ፓለቲካ እና ኃይማኖት በፖለቲካዊ – ጂኦ-ፖለቲካዊ ገበያ

    ▪️ እስሌማን ዓባይ ✍️


ፓለቲካ እና ኃይማኖት በፖለቲካዊ – ጂኦ-ፖለቲካዊ ገበያ

   ▪️ እስሌማን ዓባይ ✍️

ሀገረ ቱርክ ለእስራኤል እውቅና የሰጠች የመጀመሪያ ሙስሊም ሀገር መሆኗ ይታወቃል፤ ጊዜው ደግሞ 1949 እኤአ። ኤርዶጋን የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ዘመን (2005 ላይ) እስራኤልን ጎበኙ። በወቅቱም የምእራብ እስያ የሰላም አሸማጋይ ለመሆን ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ይፋ አደረጉ።

ኤርዶጋን ፕሬዝደንት ከሆኑ ወዲህ አሜሪካ በእስራኤል የሚገኘው ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ማዛወሯን ተከትሎ 2018 ላይ ቱርክ የእስራኤል አምባሳደሯን ጠርታ ነበር። ግንኙነታቸውም በዚያው መሻከር ጀመረ። ኤርዶኻን በማስከተል እስራኤልን አሸባሪ መንግስት ሲሉ ገለጿት። እስራኤልም በምላሿ ቱርክን ለሀማስ ፈንድ በማቅረብ ወነጀለች።

ከሶስት አመት በኋላ ማለትም በዘንድሮው ጥር 2022እኤአ ኤርዶዃን እስራኤልን ከወር በኋላ ለመጎብኘት እቅዳቸውን ይፋ አደረጉ። “የቱርክ እስራኤል አዲስ የትብብር ምእራፍ ሲሉም እቅዳቸውን ገለፁ”።

ኤርዶዃን በቅርቡ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት የአቋም ፅናት በተለየ ፈጣን የፖሊሲ መለዋወጥ እያሳዩ መሆናቸውን ታዝበናል።
እዚጋ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ በመቀሌ ያደረገው ንግግር ስለ ቱርክ-ኢትዮጵያ ወቅታዊ አቋም የተናገረው ውሃ የማያነሳ በሚለው ተመልክቸው ብቻ አልፋለሁ። ጌቾ በትግርኛ ባደረገው ንግግሩ “ቱርክ ከኢትዮጵያ መንግስት ያለኝን ትብብር ቆም ብየ መመልከት ጀምሬያለሁ” አይነት መረጃ እንደሰጠቻቸው ነው ያወራው።
የጌቾን በዚሁ ከመዝጋታችን በፊት የቱርክ ሚዲያዎች ከቀደሙ ጊዜያት በተለየ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ቀውስ የህወሃት ደጋፊ አለማቀፍ ተቋማትን መግለጫ እንደወረደ መዘገባቸውን እንጥቀስ። በተለይም ከአንድ ቀን በፊት TRT ያወጣውን ዘገባ በማሳያነት በስክሪን ሻት ምስሉ ውስጥ አካትቼዋለሁ።
ኤርዶጋን ከሰሞኑ ያደረጓቸውን የፖሊሲ ሺፍት ላይ ስናተኩር ተከታዮቹን እናገኛለን።
▪️ “ዓለም ከአምስት ሀገራት በላይ ግዙፍ ናት” በሚለው ዝነኛ ንግግራቸው እንዲሁም “A fairer world is possible.” በማለት “ፍትሃዊ ዓለምን እውን ማድረግ ይቻላል” በማለት ጭምር የምዕራባዊያኑን አድልዖና ኢፍትሀዊነት ሲያወገዙ የሚታወቁት ኤርዶጋን በፀጥታው ምክር ቤት ሩሲያን ከሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ስለማስወገድ በተደረገው ድምፅ አሰጣጥ ላይ ቱርክ በአለም ጉዳይ ላይ ከአምስት ሀገራትም በታች አንድ አሜሪካ የጠራችውን ቅስቀሳ በመደገፍ ነበር።
▪️በዚሁ ሰሞን ኤርዶጋን ያሳዩት የፖሊሲ ለውጥ ሳኡዲ አረቢያንና በሳኡዲ ደህንነት የተገደለውን ጋዜጠኛ ይመለከታል። ኤርዶዃን በዚሁ ወቅት መነጋገሪያ በሆነው የጋዜጠኛው ጉዳይ ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ከማውገዝ ተቆጥበው ከሳኡዲ ጋር ስለመቀራረብ ማውራትን ነበር የመረጡት።
▪️ከጥቂት ቀናት ወዲህ ደግሞ በአልአቋሷ መስጂድ የእስራኤል ሀይሎች በርካታ ፍልስጤማዊ ዜጎችን ለጉዳት የዳረገ ጥቃት አደረሱ። በመሰል ጉዳይ ላይ ከሁሉም ቀዳሚ እና ብርቱ የውግዘት መግለጫቸው የሚታወቁት ኤርዶጋን የሰጡት ምላሽ በቅርብ ከእስራኤል ከተጀመረው ቅርርብ አኳያ እክል እንዳይፈጥር የሚለው ላይ በማተኮር ነበር። ይኸውም እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ ያደረሰችው ጥቃት የቱርክና እስራኤልን ቅርርብ አያደናቅፈውም” በማለት ነው እምነታቸውን ያሳወቁት። በተረፈ ስለ ፍልስጤማውያን የደረሰባቸውን ጥቃት በተመለከተ “የእስራኤል ሀይሎች ጣልቃ መግባታቸው ስህተት ነው” ከማለት የዘለለ አልነበረም።
▪️ ቱርክ የሩሲያ ሲቪልም ሆነ ወታደራዊ አይሮፕላኖችን በረራ ከልክያለሁ ያለችው ደግሞ በትላንትናው እለት ነው።

እንግዲህ ኤርዶጋን ስለ ሩሲያ፣ ስለ ሟቹ ጋዜጠኛ፣ ስለ ፍልስጤምና የመሳሰሉ ጉዳዩች ያሳዩት የአቋም ለውጥ ከምን የመነጨ ስለመሆኑ ተጨባጭ ትንታኔ ባይቀርብም የተለያዩ ምልከታዎች መንፀባረቃቸው አልቀረም፦
-ከግሪክ ጋር ያለውን የይዞታ ይገባኛል ውዝግብ ለማብረድ
-በአርመናዊያን ላይ ቱርክ ዘር ማጥፋት ፈፅማለች የሚለውን ጫና ለማክሰም
-ቱርክ ከአውሮፓ ህብረት የምትፈልገውን አጀንዳዋን በወቅታዊው ትኩሳት መሀል ለማሳካት
-ከእስራኤል፣ ከሳኡዲ፣ ኤምሬትስ፣ ግብፅ… ሀገራት በጥቅሉ ከጀመሩት የቅርርብ ፖሊሲ ጋር ወዘተ.. የሚያያይዙት ልሂቃን በርካታ ናቸው።
ከነዚህ ሁሉ የቱርክ መግለጫዎች በኋላ ታዲያ አሜሪካ ለአንካራ አልተኛችላትም። በትላንትናው እለት ከፕሬዝደንት ባይደን እስከ ካረን ቤዝ ድረስ ቱርክ በአርመን ላይ ዘር ማጥፋቷን አሜሪካ እንደምታወግዝና ይህንንም ሌሎች ሀገራትና ተቋማትም እንዲስማሙበት ድጋሚ ጠይቀዋል።
ይህን ከሆነ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬስን ወደ አንካራ ጉዞ ያደረጉ ሲሆን አቀባበል ካደርገውላቸውና ከተወያዩ በኋላ ኤርዶጋን ተከታዩን መግለጫ ሰጥተዋል።
“የአሜሪካ መሪዎች ታሪክን ጠንቅቀው ሊማሩና ሊያውቁ ይገባል። ይህ ቱርክን ለመፈታተንና የሚደረግን ሙከራ እንዲሁ “ታሪካዊ” እውቀት የሌላቸውን ይቅር ልንላቸው አንችልም”
በማለት ነበር የቁጣ ማስጠንቀቂያ የሰጡት። እዚጋ የኤርዶጋን ሰሞነኛ የፖሊሲ መለዋወጥ ታላሚውን ግብ እየመታ ይሆን የሚለው ጥያቄ ይነሳል ማለት ነው።

ትኩረታችን ፖለቲካና ከእምነት እየተዛነቀ የመጓዙት ጎጂ ድርጊት ለያይቶ መመልከት ነው። ሌላ የቅርብ ጊዜ ማሳያ መጥቀስ እንችላለን።
በአርመንና አዘርባጃን በቅርብ የተደረገው ጦርነት ውስጥ ከሁለቱ ሀገራት አንዱን በመደገፍ እጃቸውን ያስገቡ አገራትን እናውሳ። መንስኤው ፖለቲካ — ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳይ በመሆኑ በዘር ግንድም ሆነ በእምነት ከሚመሳሰላቸው በተቃራኒው የሚገኘውን ሲደግፍ ታዝበናል።
ለምሳሌ ኢራን አርመንን መደገፏን እንመልከት። ከኢራን 80 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ከ 30 ሚሊዮን የሚበልጡት አዘርባጃኖች ናቸው። ይህ አሀዝ ማለትም በአዘርባጃን ካሉት አዘርባጃኖች በላይ በኢራን የሚኖሩ አዘርባጃኖች ቁጥር አላቸው። እነዚህ በኢራን የሚኖሩ አዘርባጃኖች በአገረ አዘርባጃን ካላቸው ግዛተ ወሰን በሁለት እጥፍ የሚሰፋ ነው። አዘርባጃን ከኢራን ቀጥሎ ከፍተኛው የሺአ ህዝብ መኖሪያ ነው። በእምነት ኦርቶዶክስ በባህልም ለማትቀርባት ነገር ግን ለጂኦ ፖለቲካዋ የምትጠቅማት አርሜኒያ ናትና ወዳጅ ሆናታለች። ኢራን ሰሜን አዘርባጃንን ወደ ኢራን ለመቀላቀል የሚዋጋ ታጣቂ አንጃ በመሬቷ እንዲመሰረት አድርጋ እንደነበርም ይታወቃል።

እስራኤል ደግሞ አዘርባጃንን ደግፋለች። ከቱርክ ተመሳሳይ አቋም ሲሆን ከኢራን ተቃራኒ መሆኑን መርጣዋለች። ዘመነኛ የተባሉትን ሰው አልባዎ ጄቶቿንም አስታጥቃታለች። ThunderB, Orbiter 3, SkyStriker, and IAI Harop የተባሉ ቴክኖሎጂዎች ከዋናዎቹ ናቸው። በተለይም IAI Harp የተባለው የእስራኤል ሰው አልባ (drone) የአርመንን ወታደራዊ መሳሪያዎች በስፋት ሲያወድም ታይቷል።

በዚህ የሀይማኖት-ፖለቲካ ‘ሚስቶ ‘ማሳያነት በሀገራችን ተመሳሳይ የውስጥ ውዝግቦችና አለማቀፍ ሁነቶች ላይ ጉዳዮችን እንዴት እየፈረጅናቸው እንደምንገኝ ራሳችንን እንጠይቅ።

በእኔ በኩል ነገሮች… “አምበሳም ለሆዱ፣ ዝሆንም ለሆዱ፣ ነብርም ለሆዱ: ወንዝ እንደወረዱ፤ እርሶ ተወለዱ” ነውና ተረቱ፣ … ጉዳዩ ፖለቲክስ ሆኖ እያለ በአንድ ወገን መረጃ ላይ ተመስርተን አንዱን ደግፈን ሌላውን እንረግማለን፤ በየዋህነት….እውነታው ዘላቂ ጥቅም እና እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ የወዳጅነት ቃል-ኪዳን ቢሆንም ቅሉ፣ ሲቪሉ ህዝብ ግን ነገ የሚለዋወጠውን ፖለቲካዊ የቃልኪዳን ጤዛ ወደ ቁስአካልነት ለመለወጥ አላስፈላጊ ዋጋ እና መስዋእትነት ሲከፍል ይታያል~~~
ሰላም ለሀገራችን ለምድራችን

#የዓባይልጅ #EslemanAbay

Telegram:
https://t.me/eslemanabayy

Twitter: https://twitter.com/eslemanabayy?t=JKWNRtromTjEOKsqBvV0ZA&s=09

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories