When Egypt's Media arrative & Disinformation Exposed

ነገረ – ውኃ፣ መጪዎቹ ዓመታት እና ኢትዮጵያ

By Esleman Abay

May 11, 2024

   By, Esleman Abay፡ የዓባይ፡ልጅ

  …ዓለማችን በውሃ እጥረት ስትፈተን፤ ኢትዮጵያችን ደመናዋም ዝናቡም ይበዛላታል፤ የዓባይ ውሃ ባለቤትነቷ በምንም የማይሸጥ ፀጋዋ…

 በአሜሪካ ዋሽንግተን የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ባሰናዳው የህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ የተረቀቀውን የውሃ ድርሻ ክፍፍል የተመለከተ ስምነት ብንፈርም ኖሮ ወደፊት(በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ)፣ ከሚፈጠረው አለም አቀፍ ሁኔታ አንፃር በተለይም ከቀጣዩ ትውልድ የሚሰነዘረውን ወቀሳ በኛ የመረረ የሚያደርግ ነበር። ምክንያቱም መጠነ ሰፊ የድርቅ መከሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ የውሃ ዋጋን መተኪያ የለሽ ማድረግ አሁንም ጀምሮታል – በዬአመቱም እየከፋ ቀጥሏል።

መጪው ዘመን የሚያስተናግደው የአየር ንብረት ለውጥ ድፍን አለምን ለውሃ እጥረት የሚዳርግ ይሆናል። በርካታ ጥናቶችም ይህንኑ አስጠንቅቀዋል። አንዳንድ ሀገራት የሚያገኙት ዓመታዊ የዝናብ መጠን እስከ ዜሮ ድረስ እምደሚሆን እና፤ በድርቅ የታጀቡ ተከታታይ አመታትን ማስተናገድ የሚጠበቅ የምድራችን ስጋት ሆኗል። እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን መቀነስ አደጋጋ አብዛኞቹን የሚጋረፍ መከራ ይሆናል ነው የተባለው። በዝናቡ እጥረቱ ሳቢያ የሚፈጥረው የአፈር ርጥበት ማጣትና የምርታማነት መንጠፍ አይቀሬ ስጋት ነው ተብሏል።

እኛ የምንገኝበት የናይል ላይኛው ተፋሰስ ተራራማ አካባቢ ግን፣ በሚገርም ተቃርኖ ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኝ ይሆናል። ተፋሰሱ የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ዓባይ/ናይልን ይዟል። ናይል 11 የአፍሪካ አገራትን አቋርጦ የሚያልፍ ሸለቆ ያቅፋል። ተፋሰሱም 10 በመቶውን የአፍሪካ ምድር ይሸፍናል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ግብፅ ከሚኖሩ ዜጎች ውስጥ 250 ሚሊዮን የሚሆኑት ህይወታቸው የዓባይ ወንዝ በሚሰጣቸው ውሃ ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፡፡

የአየር ንብረት (የየያዝነው ክፍለ ዘመን ማብቂያ) ትንበያዎች እንደሚጠቁሙት፣ በላይኛው የናይል ተፋሰስ አካባቢዎች 20 በመቶ የሚደርስ የዝናብ መጠን ጭማሪ የሚያገኙ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ ይኸው የተፋሰሱ አካባቢ አስከፊ ሞቃታማ እና ደረቅ አመታት/spells በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ ነው የተተነበየው፡፡

በያዝነው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በእጥፍ እንደሚጨምር ከተተነበየው የህዝብ ቁጥር ጋር የሞቃታማና ደረቃማ አመታት ድግግሞሽ በቀጠናው በአንድነት ይከሰታሉ።  በተጠቀሰው የክፍለ ዘመን አጋማሽ (2040 – 2050 ገደማ) የዝናብ መጠኑ የተጠቀሰውን እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ የሚያገኙ  ቢሆንም በወቅቱ የሚኖረውን የሕዝብ ቁጥር ለማዳረስ ከፍተኛ እጥረት ይገጥመዋል። ከተፋሰሱ ፈቀቅ ብለው በሚገኙትና ድርቅ ከሚበረታባቸው አካባቢዎች ውሃ ወደሚኖርባቸው ማዝገም፣ የሚገኘውን የውሃ ፀጋ መሻማት ብሎም መሻኮትና መፋጠጥ ተጠባቂ የህልውና ግብግብ ሆነው ይመጣሉ – በቀጠናውም የውሃ ውጥረት/Water Tension የዕለት ተዕለት ገፅታ ይሆናል።

አሁን ላይ በአካባቢው ባለው የዝናብ ወቅታዊ መዋዠቅና የውሃ ሀብት ክፍፍሉ ኢ-ፍትሃዊነት ሳቢያ ከተፋሰሱ ነዋሪዎች 10 በመቶው በከባድ የውሃ እጥረት ውስጥ ይገኛል፡፡ በፈረንጆቹ 2040 የውሃ እጥረት የሚያጋጠማቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 35 በመቶ ይደርሳል – ይህም፣ የዕለት ኑሯቸውን ለመምራት በቂ ውሃ የማያገኙ ሰዎችን ቁጥር ከ 80 ሚሊዮን በላይ ያደርሰውል ከታች በዋቢነት ያስቀመጥኳቸው ጥናቶች እንደሚጠቁሙት።

የሞቃትና ደረቅ አመታት ከሌላው ዘመን በተለየ ሁኔታ ቶሎ ቶሎ መከሰት የችግሩ አንዱ መገለጫ ሲሆን፣ ይህም ሰብሎችን  ይገድላል፣ የውሃ ሃይል ማመንጫዎችን አቅም ያዳክማል፣ ለሰውና ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን የውሃ መጠን ያሳንሳል። በውጤቱም በቀጠናው የውሃ ሀብት ድርሻ የሚፈጥረው ውጥረት አደገኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ችግሩ በ 2040 በአካባቢው ከሚኖረው ህዝብ 45 በመቶ ማለትም ከ 110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የናይል ተፋሰስን ተጠግቶ መኖርና የውሃ እጥረቱን ለመቅረፍ የህልውና ትግል ለማድረግ ይገደዳል፡፡

ደረቅ አመታት ባይከሰቱም እንኳን የህዝብ ቁጥሩ መጨመር ብቻውን ለላይኛው ተፋሰስ የውሃ እጥረት መከሰት በቂ ምክንያት ይሆናል፡፡ በሞቃት-ደረቅ ዓመታት ሳቢያም ባካባቢው ከ 5% እስከ 15% የሚሆን ተጨማሪ ህዝብ ለውሃ እጥረት ይዳረጋል። የእነዚህ ችግሮች መባባስ ቀድሞውኑም ውስብስብና በውጥረት የተሞላውን የቀጠናው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተና የተባባሰ ያደርገዋል፡፡ ሌላው አደጋ ደግሞ የሞቃት እና ደረቅ ዓመታት በፍጥነት የሚደጋገሙ መሆናቸው ነው።

   የዘርፉ ምሁራን በተፋሰሱ ከ 1961 እስከ 2005 ጊዜ መካከል የነበረውን የዝናብና ሙቀት መጠን ዳታዎች በመተንተን መጪውን ሁኔታ ለመተንበይ አውለውታል፡፡    ግኝታቸው የሚያሳየውም ባለፉት አራት አሥርት ዓመታት በላይኛው ተፋሰስ አካባቢ ሞቃታማ-ደረቅ ዓመታት በየ 20 ዓመቱ አንድ ጊዜ ተከስቷል፡፡ ድግግሞሹ ጭማሪ ወደፊት ባለው ጊዜ በዬ 6 እና 10 ዓመት አንድ ጊዜ ሊከሰት እንደሚችል ተተንብይዋል።ይህም በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የተለመደ ተሞክሮ ነው ፡፡የቀጠናው ሙቀትም ከ 2 እስከ 6 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ይላል። ይህም እስካሁን ከተከሰቱት ሁሉ በባሰ ሁኔታ በሰዎች፣ በእንስሳትና ሰብል ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል፡፡

ለተፋሰሱ መፃኢ የውሃ እጥረት ችግር የተለያዩ መፍትሄዎች ተቀምጠዋል። አንዱና የመጀመሪያው የተፋሰሱ አገራትን የውሃ ድርሻ ፍትሃዊ ማድረግ የሚል። በተለይም የግብፅን የቅኚ ግዛት የውሃ ድርሻ ስምምነት ማደስ የሚጠቅስ። እንግዲህ ይህ ባለበት ሁኔታ ነው ግብፅ የውሃ ድርሻዋን 41 ቢሊየን ሜ.ኪዩብ እንድንፈርምላት በትራምፕ ጫና ልትጫወትብን የነበረው። እስካሁን ተደርሷል በተባለ ስምምነት በግድቡ የውሃ ሙሊት ላይ ብቻ መሆኑ ከዋንሽግተኑ ወጥመድ የተላቀቀ ይሆናል።

ግብርና ዋናው የኢኮኖሚዋ መሠረት በሆነባትና የናይልን ውሃን ወደ 80 በመቶ የሚጠጋ የውሃ  መጠን የማበርከት አቅም ያላት ኢትዮጵያ፣ በድርቅ ስጋት ከተመላከቱት ቀጣይ አመታት ጋር ተገናኝታ በብርታት የምትሻገርበትን በትር ይኖራት ዘንድ አሁን ላይ፣ በዓባይ/ናይል የውሃ ድርድሮች ላይ በግብፅ እንዲሁም በግብፅ አጋር መንግስታት በኩል ከሚቀርብ ባለወጥመድ የስምምነት ድር ሳትጠለፍ ተቋቁሞ በመቀጠል ፅኗቷ ላይ የተመሰረተ ነው የሚሆነው።

ለኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ባለቤትነቷን ማረጋገጥና ማስጠበቅ አለባት የሚለው ምክረ ሐሳብ ጉዳዩየእራት፣ የመብራት፣ የሐብት፣ የጉልበትና የሌሎችም ትሩፋቶች መሠረት ከመሆኑ እውነታ አንፃር መሆኑ አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ በዓባይ የውሃ ሃብታችን የማዘዝ ልዕልናችን ተጠብቆ ውሃ ብርቅዬ በሚሆንበት ቀጣዮቹ ዘመናት ለሀገራችን የኃያልነቷ መደላድል እንዲሆናት የሚለው ደግሞ ሌላኛው ምልከታ ነው።

በአንፃሩ ድርድር ላይ በህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ተስማምታ፤ ነገርግን በዓባይ ውሃ ላይ ካይሮ የማይነካ ድርሻ እንዲኖራት ኢትዮጵያ በፈርማ እንድትስማማላት የማድረግ ጥረቷን አሁንም ቀጥላበታለች። የዚህ ጥረቷ ዋነኛ ሰበብ የተደበቀ አይደለም — ከምንም በላይ የተወደደ በሚሆነው የውሃ መፃዒ ዋጋ ውስጥ እንደ ድሮው በነፃ የማትረፍ እና ያለ ድካም የመጎልበት ፍላጎቷ በኢትዮጵያ መዳፍ ስር እንዳይውል የምታደርገው ግብግብ ነው።

▪️Neukom Institute & Dartmouth ኮሌጅ፣ የድህረ-ዶክትሬት ማሟያ ጥናት፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ተቋማት ጥናቶችና ከመረጃ ምንጮች ማጠናከሪያዎችን በማሰባሰብ የተጠናቀረ።▪️https://eslemanabay.com/in-the-future-there-will-be-more-rain-but-less-water-in-the-nile-basin/▪️https://eslemanabay.com/in-the-future-there-will-be-more-rain-but-less-water-in-the-nile-basin-2/▪️https://www.google.com/search?q=more+rain+less+water+nile&oq=more+rain+less+water+nile&aqs=chrome..69i57j33j69i60l2.8860j0j1&client=ms-android-lenovo&sourceid=chrome-mobile&ie=UTF-8