ግብፅ፡ የናይል አሸባሪ እንጂ ከናይል ስጦታ የሚፃረር ታሪኳ


        የዓባይ፡ልጅ ✍️ እስሌማን ዓባይ

Terror State of the Nile, Not Gift of the Nile

==በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲደርስ የተሰናዳ==

በናይል ዙሪያ የግብፅ መሪዎች በተለይም ሰሞነኛው የአል-ሲሲ ድርጊት በህግ የሚያስቀጣ፤ ጠበቅ ያለ እገዳ ከአፍሪካ የሚያስከትል ነበር፤ ዳሩ አፍሪካ ለአፍሪካዊያን ገና አልሆነችማ..። የሆነ ሆኖ ሲሲ ግድቡን የፀጥታ ስጋት ሲሉ ያራመዷቸው ተግባራት እንደ “Logan Act” አይነት ህጎች ወደ ህጋዊ እንጦሮጦስ በከተቷቸው ነበር።
ጆርጅ ሎጋን የተባለ የፔንሲልቬኒያ ገዢ በአሜሪካ እና ረንሳይ መካከል የተፈጠረውን ቀውስ ሊደራደር ወደ ፈረንሳይ ተጓዘ። ይህን ተከትሎ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆን አዳምስ Logan Act የተሰኘ ህግ እንዲወጣ አደረጉ። በቀጣዩ አመት 1799 Logan Act ህግ ሆኖ ፀደቀ። አሜሪካ በገባችበት ግጭት ውስጥ ከማእከላዊ መንግስተ በስተቀር ወደ ታች ያሉ ባለስልጣናት በራሳቸው ሊደራደሩም ሆነ ምክክር ሊያደርጉ እንደማይችሉ ህጉ ከለከለ። ይህን ተላልፎ የተገኘም ሶስት አመት እስራት በትንሹ ይጠብቀዋል ተብሎ ታወጀ። በዘመነ ኦባማ የአሜሪካ house speaker ማይክ ፔሎሲ በራሷ ውሳኔ ወደ ደማስቆ ያደረገችው ጉዞ ከፍትህ አካላት ጋር ያላተማትም ይኸው ህግ በመኖሩ ነበር። የካይሮ ሰዎች አፍሪካ አንድ እንዳትሆን ለዘመናት መስራታቸው በጃቸው እንጂ ለፕሬዝደንት ሲሲ ንቀት ይህች የጥቁሮች ምድር ህጋዊ ዋጋቸውን በሰጠችልን ነበር።

ፕሬዝደንት ሲሲ ከባይደን ሲገናኙ የሰጡት የገነገነ ግትርነታቸው የተንፀባረቀበት መግለጫ ዛሬም ድረስ የህዳሴ ግድቡ የፀጥታ ስጋት ጉዳይ ነው ይላል። እውነታው ደግሞ በተቃራኒው የራሷ የግብፅ መሪዎች ከጥንት እስከ ዛሬ ለናይል ተፋሰስ ግጭትና ጦርነቶች ማእከል መሆናቸው ነው። ለልማት የሚገነባን ግድብ ለጦር መሳሪያ በሚያገለግል አለም አቀፍ ጉባኤ የወሰደች ብቸኛ ሀገር’ኮ ግብፅ ናት።
“…እየገነባን ያለነው የውሀ ግድብ እንጂ የኒውክሊየር ማብላያ አይደለም። ግድቡ ሰሞኑን በባዶ እግራቸው ከአረብ ሃገራት የሚያባርሯቸው ዜጎቻችንን ነፃ እንዲያወጣ የምንሰራዉ በመጠን ከአስዋን የሚያንስ ነው።” ሲሉ ዶክተር ኢንጂኔር ስለሺ በቀለ በትያትረኞች የተደገሰውን የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤ እምሽክ ያደረጉትም ታላቅ እውነትን በመያዛቸው ነበር።

በግብፅ የተናቀው አፍሪካ ብቻ አልነበረም፤ ራሱ የፀጥታ ምክር ቤቱ ጭምር እንጂ..። ኢንጂነር ስለሺ ቀጠሉ “የተባበሩ መንግስታት ድርጅት በሰጠው ፈንድ፤ የናይል ኢኒሼቲቭ ትብብር ማእቀፍ በተፋሰሱ 11 ሀገራት ተዘጋጅቶ ቀርቦላቸው፤ ግብፅ እና ሱዳን ግን የቅኝ ግዛት ውሎችን እንጂ ይህን ስምምነት አንፈርምም ብለው እዚህ አድርሰውታል..” ኢንጂነሩ የቅኚ ገዢዎችን አናት በመዶሻ ነረቱ…። ግብፅ ግን የቅኚ ግዛት ውሎች ይከበሩልኝ በሚለው ያለፈበት አቋሟ ቀጠለች።

በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ግብፅ አሉኝ የምትላቸው ታሪካዊ መብቶች አንግሎ-ኤጅብሺያን Anglo Egyption Treaty ተብሎ የሚጠራ በቅኚ ገዢዋ ብሪታንያ 1929 የተፈረመውን ውል መሰረት አድርጋ ነው።

የ1959 ስምምነትም በግብፅ እና በሱዳን መካከል የተደረገ የሁለትዮሽ ሰምምነት ሲሆን ለግብፅ በላይኛው ተፋሰስ የውኃ ሥራዎችን የመቆጣጠር የመፍቀድ እና የመከልከል መብት የሰጠ ሲሆን ከዓባይን የውኃ ፍሰት ለግብፅ 55.5 ቢሊዮን፣ ለሱዳን 18.5 ቢሊዮን እና (ለትነት 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ) የሚሰጣቸው ነው።

ሁለቱም ስምምነቶች በኢትዮጵያና በሌሎች የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ተቀባይነት የላቸውም። እነዚያ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች በኔሬሬ ዶክትሪን ውድቅ መሆናቸውም ይታወቃል።
ታንዛኒያዊው ጁሌስ ኔሬሬ ስምምነቶቹን ውድቅ በማድረግ ከሕዝባቸው ፍላጎትና ጥቅም አንፃር ከመከሩበት በኋላ ሐምሌ 1962 ለብሪታንያ፣ ግብፅና ሱዳን በላኩት ማስታወሻ “ታንዛኒያ በቅኝ ግዛት በተፈረመው ስምምነት አትገዛም። የናይል ውሃ ለሁሉም የተፋሰሱ አገራት አስፈላጊ በመሆኑ አጠቃቀሙም ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በፍትሃዊና ለሁሉም ህዝቦቻቸው ከፍተኛ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ መከናወን አለበት” ሲሉ ነው ያሳወቁት።
ኢትዮጵያ የኔሬሬ ዶክትሪንን የተቀበለች ሲሆን የ1959 ስምምነቶችን ያኔውኑ “አልቀበልም፤ አልታሰተፍኩበትም።” በማለት አውጃለች፡፡ ታንዛኒያ እና ኬኒያ በተመሳሳይ የቅኚ ግዛት ውሎችን አይቀበሉም።
ግብፅ እንግዲህ እነዚያን የቅኚ ግዛት ስምምነቶች፤ አነዚያን አግላይ እና ኢ-ፍትሐዊ የውኃ ውሎች ነው እስከዚህ ዘመን ድረስ “ታሪካዊ መብቴ” ስትል በማጣቀሻነት የምታቀርባቸው። እነሆ ከ90 ዓመታትም በኋላ የግብፅ መሪዎች እስከያዝነው 2022 ድረስ “አይነኬ ታሪካዊ መብቴ” ማለት መቀጠላቸው ለችግሮቹ ሁሉ ስረ መሠረት ነው።

የካይሮ ፀረ ሰላም ተግባራት ከህጋዊ ይልቅ ኢመደበኛ መፍትሄ በማማተር፤ ወታደራዊ ጫናን እና በተፋሰሱ ሀገራትና በውስጥ ጉዳያቸው መሀል ግጭት በመፍጠር፤ የውሃ ሃብቱ ባለቤቶችን በመናቅ የማይመለከታቸውን አካላት አሸማጋይ በማድረግ፤ የቅኝ ግዛት ውሎች በዚህ ዘመን ላይም እንዲከበሩ በመናፈቅ ወዘተ ይገለፃል። ይህንን ለማሳካትም የተለመደውን የተፋሰስ ሀገራቱን አንድነት የመከፋፈል ስልት መጠቀምን ትመርጣለች፡፡ ኢትዮጵያን የመረበሽ ተግባሯን ራሷ ካይሮ የማትክደው ደረጃ ግልፅ የሆነ ሀቅ ነው። ከዚያድባሬ ወረራ እስከ ትህነግን ማሳደግ፤ እንዲሁም ሽብርን በይፋ የተቀላቀለው ህወሃት ሸኔ እና ሌሎች ካይሮ ሰራሽ ናቸው። ከኦጋዴን እስከ አልፋሻቃ፤ ከቤንሻንጉል እስከ ጋምቤላ ሽብር ካለ ሁሌም ካይሮ አለች። እኛም ተመቻችተን ተገኘንላት፤ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሽብር ስራዋን አሳክታለች። በይፋ የተዘገቡ ሴራዎቿን ማውሳትም ይቻላል።
▪️ሜይ 5 ፣ 2014 ላይ ግብፃዊ ሰላዮች በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ዋሉ። ግብፃውያኑ በኢትዮጵያ ግድብ ላይ የደህንነት መረጃዎች ለመሰብሰብ ሲንቀሳቀሱ አቦቦ ግድብ አቅራቢያ እንዲሁም የተቀሩት ወደ ህዳሴ ግድቡ ለማምራት ሲሞክሩ ነበር የተያዙት፡፡
▪️እንግሊዝ የግብፅ የስለላ ሰዎችን ስልጠና መስጠት መጀመሯ ሌላኛው ሲሆን የእንግሊዙ MI6 ከሳውዲ አረቢያ እና ከግብፅ የተውጣጡ ሰላዮችን ነው ብሪፎርድሻየር በሚገኘው የጦር ሰፈር ነው በመገናኛ ብዙኃን ሚና እና የመረጃ ዘመቻ፣ የደህንነት ፖሊሲ እና የስለላ መረጃ ልውውጥ ላይ ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና ሌሎችም የደህንነት ጉዳዮችን የሸፈነ ስልጠና የሰጠችው፡፡
▪️ግብፃዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር african studies ስፔሻሊስት ዶክተር Badr Hassan Shafei ከሁለት አመት በፊት ባስነበቡት “Egypt between Horn of Africa” በሚለው ፅሁፋቸው ግብፅ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር በጥቅም በመተሳሰር የህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ጫና የማሳደር ስትራቴጂዋ ባለፈ፤ ካይሮ የቀደሞ አጋሯ ኤርትራን በጠ/ምኒስትር አብይ መነጠቋን ይጠቅስና እጇ ላይ የምትጠቀመው አማራጭ በኢትዮጵያ የብሔር ግጭቶች እጇን መክተት ስለመሆኑ ነበር በአደባባይ ያስነበበው። የቀጠናው አገራትን መሳሪያ እንደምታደርግም ነው ግብፃዊው ዶክተር ያለ ሀፍረት ያፍረጠረጡት።
እንዲህ ያፈጠጠ መንግስታዊ አሸባሪነት የምታራምደው ካይሮ አይኗ በጨው ታጥቦ የግድቡን ጉዳይ የጦር መሳሪያ አጀንዳው ወደሆነው ምክር ቤት ወሰደችው። ኢንጂነር ስለሺ የተናገሩት አሁንም ይታወሰኛል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የአፍሪካ አምባሳደሮች ስለ ሀይድሮ ፓወር ለአፍሪካ ያለውን አንድምታና በዚህ ረገድስ በተለይም ምስራቅ አፍሪካ ምን ያህል የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር እንዳለባት ተጨባጭ እውነታውን ለአምባሳደሮቹ ገለፁ፣
“ኢትዮጵያ አሁን ላይ በዓመት በሰው 100 ኪሎ ዋት ሃይል ብቻ ስታመርት በአንጻሩ ግብጽ አሁን ላይ 1 ሺ 800 ኪሎ ዋት በዓመት በሰው ደርሳለች፤ ግብጽ ከውሃ ውጪ ከኒውክሌር የምታመነጨው ሃይልም 4 ሺ 500 ሜጋ ዋት ነው፤ ከጂዎተርማልም በተመሳሳይ ከፍተኛ ሃይል ለማመንጨት እየሰራች ነው፡፡ ይህን ደግሞ የኢትዮጵያን 120 እጥፍ መሆኑን ነው..።” ኢንጂነር ስለሺ አፋቸውን አስከፈቷቸው።

የግድቡ ጉዳይ በካይሮ እና ጋሻ ጃግሬዎቿ ትብብር ያለቦታው ከፀጥታው ምክር ቤት እንዲገኝ ሆነ፤ ይሁን እንጂ ጉዳዩ እንዳሰበችው የእሳት ጉዳይ ሳይባልላት ቀረ፤ ምስጋና ለወዳጅ ሀገራት ታሪካዊ ድጋፍ ይሁንና ጉዳዩ የውኃ እና የልማት ጉዳይ ነው ተብሎም ወደ ቤቱ ወደ አፍሪካ እንዲመለስ ሆነ፤ ከጉባኤው በኋላ ካይሮ የጣሰቻቸው ነገር ግን የፀጥታ ምክር ቤቱ በወቅቱ በሰጠው ይፋዊ መግለጫው ካስቀመጣቸው የግጭት ማባረሪያ ጥሪዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው
▪️የአረብ ሊግ እና የአፍሪካ ህብረት አባል በሆነችው በቱኒዚያ ፕሮፖዛሎች ላይ ከተደጋጋሚ ዝግ ምክክሮች በኋላ በግብፅና ሱዳን ጥያቄ መሰረት June 15 አረብ ሊግ ስብሰባ ተቀምጦ፤ “ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ያለ አስገዳጅ ስምምነት እንዳታከናውን ጫና ያድርግ” የሚል ጥያቄ ለፀጥታው ምክር ቤት አድርሶ ነበር።
▪️የፀጥታው ምክር ቤት የግድቡን የሙሌትም ሆኘ አጠቃላይ አለመግባባት በተመለከተ ቀደም ሲል እንደ ቅድመ ሁኔታ ሲጠቀስ የነበረው አስገዳጅ ስምምነት የሚለው አቋም ተወግዷል።
▪️የፀጥታ ምክር ቤቱ ምንም መርሆ አለማስቀመጡን በአፅንኦት ነው የገለፀው። “statement does not set out any principles or precedent in any other transboundary water disputes”
▪️የፀጥታው ምክር ቤት “በመግለጫዬ ውስጥ አስገዳጅ መርሆ አላስቀመጥኩም ሲል በአፅንኦት እንዲያሳውቅ የምክር ቤት አባል የሆኑ አገራት የሰነዘሯቸው ማስጠንቀቂያዎች ሳቢያ መሆኑን ያሰመረበት ሲሆን በቀጣይ ድርድር ለሚፈጠር አለመስማማት እንዲሁም ሊቀርቡ በሚችሉ ቅሬታና አቤቱታዎች ምክር ቤቱ የሚጫወተው ሚና አይኖርም።
▪️ቱኒዚያ ከአራተኛው ረቂቅ በፊት ባቀረበቻቸው ተከታታይ ፕሮፖዛሎች ውስጥ ያካተተችውና በቀጣይ የግድቡ ድርድር ውጤትን በተመለከተ ዋና ጸሐፊው በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለፀጥታው ምክር ቤት ሪፖርት እንዲያቀርብ” የሚለው መጠይቅ የፀጥታ ምክር ቤት አባል ሀገራቱ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ በፀጥታው ምክር ቤት የ GERD ጉዳይን አጀንዳ ማድረግ የለበትም በማለት ተቃውመውት ከፕሮፖዛሉ እንዲወገድ ሆኗል።
▪️በተመሳሳይም ምክር ቤቱ ሦስቱ አገራት የድርድሩን ሂደት ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲቀጥሉ እና “ማንኛውንም አፍራሽ መግለጫ ከመስጠት ወይም የድርድር ሂደቱን አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ተግባር ከመፈፀም እንዲቆጠቡ” ጥሪ አሰምቶ ነበር።
▪️ምክር ቤቱ “በአፍሪካ ህብረት ስር በሚደረገው ድርድር ስለ ግድቡ ሙሊትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሶስቱም አገራት የሚያፀድቁት የመስማሚያ ነጥቦች ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንዲመጣ ይሆናል።
▪️ምክር ቤቱ ግድቡን በተመለከተ አስገዳጅ መርሆ ሊያደርገው የሚችለውም ይህንኑ ሶስቱም አገራት የሚስማሙበት ሐሳብ ብቻ ይሆናል…።

ግብፅ በአጭሩ እንዲህ ናት፤ ነበረችም። ይህ ታሪኳ መንግስታዊ አሸባሪ ለመባል ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፤ ጉልበት ከጊዜ ነውና አላደረግነውም። እንደ ሀገር ጉልበተኛ የመሆን ቁጭት ጣሪያ የሚነካውም መሰል ብሶት ሲሰማህ ነው። ግብፅ Gift of the Nile አይደለችም፤ የሚገልፃት Terror State of the Nile ነው።

#eslemanabay | የዓባይ ልጅ

#GERD #gerd4all #ItsAfricanDam #Ethiopia #Eritrean #sudan #Egypt #HornOfAfrica  #IMF

https://eslemanabay.com/egyptian-spies-captured-while-gathering-intelligence-on-ethiopian-dams/
https://eslemanabay.com/egypt-on-the-centre-of-horn-of-africa-renaissance-dam-crisis/
https://eslemanabay.com/tplf-egypt-eu-us-drama-at-un/

https://eslemanabay.com/egypt-bet-horn-of-africa-settlements-gerd-crisis/
https://eslemanabay.com/britain-is-training-spies-from-saudi-arabia-egypt-and-the-uae/

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories