የአፍሪካ ቀንድን ከበባ እና ጅቡቲ New Age of Imperialism In the Horn & Djibouti

አሜሪካን ጨምሮ የዘመኑ ኀያላን የአውሮፓ አገሮች በምጣኔ ሀብትና ወታደራዊ አቅም እየገዘፉ የመጡ ዘመነኛ ተገዳዳሪ አገሮች፤ አዲስ ዓይነት የአፍሪካ አገሮችን ቅርምት የተመረጡ የአፍሪካ አገራትን የመሰንጠቅ “a new scramble for Africa” መተግበር ከጀመሩ ከራርመዋል።

በዚህ የአፍሪካ አገሮችን ለመቀራመት በሚደረገው ሽሚያና አገራትን የመበለት ስትራቴጂ ደግሞ፤ ኀያላኑና ተባባሪዎቻቸውን ጨምሮ ዘመነኛ ተገዳዳሪ አገሮችና ሲያስፈልግ የሚተባበሩ፤ ሲያሻቸው የሚፎካከሩና የሚናቆሩ አገሮች ቀዳሚ የትኩረት መዳረሻቸውን፤ የቀይ ባህር ተዋሳኝ የሆኑ ምሥራቅ አፍሪካ ወይም የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን አድርገዋል።

ይህ የቀጣናው አገራትን እስከ መሰንጠቅ የሚያደርሰው አደገኛ ስትራቴጂያቸው “የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን የመቀራመት፣ ለመቀራመት የመሻማትና አገራቱን የመሰንጠቅ (በተለመዱ ቃላት አጠቃቀም የመገንጠል ወይም የመለየት” በእንግሊዝኛ አገላለጹ “The scramble for the horn of Africa” የሚል ሁነኛ መጠሪያ ወይም “የዳቦ ስም” ተሰጥቶታል። – ጌታቸው ወልዩ ]

በመሆኑም የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን የመቀራመት፣ ለመቀራመት የመሻማትና አገራቱን የመሰንጠቅ ስትራቴጂያቸው እንዲያመቻቸውና ለቅርምታቸው ዋነኛ መረማመጃቸው፣ መንደርደሪያቸውና ለከበባቸው የመሞከሪያ ሜዳ መነሻቸው (a testing playground) ያደረጓት ደግሞ፤ እንጥል የሚያክል ቆዳ ስፋት ያላትን ስትራቴጂያዊቷን አገር ጅቡቲ ነው።

ይህ አደገኛ ስትራቴጂያቸው የተቀዳውም “አገሮችን ወይም ወሳኝ ቀጣናዎችን በኀይል መጫንና በበላይነት መግዛት”
(dominates a weaker nation or region) ከሚለው “አዲሱ ዓይነት ኢምፔሪያሊዝም” (A new age of Imperialism) መርህ ነው።

እንደሚታወቀው “አዲሱ ዓይነት ኢምፔሪያሊዝም” የተጀመረው፤ የኢንዱስትሪ አብዮትን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1874 አካባቢ ሲሆን፤ እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ጅማሬ ማለትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1914 ድረስ በስፋት ተጠናክሮ ተግባራዊ የሆነ ነው።

ይህን ስትራቴጂ:- ኀያላን የአውሮፓ አገሮች “ያልሰለጠኑ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፖለቲካዊ ብቃት፣ አገራዊ አንድነትና ፀጥታና ደኅንነት ደካማ የሆኑ” የሚሏቸውን የአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅን ጨምሮ የሌሎች እስያና ላቲን አሜሪካ አገሮችን “በኀይል በመጫን በበላይነት መግዛት” (dominates a weaker nation or region) በሚል ዘዴ የአገራት ቅርምት ዘዴያቸውን ለዘመናት ተፈጻሚ አድርገውት ቆይተዋል፤ እያደረጉትም ይገኛሉ።

ከዚህ አንጻር “የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን የመቀራመት፣ ለመቀራመት የመሻማትና አገራቱን የመሰንጠቅ/የመገንጠል/ የመለየት አደገኛ ስትራቴጂያቸው ሁለት ጉልህ ወይም አንኳር ስልቶችን ወይም ዘዴዎችን ሸክፎ የያዘ ነው። እነርሱም “ወታደራዊና የንግድ ጉዳዮችን አዋህዶ ፍላጎትን ማሳካት” (mixing military interests and commercial issues) እና “ወታደራዊ ጉዳዮችን (military interests) ማዕከል በማድረግ ተልዕኮን ማስፈጸም” የሚሉ ናቸው።

የሚፈልጉትን ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ መመዘኛቸው/መስፈርታቸውና የትኩረት አቅጣጫዎቻቸውም የሚከተሉት ናቸው።

  • ባህር ማዶ ተሻግሮ ወይም ባህር አሳብሮ (አቋርጦ) ወታደራዊ ኀይልን ማስፋፋት፤ (overseas military expansion)

-ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ማሳደር፤ (maintain economic influence)

-የአዲሱ ዓለም ሥርዐት (አመራር) ጥብቅና/ ትውውቅ ወይም የአዲሱ ዓለም የኀይል አሰላለፍ ትውውቅ /አዲስ የአገር ካርታ እስከ መቀየር መጓዝ፤ (advocacy of a new world order)

-ከአዲሱ ዓለም የኀይል አሰላለፍ ጋር የተያያዘ የመረጃና ቴክኖሎጂ ጦርነት ማካሄድ፤ (Information and technology warfare)

-የተጠናከረ መረጃና ደኅንነት ዘመቻዎች ማካሄድ (Intelligence operations)
“ኢንተሊጀንስ ኦፕሬሽንስ” ማለት:- መንግሥታት ፣ ወታደራዊ ቡድኖች ፣ የንግድ ተቋማት እና ሌሎች ድርጅቶች የተቀናቃኞቻቸውን/ ተፎካካሪዎቻቸውን ፍላጎት፣ ዓላማ፣ ግብ፣ ሁለንተናዊ አቅም፣ ችሎታና ብቃት ለማወቅ ስልታዊ በሆነ መንገድ መረጃን የሚሰበስቡበት እና የሚገመግሙበት ሂደት ማለት ነው። (እዚህ ላይ ጅቡቲ የተቀመጡት ኀይሎች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉና ምን እያደረጉ እንዳሉ መገመት አይከብድም)

_አዋጭ የሆነ ጂኦስትራቴጂያዊ አቀማመጥን መምረጥ፤ (geostrategic position)

-የዓለም አቀፍ የባህር ጉዞ ንግድ መተላለፊያን መምረጥ ወይም ማተኮር (corridor for International shipping)፤

-የባህር ንግድ ደኅንነት /ፀጥታን መከታተል፤ (maritime trade security)

-የውጭ ወታደራዊ ኀይልን ለማስተናገድ የተዘጋጀ አገርን መምረጥ፤ (willingness to host foreign militaries)

-ቀጣናዊ አደጋዎችን ለይቶ/ ነቅሶ ማውጣት ወይም ሆን ብሎ መፍጠር፤ (regional threats)፤
ለአብነትም፦ የባህር ውንብድና (sea piracy)፣ ቀጣናዊ የአማጺ ኀይል አደጋዎች (regional militant threats)፣ የእርስ በርስ ጦርነት (civil wars) ፣ አሸባሪነት (terrorism) ፣ አክራሪነት ወይም ወግ አጥባቂነት (fanaticism)፣ የሃይማኖትና ፖለቲካ ጽንፈኝነት (extrmicism)፣ ፖለቲካዊ ቁርቁስ/ ሽኩቻ (political fragility)፣ ንቅዘት/ሙስና (corruption)፣ የምጣኔ ሀብት ግሽበት (inflation)፣ ድህነት (poverty) ያሉባቸውንና በስፋት የሚታዩባቸውን አገሮችና ቀጣናዎች መለየት።

በዚህም መሠረት፦ እነዚህ መመዘኛዎች/መስፈርቶችና የትኩረት አቅጣጫዎች በቀዳሚነት ተግባራዊ የሆኑበት ቀጣና የትኛው የአፍሪካ አኅጉር ክፍል እንደሆነ መገመት አዳጋች አይሆንም።

ልዕለ-ኀያሏ አሜሪካንን ጨምሮ የዘመኑ ኀያላን የአውሮፓና እስያ አገሮች፤ በነዳጅ ዘይት ሀብት የበለጸጉ የዐረቡ ዓለምና በምጣኔ ሀብትና ወታደራዊ አቅም እከፍ ከፍ ያሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ዘመነኛ ተገዳዳሪ አገሮች፤ የግልና የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት የሚሻኮቱባትና የሚሯሯጡባት፤ በርካታ የፍጥጫ ዓይኖቻቸውን ክፉኛ ያሳረፉባትና የባህር በሯን (ወደቦቿን ጨምሮ) እና አስተዳደሯን ጭምር የተቀራመቱባትና ሊቀራመቷት ያኮበኮቡባት፣ እርሷን ተቀራምተው ሌሎች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ስትራቴጂካዊ አገሮች ላይ ጫና ለማሳደር የመረጧት ሚጢጢዬ ግን ተመራጭ አገር፤ በቀይ ባህር መግቢያና መውጫነቷ የምትታወቀው፤ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የምትገኘው፤ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ፤ ስትራቴጂካዊቷ ትንሿ አገር፤ ጂቡቲ ነች።

በጅቡቲ ሽፋን ደግሞ እንድትከበብ የተፈለገው አገር ኢትዮጵያ ነች። ግን ለምን ኢትዮጵያን ለመክበብ ፈለጉ? ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አንድ ማሳያ ልንገራችሁ።

ነገሩ እንዲህ ነው። አውሮፓውያን “ያልተነካውን፣ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገውን፣ ያልሰለጠነውንና ርካሽ ጉልበት (የሰው ኀይል) ያለውን አፍሪካ አኅጉር በሦስት ዋና ዋና መንገዶች መቆጣጠር!” የሚል ስትራቴጂዎች፣ ስልቶችና ዘዴዎችን እንደ ጎርጎሮሳውያን ቀመር ከ1884 እስከ 1914 ድረስ ባሉ አመታት ውስጥ ቀየሱ።

ሦስቱ ዋና ዋና የመቆጣጠሪያ መንገዶችም:- በአውሮፓዊ አገር በሞግዚትነት የሚተዳደሩ አገሮችን መፍጠር/ማመቻቸት (protectorates)። ሙሉ በሙሉ በቅኝ ግዛት ሥር ማድረግ (colonies)። ነጻ የንግድ ቀጣና መፍጠር (free-trade areas) የሚሉ ነበሩ።

ይህ አፍሪካን ወይም የአፍሪካ አገሮች የመሰነጣጠቅ፣ የመከፋፈል፣ የመቀራመት፣ የመቆጣጠርና ተቆጣጥሮ እንዳሻው እየተጫኑና እየጨቆኑ በዘመናዊ ባርነት የማስተዳደር ስትራቴጂም “የአፍሪካ አገሮች ቅርምት፣ ሽሚያና ስንጠቃ” (The scramble for Africa) ተሰኘ።
ማሳያ መጥቀስ ካስፈለገ ደግሞ፤ ከጦረኛውና አገራትን ለመቀራመት ከተራሯሯጠው ፈረንሳዊው ጦረኛ ናፖሊዮን ጦርነቶች በርካታ አመታት በኋላ፤ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት እንዲረዳቸው ያዘጋጁትን የመማማያና የመዋዋያ ኮንፈረንስ (ጉባኤ) በተለምዶ “የበርሊን ኮንፈረንስ” የሚሰኘውን መጥቀስ እንችላለን።

እናም አውሮፓውያን ጉዳት ሳይደርስባቸው ወይም ሳይጎዱ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት የሚያስችል ዓለም-አቀፍ አቅጣጫዎችን (International Guidelines) ያስቀመጠ ጉባኤ፤ እንደ ጎርጎሮሳውያን ቀመር ከኖቬምበር 15 ቀን 1884 እስከ ፌብሩዋሪ 26 ቀን 1885 በጀርመን-በርሊን ተካሄደ። ጉባኤውም “የበርሊን ኮንፈረንስ” ተባለ።

በበርሊን በተካሄደው ኮንፈረንስም፦ አሜሪካንን ጨምሮ ኦስትሮ-ሀንጋሪ (Austria-Hungary)፣ ቤልጅየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስ (ሆላንድ)፣ ኦቶማን ኢምፓየር ቱርክ፣ ፖርቹጋል፣ ራሽያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን-ኖርዌይ (ተጣምረው) እና እንግሊዝ ተሳታፊ ሆኑ።

በበርሊን ኮንፈረንስ መነሻም የዚያን ዘመነ ኀያል የነበረችው ፈረንሳይ፤ በጎርጎሮሳውያኑ ቀመር 1896 “የፈረንሳይ ሶማሌላንድ” ወይም “በአፋሮችና ኢሳዎች ምድር የፈረንሳይ ግዛት” ( Territory of the Afars and Issas) እያለች ትጠራት የነበረችውን የአሁኗን ጅቡቲ በቅኝ ግዛቷ መዳፍ ሥር አስገባቻት። ይህ የቅኝ ግዛት ቅርምት ጅቡቲ ነጻነቷን እስካገኘችበት ጁን 27 ቀን 1977 (ሰኔ 20 ቀን 1969 ዓመተ-ምህረት) ድረስ ቀጠለ።

ምንም እንኳ ጅቡቲ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሥር ብትወድቅም፤ ኢትዮጵያ ግን ቀድማ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓመተ-ምህረት (በአውሮፓውያኑ ቀመር ማርች 2 ቀን 1896) በአድዋ አቅራቢያ ባሉ ሰንሰለታማ፣ ክብና ጉልላታማ ተራራሮች (Mountains in conferences)፤ ጣልያን አደራጅታ፤ እጅጉን አሰልጥናና ዘመናዊ ጦር መሣሪያዎች አስታጥቃ ያመጣችውን ዘመናዊ የአውሮፓ ሠራዊት፤ በአድዋ ጦርነት አሸንፋ፤ የበርሊን ኮንፈረንስ እሳቦትን በአድዋ ተራሮች ኮንፈረንስ እንደ እምቧይ ካብ ንዳ ድማሚት እንደ ፈረካከሰው ድንጋይ በመበታተኗ በአውሮፓ አገሮች መንግሥታት ጥርስ ተነከሰባት። ቂም ተቋጠረባት።
በወቅቱም የአድዋ ጦርነት ተሸናፊዋ አገር ጣልያን ወዳጆች የሆኑት “የበርሊን ኮንፈረንስ” ተሳታፊ አገሮችና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች መንግሥታት በዋናነት ይህንን ጥያቄ ጠየቁ።

ጥያቄውም “ኢትዮጵያውያን ለምን በአድዋ ጦርነት ስኬታማ ሆኑ?” (Why were the Ethiopians successful at the Battle of Adwa?) የሚል ነበር።

ስለዚህ “ኢትዮጵያ የበርሊን ኮንፈረንስ ተግባራዊ እንዳይሆንና በዋናነት ‘የአፍሪካ አገሮች ቅርምት፣ ሽሚያና ስንጠቃ’ (The scramble for Africa) ስትራቴጂ እንዳይሳካ፤ ለሌሎች አፍሪካውያን፣ እስያውያን፣ ላቲን አሜሪካውያን መንገዱን አሳይታብናለች! በባርነት ውስጥ ለነበሩ ጥቁር ሕዝቦች (ለአሜሪካ ጥቁሮች ጭምር) የነጻነት መንገድን አመላክታለች! ከአሁኑ የአውሮፓውያን የጉሮሮ አጥንት ሆናለችና ይቺ ባቄላ ካደረች ስለማትቆረጠም፤ ኢትዮጵያ በየትኛውም መንገድ ወደ ፊት እንዳትራመድ እንቅፋት መፍጠር ያስፈልግል!” የሚል አቋም ያዙ። ጎበዝ! እውነትን ይዞ ማሸነፍና ድልን መጨበጥም ጠላት ያበዛል?!

ይህ ጥላቻቸው ለዘመናት ቀጥሎ በተመሳሳይ ጅቡቲ ነጻ በወጣች ከአንድ ወር በኋላ፤ ሐምሌ 5 ቀን 1969 ዓመተ-ምህረት የሶማሌያ ሪፑብሊክ አምባገነን ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ፤ ከኢትዮጵያ ሠራዊት የበለጠ መሣሪያዎችን የታጠቀው ጦሩን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ወደ መኻል አገር እንዲገባ ትእዛዝ በመስጠት ወረራ ፈጸመ።

የዚህን ጊዜ የበርሊን ኮንፈረንስ የአፍሪካ ቅርምት (the scramble for Africa) አንዷ ጋሻ ጃግሬ ጣልያን አበልጅ የነበረችው ፈረንሳይ በበኩሏ፤ ነጻ የወጣችው ጅቡቲን አመራሮች ጠምዝዛ፤ ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብን እንዳትጠቀም በማድረግ ጁቡቲ ከወራሪው የሶማሌያ ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ጎን እንድትሰለፍ አደረገቻት። ጅቡቲም በታሪክ አሳፋሪ ድርጊት ፈጸመች። በዋናነት በፀረ-ኢትዮጵያ አቋሟ የምትታወቀው ግብጽ ቆማ አጨበጨበች።

ነገር ግን የቃል-ኪደን አገር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የሶማሌያ ሪፑብሊክ ወረራን ቀልብሳ የሶማሌያ ጦርን ከግዛቷ በማስወጣት ወራሪዋ ሶማሌያን ከባድ የሽንፈት ካባ አልብሳ አዋረደቻት። በወቅቱ የሶማሌያ ሪፑብሊክ ወዳጅ የሆኑ የገንዘብና ጦር መሣሪያዎች ድጋፍ ያደረጉ እንደ ግብጽ ያሉ አገሮችንና ግልጽ ድጋፍ የሰጡ ሶማሌያ ሪፑብሊክ አባል የሆነችበት እንደ ዐረብ ሊግ ያሉ ቀጣናዊ ግዙፍ ኅብረቶችም ከሶማሌያ ጋር የሀፍረት ማቅ ለበሱ።

እናም! ፀረ-ኢትዮጵያ መንግሥታትና ኀይሎች ኢትዮጵያን በሚችሏቸው መንገዶችና ዘዴዎች በማዳከም መጀመሪያ ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ቀጣና ለማስወጣት ጥረት አደረጉ። ለዘመናት እንቅልፈው አጥተው የክፋትና ጥፋት ስትራቴጂዎችን፣ ተልእኮዎችንና ስልቶችን በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ አደረጉ። ተሳካላቸውም።

አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር እንዳትመለስ በድጋሚ እንቅልፍ አጥተው እየሠሩ ይገኛሉ። የሚያስዝነው ደግሞ በኢትዮጵያ ሕልውናና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ቁልፍ ድርሻ ባለው የጅቡቲ ወደብ ላይም እኩይ ዕይታዎቻቸውን የማተኮራቸው ጉዳይ ነው። በዘመነኛ ቃላት አጠቃቀም ኢትዮጵያ ምን ያህል ባንናለች?

ጅቡቲ ገቢ ለማግኘት ብላ፤ ራሷ ባመጣችው መዘዝና በውጭ ኀይሎች ተጽእኖ፤ የራሷን ግዛት (ባህር በሯን) በምጣኔ ሀብትና በወታደራዊ አቅማቸው በፈረጠሙ አገሮች ወታደራዊ ጦር ሰፈሮች ማስወረሯንና በራሷ ባህር በር እንደ “ዶራሌህ” ባሉ ወደቦቿ ጭምር ተፈትሻና ፈቃድ ጠይቃ እስከ መግባት መድረሷን ምን ያህል ተገንዝባዋለች?

የቀድሞ የጅቡቲ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይን ጨምሮ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጃፓን፣ ጣልያን እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቻይና ለምን በጅቡቲ ወታደራዊ ጦር ሰፈር መሠረቱ? ልዕለ ኀያሏ ራሽያ፣ በምድራችን ከቻይና ቀጥላ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ የሆነችው ሕንድና ፀረ-ኢትዮጵያ አቋሟ እጅግ እየገነገነ የመጣውና ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ እንቅልፋ አጥታ እየሠራች ያለችው ግብጽ፣ ቱርክና ሳዑዲ አረቢያ ወደ ጅቡቲ አምርተው ወታደራዊ ጦር ሰፈር ይመሠርታሉ ተብሎ መታሰቡስ እንዴት ይታያል?

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories