የደህንነት ጥናት አዲሱ ምዕራፍ – ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ


▪️ እስሌማን ዓባይ

የአሜሪካ የስለላ ድርጅት በታህሳስ 2021 ሳዑዲ አረቢያ የባለስቲክ ሚሳኤል በቻይና ድጋፍ መገንባት ላይ መሆኗን በምስል አስደግፎ ማውገዙ የሚታወስ ነው። አሜሪካ ይህን መሰል እንቅስቃሴ መለየት ይቻላት ዘንድ ትልቁን ሚና የተጫወተው Geo-Spatial Intelligence ነው። እዚህ ላይ መጠቆም የምፈልገው ከጥቂት አመታት ወዲህ በዚህ ዘርፍ ቻይና እና ሩሲያ ከአሜሪካ በብዙ ደረጃ የላቀ አቅም መፍጠር መቻላቸውን ነው።(ይህን የራሷ የዋሽንግተን ባለስልጣናት የመሰከሩለትን መረጃ እመለስበታለሁ።)

የጂኦስፓሺያል ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ጠቀሜታው የገዘፈ ሆኗል። በደህንነት እና ስትራቴጂካዊ ጥናቶች መስክ እንዲሁም በብሔራዊ ደህንነት ደረጃ ሽብርተኝነትንና የድንበር ላይ የሚኖሩ ስጋቶችን ለመለየት ጠቀሜታ ወሳኝ ሆኗል።

ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ የካርታ እና ግራፍ ላይ ምስሎች መረጃ ትንተና ነው። የዩኤስ ናሽናል ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ (NGA) “
ምስሎችን፣ የጂኦስፓሻል ዳታዎችንና መረጃን በመጠቀም ትክክለኛ እቅድ ለማቀድ፣ ውሳኔ ለመስጠትናና ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችል እውቀት የሚገኝበት ነው።” ሲል ገልፆታል። ለምሳሌም፦ ከሳተላይቶች፣ ከድሮኖችና ከመሬት ዳሳሽ ቴክኖሎጂዎች የተገኙ መረጃዎች ከካርታዎች እና ከሌሎች የስለላ መረጃዎች ጋር ተጣምረው ኢላማ የተደረገ አካል የሚገኝበትን ቦታ መለየት የሚያስችል መረጃ ይገኝበታል።

የዘርፉ አጀማመር በ 1803 የዩናይትድ ስቴትስ ሶስተኛው ፕሬዝዳንት ቶማስ ጄፈርሰን በናፖሊዮን ፈረንሳይ በዋሽንግተን የተካተቱትን አዳዲስ ግዛቶች እንዲመረምር በሆነበት ወቅት ነው፤ የሚሉ መረጃዎችን ተመልክቻለሁ።

በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ይህ ዓይነቱ የስለላ ጥናት ዘርፍ በዋነኛነት በዩናይትድ ስቴትስ በተለየ ትኩረት የተጀመረ ሲሆን ከሴፕቴምበር 11 ጥቃት በኋላ የካርታ ጥናት ቡድኖች ትልቅ ሚና ከተጫወቱ በኋላ የጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ “GEOINT” አስፈላጊነት ብቅ አለ።
በተለይም ሽብርተኝነትን፣ የቴክኖሎጂ ፉክክርን፣ እንደ ሳይበር ጦርነት ወይም ልዩ ልዩ ወታደራዊ ስልቶች፣ እንዲሁም ማህበራዊ አለመረጋጋትና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ለሀገሮች ብሄራዊ ደኅንነት ሥጋቶች ባሉበትና እየተለዋወጡ ባሉት የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ዘርፍ በጣም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

የጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ በተለያዩ የአለማችን ቀጣናዎች መካከልም የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፉክክር መስክ ሆኗል። የአሜሪካው mitr ሪፖርት መሰረት በ2019 ብቻ የአውሮፓና የእስያ ሀገራት በጋራ ለጂኦስፓሻል የስለላ አገልግሎቶች ከአሜሪካ ከ 4 እጥፍ በላይ በጀት ወጪ አድርገውበታል።

▪️በብሔራዊ ደህንነት ውስጥ የጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ
ይህ አይነቱ የመረጃ ትንተና አስፈላጊነት እንደ ሀገር እጅግ ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጠው ስጋት መገኛ ቦታ መለየት ላይ ቀዳሚው ጠቀሜታው ነው። በተገኘው መረጃ መሰረትም አስፈላጊ ግብአቶች ማሟላት የሚቻልበትን ሁኔታ ይገመግማል። በዚህም ከተለያዩ አካላት ትብብርን ለማሳደግ ወሳኝ እውቀት ይገኝበታል። በዚህም ለቅድመ ማስጠንቀቂያና ለቀውሶች ትንበያ በተለይም በወታደራዊ፣ በመከላከያና በስለላ ስራዎች ውስጥ አስፈላጊው አቅም ውጤታማ እና ወቅታዊ በሆነ መንገድ እንዲሟላ ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው።

▪️ቻይና
በምዕተ-አመቱ አጋማሽ የአለምን የጠፈር እንቅስቃሴዎች የበላይነት እንደ ሀገራዊ ግብ ያስቀመጠችው ቻይና የተለያዩ ተደራራቢ የሳተላይት ፕሮግራሞችን ለምድር ምስል እና ካርታ ስራ ለወታደራዊ እና ለሲቪል አላማዎች እየተገበረች ትገኛለች። በተጨማሪም በዜጂያንግ ግዛት ውስጥ “የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የጂኦስፓሻል እውቀትና ፈጠራ ማዕከል” ማእከልን ለመገንባት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የ 2030 ዘላቂ ልማት ግብን ለመደገፍ የሚያስችል ግዙፍ የመረጃ ግብአት ለማግኘት ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመተባበር እየሰራ ትገኛለች። ይሁንና ይህን ተግባር ቻይና የክትትልና ስለላ አድማሷን ለማስፋት ትጠቀምበታለች በማለት ዋሽንግተን በስጋትነት ስትተቸው ትደመጣለች።

▪️ሩሲያ
ሀገረ ሩሲያም ባልተለየ መንገድ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ የጂኦፖለቲካዊ አቅም በሆነው የሰውን እውቀትና የኤሌክትሮኒክስ አቅምን ያቀናገ የካርታ ስራ ላይ ናት። ሩሲያ በጂኦግራፊያዊና የካርታግራፊያዊ ዘርፍ ከፍተኛ ውርስ ያላት ስትሆን ይህም አለም አቀፋዊ የተፅዕኖ ቦታዎችን ዝርዝር አመላካች ካርታዎችን ያጠናክርላታል። በሩሲያ ያለው የጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ ማህበረሰብ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመሳሳይ የአካዳሚክ ዘርፎችን ይጠቀማል።

▪️ኤምሬትስ
አቡዳቢ በወታደራዊ ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ በአጠቃላይም በወታደራዊ ስትራቴጂዋ ውስጥ ወሳኝ አካልና የወደፊቱ የብሄራዊ ደህንነቷ ትልቅ አንድምታ የሰጠ ስራ ከጀመረች ቆየት ብላለች። በ2011 እና 13ም አመታዊ የጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ የመካከለኛው ምስራቅ ኮንፈረንስን በመዲናዋ አስተናግዳለች። ኤሚሬትስ የጂአይኤስና የርቀት ዳሳሽ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የምትጠቀም ሀገር በመሆን ትታወቃለች።

Perspective on terrorism በተሰኘ ጆርናል ላይ የሰፈረ ጥናት እንደሚያመለክተው የሽብርተኝነት ምርምር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለ”ጂኦ-ስፓሻል ኢንተሊጀንስ” የሚተው ሲሆን ገላጭ ካርታዎች እና የላቀ ኮምፒዩተር አገዝ የቦታ መረጃ ትንተና ለወደፊቱ ምርምር ጠቃሚ ዘዴዎች ይሆናሉ።
እንደ ጥናቱ የሽብር ድርጊቶችን በ”ጊዜአዊ ባህሪያቸው” ላይ ከባህላዊ ትኩረት ይልቅ በ “የመገኛ ቦታ ባህሪያቸው” ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲል ያሰምርበታል።

ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ ከሚነገሩለት አንዳንድ ፈተናዎች መካከል ይህን መሰሉ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የፖለቲካ ተቃዋሚዎች የቦታ ቁጥጥር እንዲኖራቸው ለመደገፍ ሊውል ይችላል የሚለው ዋነኛው ነው። በተለይም ደግሞ ደሀ ሀገራት ለዚህ አላማ የሚውሉ ሳተላይቶችና አገልግሎቶችን በሚቆጣጠሩ ሀገራት ጫና ስር እንዲውሉ በቴክኒካል ደረጃም፣ መረጃው የሳይበር ጦርነቶችን ለመክፈትና የሳይበር ቦታዎች ይዞታን ለምሳሌ የድንበር/ወሰን ካርታዎች ወይም ሌሎች መሰል ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ይውላል።

▪️ለሀገራት በምክረ ሐሳብነት ከሚሰጡ ጉዳዮች መካከል ተከታዮቹን መርጨ አስቀመጥኩ፦
• በዘርፉ ለሽብርተኝነትን መዋጋት ለሰብአዊ ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች የተጋለጡ አካባቢዎች ላይ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸውን ኤጀንሲዎችን በጂኦስፓሻል ትንተና ማሰልጠን

• በዚህ ዘርፍ ከሚሰሩ ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ኩባንያዎች ጋር የዲፕሎማሲና የስለላ ስራዎችን ለመስራት ስምምነት በመፍጠር የጋራ ስልጠና መርሃ ግብሮችን ማሳደግ
• የጋራ የመረጃ ቋቶች መፍጠር
• ውጤታማ እና ሁለገብ ሳተላይቶች ስራ ላይ ማዋል..

የዓባይልጅ Esleman Abay

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories