የአውሮፓ ኅብረት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተገናኘ ተወካዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ሊልክ ነው

8 hours ago95

 

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 9፣ 2014 ― የአውሮፓ ኅብረት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተገናኘ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኮሚሽነሯ ዩታ ኡርፒላይነን እና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበርን ወደ ኢትዮጵያ ሊልክ መሆኑን አሳውቋል፡፡

 

ዩታ ኡርፒላይነን 

 

የተወካዮቹ የኢትዮጵያ ጉዞ አላማ የአውሮፓ ኅብረት ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ ያለውን ግልጽ አቋም ለማንጸባረቅ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

 

ኔት ዌበር

 

ከሁለት ሳምንታት በፊት የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሰብስበው ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲበጅለት የጠየቁ ሲሆን፣ ነገር ግን በጦርነቱ አካባቢ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል የማያሳይ ከሆነ ኮሚሽኑ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ውሳኔ ማሳለፋቸውም ይታወሳል፡፡  

ፓርላማው ዕቀባው ይመለከታቸዋል ያላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት እና ሕወሓትን ጨምሮ ግጭቱ እንዲራዘም እና እንዲባባስ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን አካላት ነው፡፡

 

 

ይህንኑ የኅብረቱ የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ትላንት ምሽት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡ ቦሬል በመግለጫቸው የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊደፍን መሆኑን አስታውሰው፣ ጉዳዩ አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 

 

ትግራይ በአንድ ዓመት ጊዜ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተገናኘ በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ ማለፏን ያመለከተቱት የአውሮፓ ኅብረት የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ክልሉ የሰብአዊ አቅርቦት መተላለፊያ ገደብ መኖሩን ገልጸው፣ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ተገንዝቦ ምላሽ ለመስጠት ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ሪፖርት እየጠበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

 

 

የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ባለው ውጊያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት፣ የሰብአዊነት እና የስደተኞች የህግ ጥሰቶችን በተመለከተ ሲያከናውኑት የነበረውን የመስክ ምርመራ አጠናቀው የመጨረሻውን ሪፖርት በመጪው ጥቅምት 22፣ 2014 ይፋ እንደሚያደርጉ በጳጉሜ ወር 2013 ማሳወቃቸው አይዘነጋም፡፡  

ሁለቱ አካላት ያደረጉት ምርመራ የተከናወነባቸው ከተሞች መቐለ፣ ውቅሮ፣ ሳምረ፣ አላማጣ፣ ቦራ፣ ማይጨው፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ ሁመራ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ጆሴፍ ቦሬል የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ችግሮችን እንዲፈቱ በአፍሪካ ኅብረት ለተሰየሙት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories