Horn Affairs አፍሪካ ቀንድ

የምዕራባዊያን ዕርዳታ ጥቋቁር ምዕራፎች

By Esleman Abay

June 17, 2023

የካሪቢያኗ ደሴታዊት ሀገር ሔይቲ ከአስር አመት በፊት በደረሰባት ሱናሚ የ 200,000 ዜጎቿን ህይወት የቀጠፈ ነበር። የአደጋው አሳዛኝ ፎቶዎች በመላው ዓለም ሲሰራጩ ለርዳታና ለመልሶ ግንባታ ተከታታይ ቃል ኪዳኖች ተደመጡ..፤ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ መወሰኗን አስታወቀች፤ ይሁን እንጂ የዚህ ገንዘብ ሽራፊ ብቻ ነበር ወደ ሔይቲ የደረሰው።

የዳሰሳ ጥናት ውጤቶች እንደሳዩት በወቅቱ ሔይቲ የሚገኙ በጎ አድራጊዎች እጅ የገባው ገንዘብ ተከፈለ ከተባለው ርዳታ 0.9 በመቶው ብቻ ነበር። ቀሪው ገንዘብ የት ገባ? በዚያው ከዩናይትድ ስቴትስ እንዳልወጣና አብዛኛው መጠንም ወደ አሜሪካዊ የግል ኮርፖሬቶች አካውንት ሰርጎ ነበር የቀረው። ይሁንና ከዚህ ቀጥሎስ፣ ያ ገንዘብ በአሜሪካ ምን ላይ እንደዋለ ምንም መረጃ አልተገኘም። በስማቸው የተነገደባቸው ዜጎች የስቃይ ኑሯቸውን ቀጠሉ፤ የሔይቲ 100,000 ዜጎች የውስጥ ተፈናቃይ ሆነው አሁንም በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ተረስተው ነው የሚገኙት።አብዛኛው ዕርዳታ ለታለመለት ምስኪን አይደርስም ሲባል መልካም የሚሰሩ ጥቂቶችንም ቢሆን ማስቀየም እንዳይሆን ፅሁፌን በመረጃዎች ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ግድ ይላል።

አለም አቀፍ የኦዲት ውጤቶች ያስቀመጡት ከውጭ ዕርዳታዎች 1/5ኛው ገና ከጅምሩ ከለጋሽ ሀገራት ፈጽሞ እንደማይወጣ ነው። ይህ አይነቱ የርዳታ ማጨናበር በለጋሽ አካላት ባንክ ተቀምጦ ይቀራል፤ ወይም መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ይሰጣቸዋል፤ ነገር ግን ለተረጂዎች አይደርስም የሚለውን እውነት የያዘው ነው።በፈረንጆቹ 2011 ያደጉ አገሮች 100 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ገንዘብ ሰብሰቡ፤ ገንዘቡ ለታዳጊው ዓለም የሚሰጥ የውጭ ዕርዳታ ነበር፤ መጠኑን እደግመዋለሁ 100 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ከዚህ ውስጥ 22 ቢሊዮን ዶላሩ ፍፁም ከሀገራቱ ሳይወጣ ነበር የቀረው።በተመሳሳይ አመት ጣሊያን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለዚሁ ርዳታ ሰብስባ ነበር። ይሁንና 300 ሚሊዮን ዶላሩ ብቻ ነበር አገሪቱን ለቆ የወጣው። ቀሪው ተላልፏል የተባለ የ 1.7 ቢሊዮን ርዳታ እዛው ጣልያን ቀርቷል።

በፈረንጅ 2019 ይፋ የተደረገ ሌላ ሪፖርትም ነበር። ሪፖርቱ፣ 25 በመቶ የሚሆነው ዕርዳታ ከለጋሽ ሀገራት እንደማይወጣና የቀረው 75 በመቶውም ለርዳታ ተቀባዮቹ በቀጥታ እንደማይደርስ ይገልፃል። ይህ ርዳታ በበርካታ ኤጀንሲዎች ውስጥ ያልፋል። እያንዳንዱ ኤጀንሲ የየድርሻውን ይቆርጣል። ችግሩ ይባባስ ዘንድም በእያንዳንዱ ኤጀንሲና ኮርፖሬት የሚፈፀመው ተቆራጭ ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት የለበትም፤ ወይም በጣም የላላ ነው። አለም አቀፍ ዕርዳታ የአንድ ጊዜ ስሌት ውጤት አለመሆኑና በውስጡ የበርካታ ውስብስቦሾችና መዳፎች ስብጥር ያለበት መሆኑ ለችግሩ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ሆኗል። የርዳታ ፕኬጅ ከፊሉ ጥሬ ገንዘብ ነው፣ ሌላው የምግብ አቅርቦት፣ የተቀረው ደሞ የብድር ዕዳ እፎይታ ይሆንና አለፍ ሲልም ሰዎች ጭምር ዕርዳታው ውስጥ ተካትተው የሚመጡበት አሰራርም አለ። ይህም ለቴክኒክ ድጋፍ አማካሪዎችና ሠራተኞች ከርዳታው ላይ ይከፈላቸው ዘንድ የሚጠይቅ አሰራር ነው። እነዚህ ባለሙያዎች በዕርዳታ ለጋሾች በኩል የሚላኩ ናቸው። መሰል የዕርዳታ ማጨናበር ጥቁር ታሪኮችን ለማጣቀስ የምስራቅ ኤሺያ ሀገሯን ቲሞር ታሪክ እናውሳ።ቲሞር ከነባር ግዛቷ ተገንጥላ ሀገር እንድትሆን ድጋፍ ተደረገላትና የዛሬ 20 አመት ገደማ (በፈረንጅ 1999) ነፃነቷን አገኘች ተባለ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቲሞር ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ርዳታ ተቆርጦላታል። ከዚህ ውስጥ ታዲያ ሁለት ቢሊዮን ዶላሩ በሀገሪቱ ተሰማርቶ ለሚገኘው የተመድ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ብቻ የዋለ ነው። ቀሪው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በዕርዳታ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ወጪ ያደረጉት ነው። ቀሪውስ? በዚህችው ሀገረ ቲሞር የ UN ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደሞዝ ከአካባቢው ነዋሪ በአስር እጥፍ ይበልጣል። ለምሳሌ፣ ከአውስትራሊያ ወደ ቲሞር የመጣ የተ.መ.ድ ሰራተኛ 200,000 ዶላር ይከፈለው ነበር፣ ይህ የሚሆነው ታዲያ 50% የሚሆነው ህዝቧ በቀን ከ 2 ዶላር በታች የሚያገኝበት በሆነችው ሀገር ላይ ነው።

“ጥርንፍ-ርዳታ” ወይም Tied-Aid ተብሎ የሚጠራ ስትራቴጂም አዘጋጅተዋልና በዚህ ዘዴ የሚጭበረበረው ዕርዳታ ደግሞ ተከታዩን መልክ የሚይዝ ነው። በዚህ ጥርንፍ-ዕርዳታ የሚባል አሰራር ብድሩ የሚተሳሰረው ከለጋሽ አገሮች የቢዝነስ ኩባንያዎች ጋር ነው። ለጋሿ አሜሪካ ከሆነች ብድሩ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር የተሳሰረ ጥርንፍ-ርዳታ ይሆናል ማለት ነው። እነዚህ ኩባንያዎችም ገንዘቡ እንዴት ወጪ እንደሚደረግ የሚወስኑ ይሆናሉ። እንደ ጥናታዊ ሪፖርቶች በ 2012 ከ 14% በላይ የሁለትዮሽ ዕርዳታ በዚሁ Tied-Aid ስር ማለፉ የታወቀ ሲሆን በ 2017 ከ 15% በላይ፣ በ 2018 ከ 19 በመቶ በላይ አድጓል።ይህን የጥርንፍ-ርዳታ የሚከተሉ ሁሉም ርዳታ ሰጪ ሀገራት ናቸው ማለት ይቻላል። ዩናይትድ ስቴትስ በሰንጠረዡ አናት ላይ ትገኛለች። በ 2018 የፈረንጅ አቆጣጠር 40% የሚሆነው ዕርዳታ ማለትም 11 ቢሊዮን ዶላር የተገመተ ነው – አሜሪካ በ Tied-Aid ዘዴ ያስተላለፈችው። ጃፓን ከ 22% በላይ ይኸውም ከ 4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጥርንፍ ርዳታ ዘዴ ትለግሳለች። ጀርመን 15% ርዳታዋን ወይም 3.1 ቢሊዮን እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ ከ 48% በላይ ዕርዳታዋን በጥርንፍ Tied-Aid አስተሳስራ ልገሳ ትፈፅማለች።እንግዲህ እነዚህ ሁሉ አገሮች ዕርዳታ ለመስጠት ቃል የሚገቡ ናቸው። ነገር ግን ርዳታውን ለተቀባይ አገሮች ከመስጠት ይልቅ፣ ለኩባንያዎቻቸው ያስተላልፋሉ። ምክንያቱም የእርዳታ ገንዘቡ በቀዳሚነት የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስከበር ያለመ በመሆኑ ነው።

ከአመታት በፊት የወጣ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይል ነበር፡- “ብሪታንያ ለውጭ ርዳታ የምትመድበው በጀት በተቸገሩ ሰዎች ስም ኪሳቸውን ለሚሞሉ የድህነት ከበርቴዎችና የግል ተዋንያን ተፈልፍለውበታል።” ሲል ነው የሚያትተው። [ Britain’s foreign aid budget had created a group of poverty barons, private players, who were filling their pockets in the name of helping disadvantaged people. ]በዚህ ሁነት ውስጥ ኃላፊነት የተሰጠው የእንግሊዝ መንግስት ድርጅት ጭምር የዕርዳታ ገንዘብ ሲያጭበረብር ተገኝቷል። DFID, የእንግሊዝ መንግስታዊ ኤጄንሲ ሲሆን የውጭ ርዳታን እንዲያሳልጥ የተቋቋመ ነበር፤ ሙሉ መጠሪያው Department for International Development የሚሉት ነው። ይህ የእንግሊዝ መንግስት የእርዳታ ኤጀንሲ በፈረንጅ 2012 በተደረገ ምርመራ ለባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች €20 ሚሊዮን ዩሮ፣ የአይምሮ ጤናን ለሚከታተል አንድ ዩኒቨርሲቲ 6ሚሊየን ዩሮ፣ 3.9 ሚሊየን በአፍሪካ የሚደረጉ ምርጫዎችን ለሚያጠና መማክርት ወይም ThinkTank እና 400,000 ዩሮ ደግሞ በህንድ ለሚገኝ ቅርንጫፉ ፈርኒቸር ለማሟላት በሚል ወጪ ማድረጉ ነበር ይፋ የሆነው። ለልማት ዕርዳታስ ገንዘብ ሊተርፍ አልቻለም ነበር? ታዲያ ቀሪዋን ፍርፋሪ ብቻ ወደ አፍሪካ ሀገራት በሚል ተወሰደ ተብሏል።አብላጫው የልማትም ሆነ የችግር ጊዜ ርዳታ የሚውለው ቢሮዎችን ለመገንባት፣ በሚገርም ሁኔታም ርዳታውን እንዴት መስጠት አለብን በማለት በሚደረጉ ጥናታዊ ስብሰባዎች ላይ ነው ፈሰስ የሚሆነው። ቀሪው በርዳታ ወይም በብድር ወደ ታዳጊ ሀገራት ይሄዳል። አንዳንድ ጊዜ ቃል የተገባው ርዳታ በዕዳ እፎይታ መልክ ይለወጣል፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ገንዘቡ በተረጂ ሀገራት መሪዎች እጅ እንጂ በሕዝብ እጅ እንዲገባ የሚደረግ አይሆንም።በፈረንጅ 2011 ኮንጎ የ 7.5 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ቃል ተገብቶላት ነበር። ይበልጥ በሚገርም እውነታ ወጪ ተደረገ ከተባለው ርዳታ የተገኘው 0 ብቻ ነበር። እንዴት እንዴት..? የተባለው እንዲህ ነበር። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንዲሰጥ በሚል እስከዛውም የዕዳ-እፎይታ በሚለው መንገድ ተቀማጭ እንደሆነ ቀርቷል።2015 በፈረንጆቹ ዘመን ደግሞ ወርልድ ቪዠን የተባለ አንድ የእርዳታ ድርጅት እንዲህ የሚል ማስታወቂያ አወጣ “የአሜሪካውን ትላቅ ስፖርታዊ መድረክ Super-Bowl ን ለመውደድ – መቶ ሺህ ምክንያቶች!” የሚል የተብለጨለጨ ማስታወቂያ..። የተገለፁት መቶ ሺህ ምክንያቶች ምን ነበሩ? ነገሩ በሱፐር ቦውል የተሸናፊው ቡድን 100,000 ቲሸርቶችን የሚመለከት ነው። እነዚህ ቲሸርቶች በመጀመሪያ የታቀደላቸው ቡድኑ ካሸነፈ እንዲከፋፈሉ ነበር፣ ነገር ግን ተሸነፈ፣ ስለዚህም ይህ ገዢ ያጣው የትልቅ ብራንድ ባለቤት ቲሸርት ምርት በወቅቱ የተራቡ ህፃናት ያሉባቸው ወደተባሉት ዛምቢያ፣ አርሜኒያ እና ኒካራጓ አንዲያመራ ተደረገ።ወርልድ ቪዥን የተቸገሩ ህፃናትን ህይወት የሚቀይር ርዳታ በሚለው ስያሚው ስር ነው በስፖርቱ የከሰረውን ሽያጭ የዕርዳታ ገበያ ላይ አቅርቦ ሂሳብ ያወራረደው። ህፃናቱ በርግጥም ችግርኞች በመሆናቸው ይህን ወርልድ ቪዥን ለአሜሪካዊያን ያሳተመውን የቲሸርት ብራንድ አይተው አያውቁም ነበር።የእያንዳንዱ ቲሸርት ዋጋ 20 ዶላር ነበር። በአጠቃላይም 2 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የወጣበት..።2 ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው 100 ሺህ የሱፐር ቦውል ቲሸርቶች ለዛምቢያ ህፃናት ችግርን ባያባብስም ትርጉም የሌለው ብልጭልጭ ነበር።

ታዲያ እነዚህና እነዚህን መሰል ርዳታዎች አሁንም አሉ፤ የሚቀጥሉም ነው የሚመስለው። በሚናቸው ሲመዘኑ ቅኝ ግዛት ሆነው የሚዘልቁ አይነት ናቸው። ኢ-ርትአዊነትን ከመዋጋትና ድህነትን ከማስወገድ ይልቅ (በተለይም) ምዕራባውያኑ ንግዳቸውን ለማስፋፋትና ለትርፋማነታቸው አዋጪ ሆኖላቸዋል። ድሆችን ከመርዳት በላቀ ደረጃ በፖለቲካዊ አለማ እና በግልና የቡድን ጥቅም አቅጣጫዎች የሚመራ ነው።ይህ በርዳታ የተሸፈነ ስውር ተግባር አሁን አሁን አሳፋሪነቱን ማጣት ጀምሯል። ለዚህም ነው የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባይደን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አንቶኒ ብሊንከን፣ የUSAID ዳይሬክተሯ ሳማንታ ፖወር በቅርብ ጊዜያት በግላጭ ተናግረውታል። “ዕርዳታን የሚጠቀሙበት ለዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲ መሣሪያነት- የአሜሪካን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ዘዴ ፣ ለአሜሪካ አዳዲስ ገበያዎችን የማግኛ አስተማማኝ መንገድና ከዋሽንግተን ፍላጎት የሚስማሙ መንግስታትን ማንበሪያችን ነው።” በማለት በአንድ ቃል፣ በይፋ መግለጫ የሰጡበትና ደጋግመውም ያረጋገጡት።

✍️እስሌማን ዓባይ #የዓባይልጅ

References:

https://www.researchgate.net/publication/265144874_Haiti_Where_Has_All_the_Money_Gonehttps://www.ifw-kiel.de/publications/media-information/2019/more-than-a-quarter-of-development-aid-never-leaves-donor-countries/https://www.google.com/amp/s/amp.theguardian.com/global-development/2013/sep/24/foreign-aid-never-reaches-intended-recipientshttps://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=https://www.alnap.org/system/files/content/resource/files/main/1435.pdf&ved=2ahUKEwjX3vHqpvz7AhVFi_0HHaAtBWsQFnoECBYQAQ&usg=AOvVaw0U56nNPDyaUIuRSm-c_APkhttps://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=https://www.cgdev.org/sites/default/files/1426185_file_Ramachandran_Walz_haiti_FINAL_0.pdf&ved=2ahUKEwjX3vHqpvz7AhVFi_0HHaAtBWsQFnoECBAQAQ&usg=AOvVaw1eoKPc-J193roDe7CQWkgFhttps://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=https://digitalcommons.du.edu/cgi/viewcontent.cgi%3Farticle%3D1014%26context%3Dadvancedintlstudies&ved=2ahUKEwjX3vHqpvz7AhVFi_0HHaAtBWsQFnoECDoQAQ&usg=AOvVaw17S7vjl-KDQpfNIWscZqUAhttps://www.thenewhumanitarian.org/analysis/2022/04/04/haiti-wide-gap-between-aid-promise-and-realityhttps://www.sup.org/books/title/?id=30391https://www.opendemocracy.net/en/transformation/inconvenient-truth-about-foreign-aid/