
ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ – GERD ሲጠናቀቅ የበረከቱ ፋይዳዎች እንደምታገኝበት ከተለያዩ የምርምር ግኝቶች አንፃር በቀላሉ መገንዘብ የምንችለው ነው። ከነዚህ የግድቡ ፋይዳዎች መካከል ካይሮ የባሕር ውሃን ለማጣራት በመደበችው ከፍተኛ በጀት እና በክረምት የጎርፍ ወራት የሚከሰተውን የውሃ ብክነት በመቆጠብ እንዲሁም በግብፅና ሱዳን ከፍተኛ የሙቀት ቃጠሎ ሳቢያ በትነት የሚባክነውን ውሃ በመከላከል አንፃር ካይሮ ከህዳሴ ግድቡ በረከቶች ውስጥ ከፊሉን የሚያስገነዝበን ይሆናል። (በፅሁፉ ያካተትኳቸው አሀዞችን ከዋቢ ድርሳናት ለማረጋገጥ ከታች ያስቀመጥኳቸውን ሊንኮች ይጠቀሙ.)
1- ግብፅ የውሃ ችግር አለብኝ በማለት ከሁለት አመት በፊት 2020 ላይ በ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የውሃ ማጣሪያዎች ግንባታ አስጀምራለች።
ይህም 880 ሚሊዮን ኪዩቢክ ውሃ በአመት የሚያስገኝ ይሆናል።
2- እንግሊዝ እና ግብፅ በ 1925 እኤአ በጋራ ያደረጉትን ጥናት ጨምሮ በርካታ የዘርፉ የምርምር ግኝቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገነባ ግድብ የዓባይን ውኃ ማከማቸት በግብፅ አመታዊ ከ 10 እስከ 16 ቢሊዮን ኪዩቢክ የሚደርስ የውሃ ብክነት የሚያስቀር ነው። በሱዳን የሚገኙ ግድቦች የሚመዘገበው አመታዊ ትነት ደግሞ ከ 5 እስከ 7 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር መሆኑን ጥናቶች አስፍረውታል።
ከደም ባሉ ጊዜያት ጀምሮ ግብፅ አስዋን ግድብን ከጎርፍ አደጋ ለመጠበቅ በክረምት የጎርፍ ወራት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ወደ ቶሽካ በረሃ ሸለቆዎች የማፍሰስ ስራ እያከናወነች ነው የምትገኘው። ይህ ተግባር በተለያዩ ከተሞቿ ላይ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሲያደርስ የሚታወቅ ነው።
▪️ስለሆነም በግብፅ እና በሱዳን የሚመዘገበው አመታዊ የትነት ብክነት ከ 15 እስከ 23 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚደርስ ሲሆን የዚህን አማካይ ማለትም 19 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ ለስሌታችን አንዱ መነሻ ማድረግ እንችላለን።
3- የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት እንደተቀመጠው የህዳሴ ግድቡ በክረምት የጎርፍ ወቅቶች ግብፅ የሚገጥማትን የጎርፍ አደጋ እንዲሁም ወደ ቶሽካ ሸለቆ እየተለቀቀ የሚባክነውን ውሃ በመቆጠብ ከአስዋን ግድብ 5 እስከ 10 በመቶ በላይ ውሃ ማዳን የሚያስችል ነው ብሏል።
▪️የዚህን አማካይ 7 በመቶ በማድረግ ከአስዋን የ 162 ቢሊዮን ኩዩቢክ አጠቃላይ የውሃ ይዞታ አንፃር በትንሹ 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ ከብክነት ይድናል ማለት ነው።
ከላይ በተገለፁ አሀዞች መሰረት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የትነት ብክነትን በ19 ቢሊዮን፣ የጎርፍ ብክነትን በ 10 ቢሊዮን በድምሩ 29 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በአመት በማዳን ግብፅ ገጥሞኛል የምትለውን እጥረት ማቃለል ከመቻሉ በተጨማሪ ችግሩን ለመቅረፍ የምትበጅተውን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያድንላት ይሆናል። በዚህም የህዳሴ ግድቡ በውሃ ብክነት ቅነሳ ግብፅን ከከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንደሚታደጋት ነው መገንዘብ የሚቻለው።
የግብፅ መንግስት በ 2020 ያስጀመራቸው 49 የባህር ውሃ ማጣሪያዎች ከአምስት አመት በኋላ ሲጠናቀቁ 880 ሚሊዮን ኪዩቢክ( 0.88 BCM) ውሃ በአመት እንዲያስገኙ ነው የታቀደላቸው ሲሆን ለፕሮጀክቱ 2.8 ቢሊዮን ዶላር መድቧል። በዚህ የወጪ ስሌት መሰረት 1 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማጣራት 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጣ ማጣሪያ መገንባት ጠይቋታል ማለት ነው። ወጪው ግን በዚህ አያበቃም እያንዳንዷን ሊትር ውሃ ከጨዋማ ባህር ላይ የማጣራቱ ተግባር በከፍተኛ ወጪ የታጀበ ሆኖ ነው የሚቀጥለው። ይህን የወጪ አሀዝ ከሳኡዲ አረቢያ የባህር ውሃ ማጣሪያዎች አንፃር እንመልከተው።
ከአለም የባህር ውሃ የማጣራት ስራ 18 በመቶ የሚሸፍነው የሳኡዲ አረቢያ Disalination plants፣ በሀገሪሁ ምስራቅና ምዕራባዊ የባህር ዳርቻዎቿ ከሚገኙ ማጥለያዎቿ 3.3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ ውሃ ለማግኘት 300,000 በርሜል ነዳጅ ትፈጃለች።
አንድ የሲኖ ትራክ የውሃ መጫኛ የሚሞላ ማለትም 20,000 ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማምረት ሳዑዲ 12 የሀገሪቱን ሪያል ወይም ደግሞ 3.20 የአሜሪካን ዶላር ወጪ ታደርጋለች – ( ከሰባት አመት በፊት የነበረው የወጪ ስሌት መሰረት..)።
SWCC ከሳውዲው ARAMCO እና ከሀገሪቱ ኤሌክትሪክ ኩባንያ ጋር የውሃ እና ኤሌክትሪክ ምርትን ያዋሃደ ለማጥናት በተፈራረመው የሶስትዮሽ አጋርነት መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የሆነው የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክቱ በቀን 1.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማግኘት 3000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ እንደሚጠይቀው ነው ይፋ ያደረገው።
በሌላ ማሳያ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ በነዳጅ ሃይል በምታደርገው የማጣራት ስራ አንድ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማግኘት 1 የአሜሪካ ያስወጣታል፤(በፀሐይ ኃይል solar) ደግሞ ለአንድ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ 2 ዶላር ወጪ ታደርጋለች።
በዚህ መሰረት የህዳሴ ግድቡ ከብክነት የሚያድነውና ግብፅ ያለምንም ስራ የሚያበረክትላት 29BCM የውሃ አቅርቦት ቢሊዮን ከባህር ውሃ ማጣሪያዎቿ የምታገኘው ቢሆን ኖሮ ግንባታው የሚያስወጣት የ $87 ቢሊዮን አሀዝ ሀገራችን ከምዕራባዊያን እግር ስር ወድቃ ከ 10 ለሚበልጡ አመታት የምታገኘውን ድምር የእርዳታ ገንዘብ የሚስተካከል ነው።
የውሃ ማጣሪያዎቿ ከላይ የተጠቀሰውን የውሃ አቅርቦት (28 BCM) ውሃ ለማስገኘት ማጣሪያዎቿ በነዳጅ ኃይል ቢሰሩ በየአመቱ 28 ቢሊዮን ዶላሮች ወጪ ግድ የሚላት ይሆናል።
በግብፅ የአስር አመት ሀገራዊ እቅድ ውስጥ ቢካተት ወደ ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ የሚያድንላት ሲሆን የውሃ አቅርቦቱ በሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ እና በስራ ዕድል ውስጥ የሚያስገኘው ፋይዳ ደግሞ ሌላኛው ትሩፋት ነው።
ከአምስት ግብፃዊያን የአንዱ ገቢ በግብርና ዘርፍ ላይ የተፈጠረ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሰረተውም በናይል ውኃ ላይ ከተመሰረተው ከግብርናው ዘርፍ የሚመነጭ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡም ሆነ በአጠቃላይ የዓባይ ጉዳይ አለም አቀፍና ቀጣናዊ ድርድሮች ውስጥ የውሃ ባለቤትነቷን አሳልፋ ላለመስጠት መፅናት አለባት የሚለው ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ይኸው የዓባይ ውኃ በመጪው ትውልድ ህልውና ላይ የመወሰን ስጋት ስላለው እና የማደግና የመበልፀግ ተስፋውም ላይ የተደቀነ አደጋ ያጠላበት ስለሆነ ነው።
ቀጣዩ ስጋት በዋነኛነት ጀርመን መራሽ በሆነውና አውሮፓ ህብረት እጁን ለማስገባት እያሟሟቀበት ያለው በስያሜው ቀጣናዊ “ትብብር” በሚል ስያሜ የጀቦኑት አደገኛ ወጥመድ ነው።
Esleman Abay #የዓባይልጅ #ኢትዮጵያ #ethiopia #ዓባይ #gerd #بحيرة_أفريقيا
ዋቢዎች:
https://eslemanabay.com/this-is-how-the-ethipian-dam-secures-egypts-future-water-needs/
