለከቱ አዋጆች ቢኖሩም ለምን ተግባራዊ አይሆንም? የሚለው ጥያቄ ግን እስካሁን አልተመለሰም፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 44 እያንዳንዱ ሰው በንፁህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት ይሰጣል። አንቀፅ 92 መንግስት “ጥረት እንደሚያደርግ” ይደነግጋል፡፡
የኢትዮጵያ ህገ-መንግስትና የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አዋጅ ዜጎች ከማንኛውም የድምፅ ብክለት የመጠበቅ መብት እንዳላቸው በግልፅ ያሳወቀ ሲሆን ከአዋጁ የተገኙ አንዳንድ ህጎችም ከአማካይ ዴሲቤል በላይ ድምፅን የሚያሰማ አካል በህግ ተጠያቂ ነው ይላል። ህጉ የመኖሪያ፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ቦታዎች ቀን ላይ የድምፅ መጠናቸው በቅደም ተከተል 55፣ 65 እና 75 ዴሲቤል እንዲሆን ይደነግጋል። በሌሊት ደግሞ 45፣ 57 እና 75 ዴሲቤል ነው፡፡ ደንቦች መዘጋጀታቸው ጥሩ ነገር ቢሆንም አተገባበርና አፈፃፀም ነው ችግሩን መቅረፍ የሚችለው።
ይሁንና እውነታው በተቃራኒ ነው፡፡ ለምሳሌ ከማስታወቂያ አዋጁ 759/12 በተቃራኒ “በማንኛውም የድምፅ ማጉያ ማሽን አማካኝነት የድምፅ ብክለትን የሚያስከትሉ ማስታወቂያዎች ፣ አግባብ ባለው የመንግስት አካል የተቀመጠውን የድምፅ ገደብ የማያከብር” የሚለውን በመጣስ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የነበረው እንዳለ ነው የቀጠለው። የመንግሥትም ሆነ የግል (በመንግሥት የተያዙት እንደ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርና ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን መጥቀስ ይቻላል) ጆሮ በሚሰነጥቅ የማስታወቂያ ጫጫታ የሚታወቁ ናቸው።
በተለያዩ አካባቢዎች እንደ የአካባቢ ተጽዕኖ አዋጅ (ቁጥር 229/2002) እና የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ (ቁጥር 300/2002) አልፎ አልፎ እዚህም እዚያም ተጠቅሷል ፡፡ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የተጣጣመ የድምፅ ደረጃ ደንግጓል፡፡ ምንም እንኳን መመዘኛዎቹ የአገሪቱን የድምፅ ብክለት በማጥናት ላይ ያልተመሰረቱ ቢሆኑም ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪና ለመኖሪያ አካባቢዎች ለቀንና ሌሊት ተብለው የተለዩ ዲሲቤሎች ተቀምጠዋል፡፡
በወርሃ ጥር 2011 ዓ.ም የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የድምጽ ብክለት ቁጥጥር ደንብ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጿል። ይኽ ደንብ በሥራ ላይ ያለውን የብክለት አዋጅ ቁጥር 300/2002 በተለይም በድምጽ ብክለት ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ማስፈፀሚያ እንደሚሆን የኮሚሽኑ የፖሊሲ፣ ሕግና ደረጃዎች ጥናትና ዝግጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር አየለ ሄገና ገልፀው ነበር፡፡ ዳይሬክተር ጀነራሉ እንዳብራሩት ደንቡ የድምጽ ብክለት ምንጮችን በተለያዩ ቀጠናዎች የተለዩ ሲሆን ቀጠናዎቹ በሚያወጡት የድምጽ መጠን መሠረት የመኖሪያ፣ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና ቅይጥ በሚል መከፋፈላቸውን አስረድተዋል፡፡
በደንቡ ውስጥ ከተካተቱት አንኳር ነጥቦች ውስጥ ማንኛውም ፈቃድ ሠጪ አካል ለማንኛውም አገልግሎት ፈቃድ ሲሠጥ የቀጠናውን የድምጽ ልቀት መጠን መሠረት ያደረገ መሆን እንደሚገባው፤ የድምፅ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከቀረጥ ነፃ በሆነ መልኩ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ስለሚያስች ማበረታቻ መደረጉን ፤ የድምጽ ብክለት ተቆጣጣሪዎች በኣዋጁ መሠረት ማንኛውም የድምፅ ብክለት ያለበት ቅጥር ግቢ በመግባት ብክለትን የመቆጣጠርና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ማስረጃዎችን የመሠብሠብ እንዲሁም የሚወሠነውን ውሳኔ ወይም ማንኛውም ሕጋዊ እርምጃ እንዲፈጸም የማድረግ ኃላፊነት እና የመሣሠሉት በደንቡ ውስጥ እንደተካተቱበት ዳይሬክተር ጄነራሉ አብራርተዋል፡፡
የድምጽ ብክለት የተለያዩ ጉዳቶች የሚያስከትል ሲሆን በጤና ላይ (የመስማት ችሎታን የመቀነስ፣ በነርቮች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ በልብ ጤናማ አሠራር ላይ ጉዳት ማድረስ) ፤ በማሕበራዊ ኑሮ(የመቻቻልና አጠቃላይ ማሕበራዊ ትስስርን መቀነስ) ፤ በኢኮኖሚ (በንብረት፣ አገልግሎቶች ጥራትና ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሣደር፣ ምርታማነትን መቀነስ) ከብዙ ጉዳቶቹ ውስጥ የተወሠኑት ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ኮሚሽኑ በሐገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በመጋቢት 2011 ዓ.ም በከተሞች እየከፋ የመጣውን የድምፅ ብክለት መከላከል የሚያስችል ተግባራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ይኸው የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን አሳውቆ ነበር። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ጋር በመቀናጀትም በከተሞች የድምፅ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል ንቅናቄ መጀመሩን ገልፆ ነበር። ከከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለተውጣጡና 600 ያህል ለሚሆኑ የዘርፉ አመራሮችና ሠራተኞች ወደ አፈፃፀም ለመግባት የሚያስችል ግምገማዊ ስልጠና ሰጥቶም ነበር።
በወቅቱም የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን የአካባቢ ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ክብርት ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ እንዳሉት የኢፌዲሪ ህገ መንግስት (44፣1) ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው መደንገጉን ገልፀው በአፈፃፀም ጉድለት ምክንያት ይህ መሠረታዊ የዜጎች መብት በተሟላ ሁኔታ አለመከበሩን ገልፀዋል፡፡
ም/ኮሚሽነሯ አክለውም እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ሀላፊነት የተጣለበት ከፌደራል እስከ ክልሎች የሚገኘው የዘርፉ አስፈፃሚ አካል ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገባ በማሳሰብ ለአፈፃፀም የሚያስፈልጉ ማናቸውንም ድጋፎች ኮሚሽኑ እንደሚያደርግ ነው የገለፁት፡፡
በመድረኩ የቀረቡ ጥናቶችም የአካባቢ ብክለት የተለያዩ መስኮች (Medias) እንዳላቸውና (የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ብክለት፤) የአየር ብክለት፤ የአፈር ብክለት የውሀና የድምፅ ብክለቶች በሚል ለይቷቸዋል።
ይሁንና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከድምፅ ብክለት የጤና ጦሶች የሚታደጋቸው ተግባር አላገኙም። አዲስ አበባ በአንዳንድ ታዛቢያን የሞንታርቦ ከተማ የምትሰኘውም ለዚህ ነው። የከተማዋን የድምፅ ብክለት ለማስወገድ የወጡ ሕጎችና መመሪያዎች በሞንታርቦውና ክላክስ ድምፆች ተውጠዋል። ታፍነዋል።
ሕጉ ለስንት ዘመን ይሆን በስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጥ የአዳራሽ ሲሳይ እንደሆነ የሚቀጥለው?