
By, Esleman Abay የዓባይ ልጅ
” የግብፅ ፓርላማ ስምምነቱን ማፅደቁን ተከትሎም በመላ ሀገሪቱ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር፣ ተቃዋሚዎችም ዘመቻ ሲያደርጉ ነበር…
የግብፅ ሉዓላዊ ይዞታ የነበሩት ቲራን እና ሳናፊር የተባሉት የቀይ ባህር ደሴቶች በሳኡዲ አረቢያ ካርታ ላይ በይፋ መካተታቸውን የዘገበው የሳዑዲ ፕሬስ ድርጅት በዕለተ ሰኞ ዘገባው ነው። የሳውዲ አረቢያ የዳሰሳና ጂኦስፓሻል መረጃ ባለስልጣን GASGI በግብፅ እና በሳውዲ አረቢያ መካከል የረጅም ጊዜ ውዝግብ ሰበብ የነበሩትን ሁለት ደሴቶች በማካተት አዲስ በተሻሻለው የግዛቷ ድንበሮች ካርታ ላይ በይፋ አሳትሞ ማውጣሙን ተዘግቧል።
የሳኡዲው የ GASGI ተቋም የሀገሪቱ የመንግስት ባለስልጣናት አዲሱን ይፋዊ ካርታ በድረ ገፆች፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በመጽሃፍት ወይም በብሮሹሮች ላይ እንዲያትሙ ጠይቋል ሲል ነው የሳኡዲው የመረጃ ኤጀንሲው የገለፀው።
የሳውዲ ፕሬስ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው “GASGI የሳኡዲ መንግሥትን የሚወክሉ ኤጀንሲዎች በአለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ኮንፈረንሶች እና ከጂኦስፓሻል መረጃዎች ጋር በተያያዙ መድረኮች አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ይሰጣል” ሲል የዘገበ ሲሆን “ወቅታዊ የሆኑ የመንግሥት ኦፊሴላዊ ካርታዎችን እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀርቧል። ይህም ዓለም አቀፍ የመሬትና የባህር ድንበሮች እንዲሁም ደሴቶች በትክክል መገለጣቸውን ያረጋግጣል ነው የተባለው።
ደሴቶቹ ወደ ሳኡዲ የተላለፉት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ በ2016 ደሴቶቹን በይፋ ለሳዑዲ አረቢያ እንዲተላለፉ ከፈረሙ ከሰባት ዓመታት በኋላ የተፈፀመ ነው። የሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ አል ሳኡድ በተመሳሳይ አመት በሚያዝያ ወር ካይሮን ጎብኝተው ለግብፅ በርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ የኢንቨስትመንት ፓኬጅ ማወጃቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንንም የሳውዲ አረቢያው ኦካዝ ጋዜጣ “በግብፅ የደስታ በዓል” ሲል ነበር የገለፀው። የግብፅ ፓርላማ ስምምነቱን ማፅደቁን ተከትሎም በመላ ሀገሪቱ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር፣ ተቃዋሚዎችም ዘመቻ ሲያደርጉ ነበር።
ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የግዛቱን ይገባኛል ጥያቄ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ቲራን እና ሳናፊር የሳውዲ አረቢያ እና የግብፅ ወደቦችን በሚይዘው በአቃባ ባህረ ሰላጤ በር ላይ የሚገኙ ናቸው። የአቃባ ባሕረ ሰላጤ መግቢያ የእስራኤል ኢላት ወደብ እና የዮርዳኖሱ አካባ የሚገኝበት ቦታ ነው።
ደሴቶቹ በ1967 በእስራኤል ተይዘው ነበር – በ1982 ሁለቱ ወገኖች የካምፕ ዴቪድ የሰላም ስምምነትን ፈርመው ደሴቶቹ ወደ ግብፅ እስከሚመለሱበት ጊዜ ድረስ ማለት ነው። በግብፅ እና በእስራኤል መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎም ሁለቱ ደሴቶች ከ1979 ጀምሮ የጥቂት አለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጣቢያ በመሆን አገልግለዋል።
ላለፉት ረዘም ያሉ ወራት አሜሪካ ቲራን እና ሳናፊርን ከግብፅ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማዘዋወር ድርድሩን ስትመራ መቆየታ የተዘገበ ሲሆን፤ በወርሃ ሐምሌ 2022 ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ወታደሮችን ጨምሮ አለም አቀፍ ሰላም አስከባሪዎች በዓመቱ መጨረሻ ቲራንን ለቀው እንደሚወጡ ተናግረው ነበር። በዚሁ ወር የእስራኤል ባለስልጣናት እነዚህን ስትራቴጂክ ደሴቶች ወደ ሳውዲ አረቢያ እንዲዘዋወሩ አረንጓዴ መብራት ስለመስጠቷ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ አክሲዎስ የዜና ምንጭ መዘገቡ የሚታወስ ነው። ይህ ውሳኔ በእስራኤል እና በሳኡዲ መካከል የተጀመረው የሰላምና ቅርርብ የመፍጠር እቅድ እንቅፋት እንዳይገጥመው ከማሰብ የመነጨ ነው በማለትም ዘገባው ገቁሞ ነበር።
ሁለቱ ደሴቶች እ.ኤ.አ. በ2018 ከግብፅ ወደ ሳዑዲ እንዲዘዋወሩ ከስምምነት የተደረሰባቸው ቢሆኑም፣ በ1979 በእስራኤልና በግብፅ በተደረገው የሰላም ስምምነት መሰረት በግዛቶቹ ላይ በሚደረግ ማናቸውም የይዞታ ለውጥ ላይ የእስራኤል ፈቃድ የግድ ያደርገው ስለነበር ሊዘገይ መቻሉ ይገለፃል።