አሜሪካ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የውጭ ፖሊሲዋን በቀጥታ ጣልቃ ገብነት ማራመድ እንደማያዋጣ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ተገነዘበች። ይህን ተከትሎም ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አቋቁማ፣ በህዝብ ድምፅ የተሰጠን ሥልጣን እስከ መቀልበስ በዘለቀ የመንግሥት ግልበጣ ሀገራትን በተፅእኖ ሥር የማድረግ ሥልት አስፈላጊ ነው አሉ። ለዚህም በሁለተኛው የአለም ጦርነት የስትራቴጂክ አገልግሎት ተብሎ የሚጠራ ቢሮዋን 1947 ላይ በሲ.አይ.ኤ እንዲተካ አደረገች።
ከጊዜ በኋላ በተለይም በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ የአሜሪካ NGOs ጣልቃ ለመግባት ከሲአይኤ የገንዘብ ድጋፍ እያገኙ እንደነበር ተጋለጠ። በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መንግስታትን ከስልጣን ማውረድ፣ አመጽ መቀስቀስና ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎችን በመደገፍ አጀንዳቸውን መደገፍ የተጋለጡ ሴራዎች ፈርጆች ነበሩ።
ይህን ተከትሎ CIA የውጭ አጀንዳውን ማስቀጠል እንዲችል ማሻሻያ ማድረግ ነበረበት። በዚህም ከአሜሪካው አለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ USAID በሚበጀት ገንዘብ አንድ የመንግስት ለትርፍ ያልተቋቋመ ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም ተወሰነ። 1983 ላይ አዲሱ ድርጅት ተፈጠረና አሜሪካ ካዘዘችው ውጭ በራሴ መርህ እጓዛለሁ ለሚሉ መንግስታት ማፈራረሻ የሚሆን አዲስ ድርጅት እውን አደረጉ። ስሙንም “ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ NED ሲሉ ጠሩት። የእንግሊዝኛ ስያሜው ደግሞ National Endowment For Democracy.
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ሮናልድ ሬገን ዘመነ ሥልጣን የሶቭየትን ተፅዕኖ ለመቋቋም የተመሠረተው ይኸው National Endowment for Democracy NED ያሉት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በአሜሪካ መንግሥት በሚመደብ በጀት የሚንቀሳቀስ ነው። የዚህን ድርጅት አጀንዳ ወደ ተፈለጉ አገራት ለማስገባት በጀት ተመደቦላቸው አስፈፃሚ ከሆኑ ድርጅቶች ውስጥም Institute for International Affair – NDI አሜሪካ ከምትከተለው ዴሞክራሲን በማስፈን ሽፋን አንዱ ጣልቃ መግቢያ ተቋም ነው፡፡ በተመሳሳይ ረድፍም International Republican Institute IRR፣ ዓለም አቀፍ የምርጫ ሥርዓት ፋውንዴሽን International Foundation for Electoral System IFES፣ International Research and Exchange Board IREX፣ ፍሪደም ሐውስ Freedom House የተባሉት ተጠቃሽ ናቸው። የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ተቋም Institute for International Affair – NDI 97% በጀቱ በ USAID በኩል ከአሜሪካ መንግሥት ይቀርብለታል፡፡
የመግቢያ ፈረሶቻቸው
የመንግሥት ለውጥ እስከማድረግ የሚዘልቀውን ጣልቃ ገብነት በሥራ ላይ ለማዋል፣ አስፈፃሚዎቹ NGOs ወደ ታላሚ ሀገራት የሚሰርጉበት ሥልት ይመቻቻል። ቀዳሚዎቹ ደግሞ ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲን ማስፈን የሚሉ ሰበቦች ነው። በዚህ ጭንብል ተጀቡነው ሀገር ውስጥ ካሉ የሥልጣን ጥም ያንገበገባቸው ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር ጥምረት ይፈጥራሉ። በመቀጠልም በሀገር ውስጥ ያሉ ቡድኖችን ፍላጎት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተጋባት ማጉላት፤ በሀገር ውስጥ የተቃውሞ አጀንዳዎችን ፈጥረው መልሰው ያስተጋባሉ።
መንግሥታዊ ተቋማትና ሚዲያዎችን ተዓማኒነት ማሳጣት ዋነኛው አካሄዳቸው ነው። ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች በነፃ ፕሬስ ሽፋን አላማቸውን የሚያራምዱ መፅሄቶችና ጋዜጦችን በማቋቋም እና ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ በማቅረብ CIA እንዲወገድ የፈለገውን መንግስት የማጠልሸት ስራ ማሰራት።
ቅንጅትና ተከታታይነት ባለው መልኩ እንደ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድና መሰል ተቋማትን ተዓማኒነት የማሳጣት ዘመቻም ሌላኛው መገለጫቸው ነው፡፡
በተጨማሪም በጥላቻ የሚነዱ ሚዲያዎችን፣ አክቲቪስትና ጋዜጠኞችን እንደ ነፃና ገለልተኛ፣ እንዲሁም እውነትን ዘጋቢ አስመስሎ መሳል፤ እንደ ጤነኛ የመረጃ ምንጭ በማድረግ በዋቢነት እየተጠቀሙ አለማቀፍ ሚዲያዎቻቸው ላይ ዘገባዎች ማቅረብ።
አገራዊ አንድነት ላይ የሚሰሩ ሚዲያዎችን፣ አንቂዎችንና ጋዜጠኞችን ማጣጣልና እድል መንፈግ ሌላኛው ዘዴያቸው ነው። በተመሳሳይም የዲጂታል ኩባንያዎችን አሰራር በመጠምዘዝ ከነሱ በተፃራሪ የሚገኙ የዲጂታል ይዘቶችን ተደራሽነት መገደብ፤ መዝጋት፤ ማስጠንቀቂያ ማብዛት ተጠቃሽ ናቸው። ማህበራትን ማደራጀት፤ ለማስፈፀሚያነት የሚያገለግሉ የጋዜጠኞች ማህበር እና መሰሎችን ማቋቋም እንዲሁ የተግባራቸው አካል ናቸው።
NED በተለያዩ ሀገራት
አሜሪካና አጋሮቿ “ሰብዓዊ መብት ማስከበርና ዴሞክራሲን ማስፋፋት” በሚል ሽፋን በተለይም በምሥራቅ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ አገራት ውስጥ ምርጫን በማስታከክ የመንግሥት ለውጥ እንዲካሄድ ሞክረዋል፤ አድርገዋልም።
በ2004 በዩክሬን በተካሄደው የመንግሥት ግልበጣ አመፅ ብሄራዊ ኢንዶውመንት ለዴሞክራሲ National Endowment for Democracy NED እጅ እንዳለበት በማስረጃዎች ተረጋግጧል። ለየዩክሬይን ብጥብጥ ደግሞ 65 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ፈንድ አድርጓል።
ሃያሏ ቻይና ሳትይቀር ይህ ሴራ ተሞክሮባታል። በዚህም ዢንጂያንግ፣ ቲቤት፣ ታይዋንና ሆንግ ኮንግ በ”ሰብአዊ መብት” ሰበብ እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቻይናን ገፅታ የሚያበላሹ ሪፖርቶችን እንዲያዘጋጁና ለአለማቀፉ ማህቀረሰብ እንዲያደርሱ ሆኗል።
NED በ2018 “ምስራቅ ቱርኪስታን” ተብሎ ከሚጠራው ዚንጂያንግ ጋር ለተያያዙ ፕሮጀክቶች 670,000 ዶላር ሰጥቷል። ከገንዘቡ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወርልድ ኡዩጉር ኮንግረስ ለተባለው ግንባር ነው። NED በዚሁ አመት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲል ለጠሯቸው ቡድኖች 4.75 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል።
በተጨማሪም በስደት የሚገኙና የተገንጣይነት ዝንባሌ ያላቸውን የቻይና አካል ቲቤታዊ ኅትመቶችና የሬዲዮ ፕሮግራሞችን ስፖንሰር አድርጓል፣ ይህም የሰብአዊ መብት ረገጣ እያሉ እንዲመዘግቡና አዳዲስ የመገንጠል አራማጅ ግንባሮችን እንዲያበራክቱ ለማድረግ ሞክሯል። ለዚህ አላማም በ2018 ብቻ 630,000 ዶላር ሰጥቷል።
የሆንግ ኮንግ የዜና ማሰራጫ wenweipo . com ደግሞ NED ከ2014 ወዲህ በሆንግ ኮንግ የሚረጨውን ገንዘብ ጨምሯል” ሲል ነው የዘገበው። ከ1990 እስከ 2018 ውስጥም 1.3 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል። NED ራሱ ባወጣው መረጃ መሠረት ደግሞ ከ2016-2018 ለሆንግኮንግ ንቅናቄዎች 1.16 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል።
ይህ አሳፋሪ ሴራ በገለልተኛ የጥናት ተቋማት የተጋለጠባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ለአብነትም የጀርመኑ ዜና መጽሔት ዴር – ስፒገል በሰኔ 2008 ባወጣው ዘገባው “ወጣት ምሁራንን በማነሳሳት የመንግስት ግልበጣን ያበረታታል” ሲል አስቀምጧል። ጋዜጠኛ ማክስ 2018 ባወጣው ሪፖርቱ ደግሞ “በUSAID እና NED የሚደገፉ NGOs በሌሎች አገራት ምርጫዎች ላይ የሚያሴሩ የጣልቃ ገብነት ማሽኖች” በማለት ነበር የገለፃቸው።
Esleman የዓባይ፡ልጅ