ሶስቱ አሉታዎች: አል-ፋሻቃ ~ አል-ቡርሃን ~ አል-ሲሲ እና የኢትዮጵያ ጥንቃቄ

Esleman abay ✍️ የዓባይ:ልጅ

“ጦር ሜዳውን ራስህ ካልመረጥክ አትዋጋ።” ይለናል የጥንታዊው ቻይናዊ sun Tzu የጦርነት ጥበብ አንደኛው መርሆ..። ምክንያቱን ሲያብራም “..ጠላት በመረጠው ጦር ሜዳ መዋጋትህ አንተ ከምታውቀውና ከተዘጋጀህበት በተለዬ ጠላትህ በላጭ ይሆናልና..” ሲል ይመክራል። ነገረ-አልፋሻቃን የተመለከቱ መረጃዎች መውጣት መጀመራቸውም ከመሰል ስትራቴጂዎች አንፃር መመርመር ተገቢ ስለመሰለኝ ነው ይህን ፅሁፍ ያዘጋጀሁት..።
እንደ መረጃዎቹ “..በአልፋሻቃ መሬቶች የነበሩ (አልቡርሃን-መራሽ) የሱዳን ወታደሮች ከቦታው ለቅቀው እየወጡ ናቸው..” በማለት የተሰራጩ ሲሆን፤ የመረጃው አቅጣጫም ሆነ አመጣጡ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑ ነው የሚያመዝነው..።

የአሁኑ የሱዳን ውጊያ ትያትር በዋነኛነት የሃያላን ድርሰት ሲሆን ሁለቱ የጦር መሪዎች በሀያላኑ ስክሪፕት መሰረት የመተወን የመተወን ሚና ላይ ናቸው። ሁለት የኢትዮጵያ ስጋቶች የሚያደርጉት የፍልሚያ ተውኔት የልቀት resolution ደረጃውን ሲያገኝ ማንን አሸናፊ እንደሚያደርግ ከኢትዮጵያ በኩል ለተመለከተው ለመረዳት ከባድ አይሆንም። ሁለቱም ተፋላሚዎች የጦር አቅም እንጂ ህጋዊ እውቅናም ሆነ ሕዝባዊ ይሁንታ የሌላቸው ጊዜያዊ ባለስልጣናት እንደመሆናቸው ግጭቱ የቡድን ጥሎ መለፍ ሽኩቻ የወለደው ነው። ከነሱ አመክንዮ በላይ አንገብጋቢ ጉዳይ ያለባት ካይሮ በበኩሏ አንደኛውን ደግፋ የጦር ጀቶቿን በውጊያው ላይ አሰማርታለች። ይህ በሂደት የራሱ ጣጣ ያለቅ ድርጊት መሆኑን ታውቃለችና ህገ-ወጡን ውጊያ ተሳትፎ ምክንያታዊ መደላድል ለመስጠት ኢትዮጵያን ጎትታ በግጭቱ ማሳተፍ ትሻለች። የሚጠብቃትን ዘርፈ ብዙ ቀውስ በኢትዮጵያ ላይ ማውረድን ትመርጣለች። እዚጋ sun tzu “ሁለት ወገኖች ግጭትን ሲመርጡ ከመካከላቸው ቢያንስ አንዱ ስህተት ነው። ምናልባትም ሁለቱም ስህተት ናቸው። “አሸናፊው” የሚሆነውም ቢሆን የተሳሳተ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እያንዳንዱ ግጭት ሁሉንም ተሳታፊዎች ስለሚያዳክማቸው..። ታዲያ በውጊያው ራሱን በደምብ አድርጎ ባዳከመው ላይ የሱው ባላንጣ የበላይ ሆኖ ላይ ይቀመጣልና.. ” ይለናል።

The art of war ላይ “..ድል ​​አድራጊዎች ቀድመው አሸንፈው ወደ ጦርነት ይሄዳሉ፣ ተሸናፊ ተዋጊዎች ግን በመጀመሪያ ወደ ጦርነት ይገቡና ከዚያ በኋላ ነው ለማሸነፍ የሚፍጨረጨሩት..።” የሚለውን እናገኛለን። ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን ተጨባጭ የምትጠቀምበት አውድ ተፈጥሮላታል። ግብፅን ጨምሮ ሁለቱም የሱዳን ተፋላሚዎች በኢትዮጵያ ጥቅም በኩል ትልቅ ነጥብ የሚጥሉበት ጊዜ ላይ ናቸው። ለአልፋሻጋ ሉአላዊ እልባት ማግኘት ጉዳይ የኢትዮጵያ የቤት ስራ ሲሆን ከመቸውም ጊዜ በላይ የተመቻቸ አጋጣሚ የተፈጠረበት ወቅት ላይ ነን ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ካይሮ ወደ መዳፋቻን የተጠጋውን የአልፋሻቃ ካርድ የምታመላክተን ከሆነ ጉዳዩ የሱዳኑን ጦርነት ሰፊ ምስል እንዲደበዝዝብንና ቁልፉ ጉዳይ ላይ ከማተኮር እንዳያደናቅፈን ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልገናል።

አራተኛው ሙሌት ምናልባትም የመጨረሻው የግድቡ ምዕራፍ ሊሆን ይችላልና ጭንቀት ውስጥ የገባችው ካይሮ በሱዳኑ ጦርነት አልቡርሃን በየትኛውም መንገድ ድል ቢቀናው ቢያንስ የተስፋ ስንቅ ይሆናታል። የጀነራሉ ሽንፈት ግን የሞት ሞቷ ይሆናልና ይህን ከመመልከት ሱዳን እንደ ሶሪያና የመን የተልዕኮ ጦርነት አውድማ ብትሆን ትመርጣለች። የዚህ ወላፈን ዋነኛ ኢላማዋ ኢትዮጵያ ናትና ወደጫረችው እሳት እንዳታስገባን እያንዳንዷን የካይሮ ቀመር በጥንቃቄ መከታተል ጠቃሚ ጉዳይ ይሆናል። ለዚህም በ Sun Tzu መፅሐፍ ከሰፈሩ የጦርነት መላዎች አንፃር የተወሰኑ ነጥቦችን ለመምዘዝ እንሞክር…።

▪️ “ጠላትህን በተውሶ ቢላ ግደል” የሚለው አንዱ የሰን ዝሁ የውጊያ ማሸነፊያ ስትራቴጂ ነው። በዚህም ጦርነትክን ሶስተኛ ወገን እንዲፈጽመው ወይም “የጠላት የእርስ በርስ ጦርነት” እንዲፈጠር በማድረግ የባላንጣህን አከርካሪ ስበር የሚል ሐተታ የተቀመጠለት ነው።

▪️ “ቤቱ ሲቃገል ዝረፈው” – ይህ የ art of war ሌላኛው የውጊያ ማሸነፍ ምክር ሲሆን፤ “ባላንጣህን ለማጥቃት በጣም የተመቻቸ የሚባለው ጊዜ በውስጥ ጣጣው የተጠመደበት ወቅት ነው።” የሚል ሲሆን አክሎም፣ “የሚቃጠለውን ቤት የሚዘርፍ ሰው በእሳቱ ሊበላ ይችላልና ከወጥመድ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለበት።” ሲል ያስጠነቅቃል።
ኢትዮጵያ የአልፋሻቃን ጉዳይ መሰል የጎንዮሽ ውጤት በከበበው ወጥመድ በኩል ለማሳካት እንድትሞክር ካይሮ አትቀምርብም ብሎ መዘናጋት እንደማያስፈልግ ግልፅ ነው።

ከተጠቀሱት የካይሮ ስትራቴጂዎች በአንዱ ወይም በሌላው ኢትዮጵያ ብትገባላት ለግብፅ ከሚያስገኘው ስኬት በተጨማሪ በሱዳኑ ጦርነት በርካታ ምዕራባዊያን፣ የባህረ ሰላጤው እንዲሁም ለአሜሪካ መራሹ ህብረት እንደ ስጋት በሚቆጠሩ ባላንጣ (ሀያላን ሀገራት) ጭምር አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ ለግብፅ “Befriend a Distant State While Attacking a Neighbor” በሚለው የ sun tzu መርሆ ጭምር ነጥብ ልታስቆጥር ትችላለች ማለት ነው።

በጥቅሉ፣ የአልፋሻቃ መሬት ላይ ካይሮ ፀረ-ኢትዮጵያ ጨዋታዋን ድጋሚ የምትደግስበት ሜዳ እንዳይደረግ ተገቢው ጥንቃቄ እንደምናደርግ ተስፋ ይደረጋል።

ሠላም ለሱዳናዊያን ! ሠላም ለሁሉም ሰው

✍️ Esleman abay #የዓባይልጅ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories