5.3) ጉልህ ጉዳትን ያለማድረስ ግዴታ (No Significant Harm Principle)

በመሰረቱ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ወንዞች ላይ ሁለት መሰረታዊ መርሆዎች እያደጉና የአለም አቀፍ ልማዳዊ ሕግ መገለጫ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በአንድ በኩል ፍትሀዊና ምክንያታዊ የመጠቀም መብት በሌላ በኩል ደግሞ መሰረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለመጓጓዣነት የማያገለግሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለማስተዳደር ባወጣው አለምአቀፍ ስምምነት(1997) በአንቀጽ 5 እና 7 ላይ እንደቅደም ተከተላቸው ተደንግገዋል፡፡ ዝቅ ብለን እንደምናየው እነዚህ መርሆዎች የአለምአቀፍ ልማዳዊ ሕግ መገለጫ(Declaratory of International Customary Law) ተብለው የሚወሰዱ መሆናቸውን ልብ ይበሉ፡፡ ግብፅ የናይል ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ የሚለው መርህን እያነሳች ትከራከራለች፡፡ ሆኖም ግብፅ የናይል ወንዝን ኢ-ምክንያታዊ በሆነ መንገድና ከሚገባት በላይ ጥቅም ላይ በማዋል በራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እያደረሰች ነው፤የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ሚዛናዊና ምክንያታዊ የተጠቃሚነት መብታቸውን አግታለች በማለት ኢትዮጵያም መከራከር ትችላለች፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 10(2) ላይ እንደተደነገገው ማንኛውም አይነት የውሀ አጠቃቀም በአንድ በኩል ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን ተግባራዊ በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ መሆን አለበት፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬን ስመለስ በአለም አቀፍ የውኃ መሄጃ ስምምነት(International Watercourse Convention)አንቀጽ 7 ላይ እንደሰፈረው ማንኛውም ሀገር በግዛቷ ላይ የሚገኘውን ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የታችኞች ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅምና ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ መጠቀም አትችልም፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የአባይ ወንዝ በግዛቷ ስር ቢገኝም ወንዙን ሙሉ በሙሉ መዝጋትና ወደ ታሕታይ ሀገራት የሚያደርገውን ፍሰት ማስቆም ግን አትችልም፤ምክንያቱም ይህ ድርጊት የግብፅን ጉሮሮ የሚዘጋ በመሆኑ አደገኛ ጉዳት(significant harm)ያስከትላል፡፡ ኢትዮጵያ ሆነ ግብፅ የስምምነቱ አባል ሀገራት አይደሉም፡፡ ይሁንና መሰረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ በሀገራት ልምድ (State practice)ቅቡልነት ያገኘ፣ አለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት(International Court of Justice) ትርጉም የሰጠበትና አለም አቀፍ የልማድ ሕግ ደረጃን ያገኘ በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህን አለም አቀፍ ግዴታ ታከብራለች፡፡ ለምሳሌ በ1849 “የኮርፉ ቻነል” በማለት በሚታወቀው ጉዳይ ላይ አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ማንኛውም ሀገር በግዛቷ ስር እያወቀች የሌሎች ሀገራት መብትን የሚጎዳ ተግባር እንዲፈፀም ማድረግ ወይም ማስደረግ አትችልም በማለት ግልጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ይህ አለምአቀፍ መርሆ ወደ አባይ ግድብ ስናመጣው በግብጽ ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይቅርና የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በጎርፍና በደለል እንዳይጎዱ የሚያግዛቸውና ሌሎች የጋራ ጥቅሞችን እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን የሚነገርለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በጋራ ባደራጁዋቸው የቴክኒክ ባለሙያዎችም ቢሆን የአባይ ግድብ በግርጌ ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚያደርሰው መሰረታዊ ጉዳት ስለመኖሩ ያቀረቡት ግኝት የለም፡፡ በመሰረቱ ግን የላይኞች ተፋሰስ ሀገራት በግዛታቸው ስር የሚገኝ ውኃን ሲጠቀሙ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው “ተገቢውን እርምጃ” እንዲወስዱ ሊገደዱ ይችሉ ይሆናል እንጂ ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስ ብለው እጃቸውንና እግራቸውን አጣጥፈው ቁጭ እንዲሉ አይገደዱም፡፡ ህገ ወጥ ጉዳት እንዳያደርሱ መጠንቀቅ አለባቸው ማለት ፈፅመው ጉዳት ማድረስ የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያም ግብጽን “በእጅጉ ሊጎዳ” በሚችል መልኩ የአባይ ውኃን መጠቀም አትችልም ማለት ፍትሀዊ ተጠቃሚነቷን ትነፈጋለች ማለት አይደለም፤ተጠቃሚነቷ ፍትሀዊ እስከሆነ ድረስ በግብጽ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂ ልትሆን አትችልም፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የአባይ ግድብ ስትሰራ የግብጽ የቀደመ የውኃ ተጠቃሚነት ሊቀንስ ይችላል፡፡ ዋና መሰረታዊ ጉዳይም ግብጽ አስቀድማ የተቆጣጠረችው የናይል ውሀ ለሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ልታካፍል ይገባል የሚል በመሆኑ ከዚህ በፊት ስትጠቀመው የነበረውን የውኃ ኮታ ልክ ላታገኝ ትችላለች፡፡ ስለሆነም ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት ጉልህ ጉዳት ካለማድረስ ግዴታ ቅድሚያ ይሰጧል፡፡

6) የኢትዮጵያ አቋምና አለም አቀፍ የሕግ ተቀባይነቱ

6.1) ስምምነቶቹና ኢትዮጵያ ምንና ምን ናቸው ?

የናይል ትልቁ ድርሻ አመንጪ ኢትዮጵያ ነች፤የናይል ወንዝ የውኃ ይዘት ጥቁር አባይ የሚልከው ውኃ ካልታከለበት ምንም ነው፡፡ ይሁንና ግብፅ የናይል ወንዝ ውኃን አከፋፋይና ከልካይ አድራጋ ራሷን በመሾም “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሉ ውሀውን በበርጭቆ እንኳን ሳታስቀር ጥርግርግ አድርጋ መውሰድ ትፈልጋለች፡፡ በናይል ወንዝ ላይ “አዲስ ስምምነት” እንዲሮር አትፈልግም፤እንዲኖር ከተፈለገም በቅኝ ገዢዎች የተከናወኑ ስምምነቶችና ውሎች ሙሉ እውቅና ተሰጥቶዋቸው የአዲሱ ስምምነት አካል ሆኖው መካተት አለባቸው በማለት እርባና ቢሶችና መርህ ላይ መሰረት ያላደረጉ ክርክሮች ታነሳለች

በመሰረቱ ግብጽ የናይል ወንዝ አለቃ፣ አከፋፋይና ከልካይ አድርጎ የሾማት አካል እንደሌለ፤ናይል የተፋሰሱ የጋራ ኃብት እንጂ የግብፅ “የግል ንብረት” እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የግብፅ አቋም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምን በእጅጉ የሚቃረን በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ፈፅሞ የማይቀበለው ከመሆኑ በላይ አለምአቀፍ ማህበረሰቡም ለናይል ተፋሰስ ሀገራት ሰላምና ደህንነት ሲል ሊኮንነው ይገባል፡፡ የአፍሪካ ህብረት የስምምነት ሰነድ ከአንቀጽ 3 እና 4 ላይ መገንዘብ እንደሚቻለውም የህብረቱ መሰረታዊ አላማዎችና መርሆዎች የአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የአባል ሀገራት አንድነትና ትብብርን ማስጠበቅ ከመሆኑ ባሻገር ሀገራት በልአላዊ ግዛታቸው የሚገኝን ተፈጥአዊ ኃብት በመጠቀም የህዝቦች ኢኮኖሚያዊ እድገትን የማረጋገጥ ግዴታንና መብትን እውቅና የሚሰጡ ጭምር ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 1 እና 2 ላይም በተመሳሳይ መልኩ የድርጅቱ መሰረታዊ አላማዎችና መርሆዎች የተደነገጉ ሲሆን በአባል ሀገራት መካከል በሁሉም መስኮች እኩልነትን ማረጋገጥ፤እንዲሁም አለምአቀፍ ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚሁ መሰረት ሀገራት የጋራ ፀጋቸውንና ሀብታቸውን በጋራና በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፡፡ ግብፅ የናይል ወንዝ ብቸኛ ባለቤት ነኝ በማለት የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት እንድትበጠብጥ ሆነ ፍትሀዊ የተፈጥሮ ኃብት ክፍፍልን የሚቃረን ህገ ወጥ ተግባር እንድትሰራ ፈቃድ ማግኘት የለባትም፡፡ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ታሪካዊ፤ተፈጥሮአዊና የቀደምትነት የባለቤትነት መብት አለኝ በማለት የምትከራከረው በጉዳዩ ላይ መብት ከሌላቸው ቅኝ ገዢዎች ጋር የተዋዋለቻቸውን ያረጁ እና ከዘመኑ ጋር የማይሄዱ ስምምነቶችንና ውሎችን እየመዘዘች ነው፡፡ ይህ የግብጽ የተለመደው አሰልቺ ክርክር በአለምአቀፍ ልማዳዊ ሕግ የማይታወቅ ነው፡፡ የግብፅ ብቸኛ አማራጭ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የመከባበርና የመተባበር መስመርን መከተል መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ የተፈፀሙት ስምምነቶችና ውሎች የላይኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገራትን ሙሉ በሙሉ ያገለሉና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምን ታሳቢ ያላደረጉ በመሆናቸው አልቀበላቸውም በማለት በግልጽ ስትቃወም ቆይታለች፡፡ ታንዛንያና ኬንያም እነዚህ ስምምነቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ከቅኝ ገዥ ሀገራት ነፃነታቸውን በተጎናፀፉበት ማግስት ጀምሮው በመሪዎቻቸው በኩል አሳውጀዋል፡፡ የታንዛንያው መሪ ጁሊየስ ኑረሬ ማንኛውም አይነት የቅኝ ገዢዎች ስምምነቶች በታንዛንያ ላይ ተፈፃሚነት እንደሌለው በግልጽ አውጇል፡፡ ”ኒይረሬ ቀኖና” እየተባለም ይታወቃል፡፡ ይሁንና በስምምነቶቹ ላይ አስተያየታቸው ሳይሰጡ እስከአሁን ዝምታን የመረጡ የላዕላይ ተፋስስ ሀገራትም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሩዋንዳና ኡጋንዳ፡፡ እነዚህ ሀገራት በናይል ወንዝ ላይ ጠንካራ አቋም ማራመድ ያልቻሉበት ምክንያት ከናይል ወንዝ በላይ ሌሎች ጂኦግራፊካዊና ፖለቲካዊ ብልጫ ባላቸው የተፈጥሮ ኃብት የተከበቡ ከመሆኑ በላይ ግዙፍ ፕሮጀክት ለመስራት የሚያስችል አቅምም አላሳደጉም፡፡

ሲጠቃለል በካይሮና በሎንደን መካከል ወይም በካይሮና በካርቱም መካከል የተከናወኑ ውሎች ለኢትዮጵያ ምንም ናቸው፤አዲስ አበባ ያልተሳተፈችበት ማንኛውም አይነት ስምምነት ከአንድ ሺህ በላይም ቢደረደረርና የግብጽ ቤተመንግስት ቢሞላው በኢትዮጵያ ላይ ውጤት የለውም፡፡ በቬና ቃልኪዳን የስምምነት ሕግ አንቀጽ 11 እና 34 ላይ እንደተመለከተው በሀገራት መካከል የሚከናወን ማንኛውም አይነት ስምምነት ፍላጎቷ ባልገለፀች በሌላ ሶስተኛ ሀገር ላይ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ በተለይም የስምምነቱ አንቀጽ 34 ድንጋጌ ስንመለከተው በአንድ ውል ላይ ነፃ ፍላጎቷን ካልገለፀች የምታገኘው መብት ሆነ የሚጣልባት ግዴታ አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ ከላይ የተገለጹት ስምምነቶች አታውቃቸውም፤የስምምነቱ አካልም አይደለችም፡፡ ስለሆነም ስምምነቶቹና ውሎቹ በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡

6.2) ፍጹማዊ የግዛት ሉአላዊነት ኃልዮት፤

በመርህ ደረጃ አንድ ሀገር በግዛት ክልሏ ላይ ፍፁም የሆነ የሉአላዊነት ስልጣን አላት፡፡ አባይ የግዛትና የሉአላዊነት መገለጫ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፖለቲካዊ ልእልና አንፃርም መታየት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በግዛቷ ስር የሚገኝ ማንኛውም አይነት የተፈጥሮ ኃብትን የማንም ፈቃድ ሳትሻ የመጠቀም መብት አላት፡፡ በአንድ ወቅት አሜሪካ በግዛቷ ስር የሚገኘውን “ሪያ ግራንዲ” የተባለውን ወንዝ ሚክሲኮን በሚጎዳ መልኩ ተጠቅማለች የሚል ክስ ሲቀርብባት ሉአላዊነቴን የማስከበር ስራ ነው የሰራሁኝ እንጂ የጣስኩት አንድም አለም አቀፍ ሕግ የለም የሚል መከራከሪያ ነጥብ አቅርባ ነበር፡፡ ይህ ከፍጹማዊ የግዛት ሉአላዊነት ኃልዮት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሆኖ “የሀርሞን ቀኖና” የሚል ስያሜ አግኝቶ ነበር፡፡ የላይኞች ተፋሰስ ሀገራት በግዛታቸው ስር የሚገኝን ወንዝ ሲጠቀሙ የታችኞች ተፋሰስ ሀገራትን ታሳቢ የማድረግ ግዴታ እንደሌለባቸው የሚያትት ነው፡፡ ሆኖም ይህ ኃልዮት እንደ የአካባቢ ጥበቃና ወንዞች የመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከአለም አቀፍ ሕግ አንጻር ተቀባይነት የሌለውና ከዘመኑ ጋር ሊሄድ የማይችል እምነት ነው፡፡ ሀገራት የተገደበ ግዛታዊ ሉአላዊነትን ቅድሚያ የሚሰጡበት ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ በአሁን ጊዜ ተቀባይነቱን እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያም ይህን “የሀርሞን እምነት” የመረጠችው አይመስልም፤ኢትዮጵያ ያስቀደመችው የድርድርና የመተባበር መርሆ በመሆኑ የተገደበ የግዛት ሉአላዊነትን የምትደግፍ ነች ማለት ይቻላል፡፡ አለም አቀፍ የልማድ ሕግ ደረጃ ካገኙ የውሀ ህጎች አንጻር ሲታይም ትክክለኛ አቋም ይህ ነው፡፡ እስካሁን በስራ ላይ የሚገኘው የኢ.ፌ.ድ.ሪ.መንግስት የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራተጂ ላይ እንደተገለፀው በግሎባላይዜሽን ማእቀፍ ውስጥ አገራዊ ጥቅማችንና ደህንነታችን ለማስጠበቅ የሚያስችል የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲ መቅረፅ ያለብን በድንበራችን ታጥረን ሳይሆን አለም አቀፋዊውን ትስስር ጠበቅ አድርገን ይዘንና አቅፈን የምንሰራበት አቅጣጫ የሚያሳየን ፖሊሲ መሆን እንዳለበት ከዚያም አልፎም ጠቅሞ በመጠቀም፣ ሰጥቶ በመቀበል፣ በድርድርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ እንጂ በተናጠል ጥቅምን ለማስጠበቅ በመሞከር የሚፈፀም ፖሊሲ መሆን የለበትም፡፡ በዚሁ መሰረትም የአባይ ወንዝ በግዛታችን ስር ስለሚገኝ ብቻ ከአለም ማህበረሰቡ ተነጥለን በወንዞቻችን ስር መሽገን፣ የድርድር በሮቻችንን ዘግተንና አለም አቀፋዊ ትስስርን ችላ ብለን የምናሳካው ሀገራዊ ጥቅም አይኖርም፡፡

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories