“ግብፆች ጦርነትን ፈጽሞ አይሞክሩትም!” – የኢኮኖሚ ምሁር ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ

ግብፅ ከአባይ ጋር የተያያዘ 14 የሚኒስቴር መ/ቤቶች አሏት


የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ግብጽና አሜሪካ የውዝግብ መነሻ ባደረጉት የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለጋዜጣው ኢኮኖሚያዊ ትንተናዎችን በመስጠት የሚታወቁትን የኢኮኖሚ ምሁር ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄን በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

አሜሪካ የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በሚደረገው ድርድር ላይ በግምጃ ቤት ሃላፊዋ በኩል መግለጫ የመስጠቷ አንድምታ ምንድን ነው? አሜሪካና አለም ባንክ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለው ያስባሉ?
በዓለም ባንክ በኩል ምንም አይነት ችግር ይፈጠራል የሚል ግምት የለኝም፡፡ በእርግጥ የአለም ባንክ ዋና አዛዥ አሜሪካ ናት፤ ጫና ሊኖር ይችላል፡፡

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወዳጅነት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ነው፤ በተለይ በፀረ ሽብር እንቅስቃሴ ከአሜሪካ ጋር ከፍተኛ ትስስር ፈጥራለች፡፡ ከዚህ አንፃር አሁንም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት ነው የምገምተው:: አሜሪካ በጀት መድበን ፍልስጤምን እናለማለን፤ ነገር ግን በእስራኤል የበላይነት የሚተዳደር መንግስት መመስረት አለበት የሚል አቋም አላት፡፡

ለዚህም የአሜሪካን ኤምባሲ ወደ እየሩሣሌም አዛውራለች፡፡ በሌላ በኩል፤ ግብጽ ደግሞ ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ ነው፡፡ ግብጽ በአረቡ አለም እንደ መሪ ስለምትታይ፣ የግብጽ ጥቅም ተነካ ማለት ከእስራኤል ጋር ያለው ግንኙነት ይበላሻል የሚል ግምት በመኖሩ ይመስለኛል፣ አሁን አሜሪካኖቹ ግብጽን ለመርዳት የተነሱት፡፡

ሁለተኛ ደግሞ ግብጽ 90 በመቶ የውሃ ፍጆታዋ ከአባይ የሚመጣ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ አንፃር አሜሪካኖች ግብጽን ለመርዳት ነው የሚፈልጉት፡፡ እንዲያም ሆኖ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እስከ መካረር የሚደርስ ጫና አታደርግም:: ድንገት ተነስታ ጫና ለማድረግ ወይም እርዳታ ለማቋረጥ ብትሞክር ራሷ ናት ትልቅ ችግር ውስጥ የምትገባው፡፡
እንዴት?

እንደሚታወቀው፤ በአፍሪካ ላይ የቻይና ተፅዕኖ እየጠነከረ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቻይና ለአፍሪካ የምትሰጠው ብድርና እርዳታ ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል:: አሜሪካም ከዚህ እኩል መስጠት አለባት ብለው ፕሬዚዳንት ትራምፕ 60 ቢሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በርከት ያለው ገንዘብ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ላሉት አገራት የሚሰጥ ነው፡፡ ስለዚህ የቻይናን ተፅዕኖ ለማሳነስ የሚያደርጉት ጥረት አለ ማለት ነው፡፡

አሁን አሜሪካም ሆነች አለም ባንክ፣ ኢትዮጵያን አንረዳም የሚል ነገር ውስጥ ከገቡ፣ ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ጠቅልላ ትገባለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት ደግሞ ዋና መሠረቱ አዲስ አበባ ስለሆነ፣ ከአፍሪካ ጋርም ችግር ውስጥ እንገባለን ብለው ስለሚሰጉ ጫና ያደርጋሉ የሚል ግምት የለኝም፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እያለ እንዴት በግምጃ ቤት በኩል መግለጫ ልታወጣ ቻለች? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

እንግዲህ አሁን እንደምናየው፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በብዙ ጉዳዮች የተጠመደ ነው፡፡ ከአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሊቢያና ኔቶ ጋር ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ ምናልባትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በእነዚህ ጉዳዮች ተጠምደው ይሆናል፡፡ ሌላው ግብጽ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማግባባት ታደርጋለች፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ወደ ትራምፕ እየደወሉ ‹‹ወንዙን ሊያደርቁብን ነው፣ ሊጨርሱብን ነው›› እያሉ ይነግሯቸዋል፡፡

በአሜሪካ በኩል የ “ሰብአዊ ጠበቃ ነኝ” የማለቱ ጉዳይ ስላለ ይመስለኛል፣ ተገፋፍተው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት፡፡ ነገር ግን የኛም መንግስት በሚያደርገው ጥረት፣ ያለውን እውነታ እየተረዱ ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል፤ ጠ/ሚኒስትራችን የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያ ጠብ አጫሪ አለመሆኗን የሚያስመሰክር በመሆኑ፣ ፕሬዚዳንቱ ነገሩን በበጐ እየተረዱት ይመጣሉ፡፡ እናም ዲፕሎማሲው ሚዛናዊ ሊሆን ይችላል:: ግብጽ የመጨረሻ አማራጭ የምትለው ጦርነት ነው፡፡ ወደ ጦርነት ግን ብቻዋን መግባት አትችልም፡፡

አንደኛ፤ ያለችበት ቦታ ሩቅ ነው፤ ለጦርነት አያመቻትም፡፡ ሁለተኛ፤ ሱዳንና ኤርትራን ይዛ ነው ኢትዮጵያን ማጥቃት የምትችለው፡፡ በዚህ ደግሞ ጦርነቱ በጣም አክሳሪ ነው የሚሆንባት፡፡ በነገራችን ላይ ግብፆች አባይን ለመቆጣጠር ብዙ ጊዜ ሞክረዋል፡፡ በአፄ ዮሐንስ ዘመን፣ ጉራ እና ጉንደት ላይ ተሸንፈዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ግብፆች ብዙ መከራ አድርገዋል፤ ነገር ግን አንዱም አልተሳካላቸውም፡፡ በሌላ በኩል፤ የግብጽ የጦር ሃይል የአሸናፊነት ታሪክ የለውም፡፡ በ1970ዎቹ ወደ የመን 70 ሺህ ጦር ይዘው ገብተው፣ የየመን ሁቲዎች 20ሺዎቹን ገድለው ነው ያባረሯቸው:: ከእስራአል ጋር ሁለት ጊዜ ያደረገችው ጦርነትም ከሽፏል፡፡

እነዚህን ስናይ የግብጽ ጦር የቀጥታ ውጊያ ልምድም የለውም:: ስለዚህ ግብጽ ወደ ጦርነት ለመግባት አትሞክርም፡፡ ወደ ጦርነት ከገባች ደግሞ ከዚያ በኋላ መደራደር የሚባል ነገር ሙሉ ለሙሉ ነው የሚቆመው፡፡ ስለዚህ ጦርነትን ፈጽሞ አይሞክሩትም፡፡ ግድቡን እንምታ ቢሉም የሚሆን አይደለም፡፡ ምክንያቱም አሁን ግድቡ የደረሰበት ደረጃና የተሠራበት የጥራት ሁኔታ ፈጽሞ የሚፈርስ አይደለም:: የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ቲንክ ታንክ ቡድን ባወጣው ጽሑፍ፤ ‹‹ግብጽ ግድቡን ለማስቆም ምንም አይነት ወታደራዊ አማራጭ የላትም›› ብሏል፡፡

የግብጽ ሚዲያ የጦርነቱን ሁኔታ እንዲሁ ያናፍሰዋል እንጂ የሚሆን አይደለም፡፡ በመንግስታቸው ደረጃም ይሄን አቋም መያዝ አይችሉም:: አሁን አሜሪካ ልታደርግ የምትችለው፤ ‹‹ከግድቡ የምታመነጩትን ሀይል (6 ሺህ ሜጋ ዋት የሚባለውን ነገር) በሌላ መንገድ ማግኘት እንድትችሉ እናግዛችሁ፤ የውሃ አሞላሉ ግብፅን ሳይጎዳ ይከናወን›› የሚል የድርድር ሀሳብ ይዞ መምጣት ነው፡፡ ኦባማ የጀመሩትን ‹‹ፓወር አፍሪካ ፕሮግራምን›› እንደገና ወደኛ ይዘው ሊመጡም ይችላሉ፡፡

ሌሎች ምን አይነት አማራጮች ሊቀርቡ ይችላሉ?
እንግዲህ ግድቡ በሙስናም በምኑም ስለዘገየ ነው እንጂ እንደተባለው ከሦስት ዓመት በፊት አልቆ ቢሆን ኖሮ፣ እዚህ ሁኔታ ላይ ባልተዳረስን ነበር፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት አባይ ሸለቆ ላይ የዘነበው ዝናብ፣ በመቶ አመት ዘንቦ የማያውቅ መጠን ያለው ነበር፡፡ ግድቡ አልቆ ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ ውሃ ግድቡን ይሞላው ነበር፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሱዳን እየተጥለቀለቀች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበረች፤ ትርፍ ውሃ ነበር፡፡ ያ ውሃ ቢጠራቀም ኖሮ፣ ይሄ ነገር ባልተፈጠረ ነበር፡፡

ሌላው አሁን እነሱ አስዋን ላይ ከሚያጠራቅሙት ውሃ ላይ የሚተንነው ለመስኖ ከሚጠቀሙት መጠን በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ውሃው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ደጋ ላይ ቢሰበሰብ የሚጠቅመው ዞሮ ዞሮ እነሱኑ ነው፡፡ አንደኛ የሚተነው ውሃ ትንሽ ይሆናል፡፡ አስተማማኝ የሆነ የውሃ ምንጭ ይኖራቸዋል፤ እንደውም ድርቅ በሚኖርበት ጊዜም እዚህ ኤሌክትሪክ የሚያመነጨው ውሃ ሳይጓደል ይሄድላቸው ነበር፡፡ የማይቀንስ ውሃ ያገኛሉ፡፡ ምናልባት ሱዳን ለመስኖ እጠቀማለሁ ብላ ካላጎደለች በስተቀር ያልተቋረጠ ተመጣጣኝ ውሃ ያገኛሉ፡፡ ይሄን ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ድርድሩ አሜሪካኖቹ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ካልተጓዘ፣ የማታይማታ፣ አሜሪካ ማዕቀብ ትጥላለች የሚሉ ግምቶች ይሰነዘራሉ፡፡ የእርስዎ ግምት ምንድን ነው?

ማዕቀብ እንኳ አያደርጉም፡፡ አሜሪካኖች ማዕቀብ ደረጃ የሚደርሱት የራሳቸው ቀጥተኛ ጥቅም ሲነካ ነው። በሌላ በኩል፤ አሁን እንዳየነው፣ የአሜሪካ ኮንግረስ በፃፈው ደብዳቤ፣ ከወዲሁ ለምን እንዲህ አይት ነገር ውስጥ ተገባ ብለው ተቃውሞ እያቀረቡ ነው፡፡ የኮንግረስ አባላቱ ‹‹ለምንድን ነው እንዲህ አይነት ነገር ውስጥ የምትገባው?›› ብለው ለገንዘብ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል።

አሜሪካኖች ደግሞ በእንዲህ ያለ የምርጫ ጊዜ፣ ችግር ውስጥ መግባት አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ወደ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ተፅዕኖዋቸው ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህ እነ ትራምፕ ማዕቀብ ውስጥ ይገባሉ የሚል ግምት የለኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ አስቀድሜ የተናገርኳቸውን አማራጮች ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡

በተለይ በኢነርጂ አማራጭ ላይ ገንዘባቸውን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ እነሱ ይሄን ካደረጉ ግብፅ በድርቅ ጊዜ ውሃ የምታገኝበትን ስምምነት ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ሌላው የአሜሪካኖቹ አቅጣጫ ሊሆን የሚችለው፤ ከዚህ ቀደም የግብፁ መሪ አንዋር ሲናይ በነበሩበት ጊዜ፣ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ሲፈራረሙ፣ የአባይን ውሃ ወደ በረሃ ለእስራኤል ለመላክ ስምምነት አድርገው ነበር፡፡}

ከዚያ በኋላ እስራኤሎቹ ራሳቸው አላመኗቸውም፤ ስለዚህ ‹‹ውሃውን እንደዚህ ማድረግ የምትችሉ ከሆነ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለፍልስጤም ሁሉ እንዲዳረስ አድርጉ›› ብለዋቸው ነበር፡፡ ይሄን ያደረጉት ያው ‹‹ጦርነት እንኳ ቢፈጠር ውሃውን ለፍልስጤሞች ሲሉ አይዘጉትም›› በሚል ስሌት ነበር፡፡ አሁን ምናልባት እስራኤል የውሃ እጥረቷን ለማቃለል ከግብፅ የመውሰድ ሀሳብ ካላት፣ ለአሜሪካኖቹ አቤት ልትል ትችላለች፡፡

‹‹ለኛ የሚሰጡትን ውሃ ኢትዮጵያ አጠራቅማ ልታስቀርብን ነው›› የሚል አቤቱታ፤ እስራኤሎቹ ለአሜሪካ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በተለይ የትራምፕ ልጅ ባለቤት እስራኤልን ለመደገፍ የሚሰራው ስራ ይኖራል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በተረፈ ግን አሜሪካ ማዕቀብ ለማድረግ ትደፍራለች የሚል ግምት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ያንን ካደረገች፣ ሩሲያና ቻይና ሰተት ብለው ይገባሉ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለራሷ ብሄራዊ ጥቅም ስትል ማዕቀቡን አትሞክረውም፡፡
የአረብ ሊግ ውሳኔስ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ይኖራል?

አንደኛ አረብ ሊግ የሚባለው እርስ በእርሱ የተበታተነ ነው፡፡ አረብ ሊግ ሁለት ቦታ የተከፈለ ነው። አንደኛው ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትና ግብፅ ያሉበት ቡድን ሲሆን ሁለተኛው ኢራን፣ ቱርክና ኳታር ያሉበት ነው፡፡ በዚህ መልኩ የተከፋፈለ ነው፡፡ በውስጣቸው ያለውን ልዩነት እንኳ በሊጉ በኩል መፍታት አልቻሉም፡፡ የፍልስጤም ጉዳይ እስካሁን እልባት አላገኘም፡፡ ለየመን እስካሁን ድረስ አረብ ሊግ ምንም ያደረገው ነገር የለም፡፡

የአረብ ሊግ ጥፍር የሌለው ስብስብ ነው፡፡ ይሄ ጉዳይም ሲቀርብ ውይይት ሳይደረግበት ዝም ብሎ ነው ያሳለፉት፡፡ እኛ ከአረብ ሊግ ጋር ጥሩ ግንኙነትም ኖሮን አያውቅም፡፡ ነገር ግን አረብ ሊግ ውስጥ ጥሩ ተጫዋች ናቸው የሚባሉት ሳውዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ጥሩ ግንኙነት በዚህ ውሣኔ ሲሳተፉም ግብጽ መጐዳት የለባትም ከሚል እንጂ እንደ እገዛ አይሆንም፡፡

ጫና ለማድረግም ፍላጐት ይኖራቸዋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ዋናው ነገር ጂኦ ፖለቲካው ላይ ቻይናና ሩሲያ ሌላ ሃይል እያሰባሰቡ ባለበት ሁኔታ አሜሪካ ጠብ ውስጥ መግባት አትፈልግም፡፡ ሌላ ችግር ፈጥራ የጦርነት ቀጠና መፍጠር አትፈልግም፡፡ አረብ ሊግ ግን እስከዛሬ በሺ የሚቆጠሩ ውሣኔዎች አሳልፏል፡፡ ግን አንዱም ውጤታማ አልሆነም፡፡ ራሳቸውም ናቸው መልሰው የሚያፈርሱት፡፡ ስለዚህ የእነሱ ውሣኔ ብዙም ቦታ የሚሰጠው አይሆንም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን የያዙበትን አግባብ እንዴት አዩት?
በዋናነት ይሄ የሚመለከተው የውሃ ሚኒስትሩን ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለን ነው፡፡ እሣቸው ጉዳዩን በብቃት ይዘውታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአብዛኛው በመረጃና ማስረጃ ላይ ተደግፈው ነው ይሄን ጉዳይ ሲያስኬዱት የነበረው፡፡ ምናልባትም እንደሳቸው ብቃት ያለው ሚኒስትር ኢትዮጵያ አላት ወይም ነበራት ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ባለሙያ ናቸው፣ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ሰርተዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሚወዱና በጣም ኢትዮጵያን የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡ እሳቸው ማድረግ ያለባቸውን እያደረጉ ነው፡፡ እንደውም ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ ነው እየተከተሉ ያሉት፡፡ አሁንም የኛ ዲፕሎማሲ መሆን ያለበት ‹‹ግብጽን የሚጐዳ ነገር አንሠራም፤ የግድቡ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ግብጽና ሱዳን ናቸው፡፡›› የሚለውን አቋም ይዞ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ የግብጽ አካሄድ ግን እኛን እንደ ቅኝ ግዛት ይዘው ውሃውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ነው፡፡

በድርድሩም ሆነ በግድቡ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አንደኛ ግድቡ በፍጥነት ማለቅ አለበት:: ሁለተኛ ግድቡን መጠበቅ ነው፡፡ በዚህ በኩል በርካታ የውጭ ሀገር ተንታኞች፤ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመጠበቅ ያላትን ሃይል በብቃት አሠማርታለች እያሉ ነው፡፡ አንድ የአሜሪካን የጥናት ድርጅት ባወጣው ሪፖርትም ከሩሲያ የመጡ ሚሣኤሎች ግድቡን ከጥቃት ለመከላከል ተተክለዋል:: ግድቡን በተጠንቀቅ ከመጠበቅ ጐን ለጐን ግን ግድቡ ግብጽን እንደማይጐዳ ማስረዳቱ መቀጠል አለበት፡፡

ነገር ግን ‹‹ይሄን ያህል ሊትር ትሠጡኛላችሁ›› የሚል አይነት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል:: ግብፆቹ ውሃው እንደማይጐድልባቸው እኮ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እንደውም በ1977 በሀገራችን ድርቅ ባጋጠመ ጊዜ፣ እኛ እየተራብን፣ እነሱ በአባይ ሲጠግቡ ነበር:: በወቅቱ አለም ሁሉ እየተረባረበ እርዳታ ሲለግስ ግብፆች ግን አንድ ማዳበሪያ እርዳታ እንኳን አልላኩም፡፡ የአባይ ተፋሰስ በተራበ ጊዜ እነሱ እየጠገቡ ያድሩ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ዞር ብለው እንኳ ለማየት አልፈለጉም:: የኢትዮጵያ መንግስት አቋም ግን ሁሌም ‹‹ግብጽን የሚጐዳ ነገር አናደርግም›› የሚል ነው፡ ይሄ አቋም አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከግብጽ ለሚነሱ ነገሮች ፈጽሞ መደናገጥ የለበትም፡፡ ዋናው ግብጽን ለመጉዳት አለመንቀሳቀሱን ማስረዳት ነው የሚያስፈልገው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አቋሙን ፈጽሞ መቀየር የለበትም:: ግብጽ ውስጥ አባይን በተመለከተ ብቻ 14 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ናቸው ያሉት፡፡ እኛም በአባይ ጉዳይ ተመጣጣኝ አካሄዶችን መጠቀም ይኖርብናል፡፡ የአባይን ጉዳይ የሁሉም ህዝብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories