
ሂሩት በቀለ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ ለጦር ሰራዊትና ለፖሊስ ኦርኬስትራ ከ30 ዓመት በላይ ሙዚቃ ውስጥ ቆያታለች፡የሰፈር ጓደኛዋ ምድር ጦር በሙዚቀኝነት ለመቀጠር ማስታወቂያ ስለወጣ ወደዚያ ትሄዳለች፣ ሂሩትን እንድትሸኛት ትጠይቃታለች፡፡ አብረው ይሄዳሉ የተመዘገበችው ጓደኛዋ ስለነበረች ተፈትና እስክትመጣ ውጪ ትጠብቃታለች፣ ጓደኛዋ ጨርሳ መጣች ተያይዘው ከግቢው ሲወጡ ፈታኙ ጠራቸው፡፡
ፈታኙ፡- አንቺ እኮ አልተፈተንሽም
- ሂሩት፡- እኔ እኮ እሷን ለመሸኘት ነው የመጣሁት
- ፈታኙ፡- ነይ ሞክሪ
- ሂሩት፡- እኔ እኮ ዘፋኝ አይደለሁም እሷ ነች
- ፈታኙ፡- ግዴለም ሞክሪ
- ሂሩት፤- አልተመዘገብኩም እኮ
- ፈታኙ፡- ምዝገባው ችግር የለውም
የሂሩት ጓደኛ ‹‹ተፈተኚ ካሉሽ ሞክሪ በአንቺ የተነሳ እኔም እድል ላገኝ እችላለሁ›› አለች፡፡ ሂሩትም ላንቺ ስል ልሞክር ግን የማልፍ አይመስለኝም ትላለች፣ ተስማምተውም ወደ አዳራሹ ተመለሱ የምሳ ሰዓት ስለደረሰ ሙዚቀኞች እየወጡ ነው፣ በድምጽ ብቻ ተሞከረች ከተፈታኞቹ ሁሉ ሂሩት ብቻ ዘፋኝ ሆና ተቀጠረች
ምግብ አልበላም
የቡድኑ አባል በመሆን በ1951 ዓ.ም በአነስተኛ ደመወዝ ተቀጠረች አይነ አፋር ስለነበረች ከሰው ጋር ማውራት ትፈራ ነበር፡፡ ዳቦና ሻይ ሲቀርብላት እንኳን ሰው ባለበት መብላት ትፈራለች፡፡ የሚበላ ነገር ሲጋብዟት ‹‹ምግብ አልበላም›› ትላለች፡፡

አልመጣም
ሂሩትን ለዘፈን እያዘጋጇት በድንገት ትቀራለች፡፡ ለልምምድም አልመጣችም ከክፍሏ ሰራተኞች ተልከው ወደቤቷ ሲሄዱ ተደበቀች፡፡ ከጓደኛዋ ጋር ስስትወጣ አገኟት አለቃችን ጠርተውሻል ሲሏት ‹‹አልመጣም›› አለች፡፡ በኋላ ግን በጓደኞቿ ግፊት ወደ ሙዚቃ ክፍሉ ተመለሰች፡፡
ሽሽት
የመጀመሪያ ዘፈኗ ‹‹የሐር ሸረሪት›› የሚል ነው፣ ይሄን ዘፈን አጥንታ በ1952 ለዘመን መለወጫ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ፊት ቀረበች (ከዚያ በፊት በባዶ አዳራሽ ነው የሰራችው) ዘፈኗንም ብሔራዊ ትያትር ነው ያቀረበችው፣ አዳራሹ በሰው ታጭቋል፡፡ በወቅቱ ከሴቶች ብዙነሽ በቀለን የሚስተካከል ዘፋኝ አልነበረም፣ ጦር ሰራዊት ሂሩትን ሲያቀርብ በድምጿ መስረቅረቅና በአዘፋፈን ስታይሏ ተደነቁ፣ አዳራሹን የሞላው ተመልካች እየዘፈነች ሳለ በጭብጨባና በጩኸት አደመቀው አይን አፋሯ ሂሩት ደንግጣ ዘፈኑን ሳትጨርስ በሽሽት ወደ አዳራሹ ጀርባ ሮጠች፣ መንገዱም ሰለጠፋት የትራንፔት ተጨዋቹን ገፍትራ ጥላው ነው የሄደችው፡፡ ተመልካቹም እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞት ስለማያውቅ ጭብጨባውን አቋርጦ ተገረመ የጦር ሠራዊት የሙዚቃ ኃላፊዎችም ተደናገጡ፡፡
ድርድር
ሻለቃ አሽኔና ሌሎች ሰዎች ሂሩትን በአስቸኳይ ወደ መድረኩ ለመመለስ ማግባባት ጀመሩ ኦርኬስትራው ‹የሐር ሸረሪትን› በሙዚቃው እየተጫወተ ነው ሰዎቹም ሂሩትን ወደመድረክ ለማምጣት ማጣደፍ ጀመሩ፡፡
ሰዎቹ፡- ጉድ አደረግሽን! ተመለሽ
ሂሩት፡- አልመለስም
ሰዎቹ፡- ለምን
ሂሩት፡- አላውቅም
ሰዎቹ፡- መጥፎ የተናገረሽ ሰው አለ
ሂሩት፡- የለም
ሰዎቹ፡- ከቤተሰብሽ ወይም ከዘመዶችሽ የምትፈሪው ሰው ተመልካቹ ውስጥ አይተሻል
ሂሩት፡- አላየሁም
ሰዎቹ፡- ታዲያ ለምን ጥለሽ ወጣሽ
ሂሩ፡- ፈራሁ
ተንጋግተው የመጡት የጦር ሰራዊት ሰዎች ቢለምኗት እምቢ አለች፡፡ ከመህላቸው አንዱ ለማስገደድ ሂሩትን መጎተት ጀመረ፣ ሂሩትም ማልቀስ ጀመረች ነገር ግን ወደመድረኩ መመለስ አልቻለችም፡፡ አንዳንዶቹ እንደሚሉት ከሰዎቹ መሀል ነገሩ ያናደደው በመሳሪያ አስፈራርቶ ለማስገባት የሞከሩ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ሌሎች ደግሞ መሳሪያ ለሂሩት አልወጣም ይላሉ፡፡
አሰገደች መጣች
በእግር ከስ ውድድር ተጫዋች ሲጎዳ ወይም ሲደክም በሌላ ይተካል፣ በሙዚቃ ግን ዘፋኝ ሲደክም መቀየር ወይም በሌላ መተካት (በመድረክ ላይ) የተለመደ አይደለም ጦር ሰራዊትበሂሩት ዘፈን ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ በመሆኑ ያንን ውድድር ለማሸነፍ ሂሩት በር ከፍታለት ስለነበር እሷም በፍራቻ አልመጣም ስላለች የሐር ሸረሪት የተባለውን ዘፈን ሂሩት ጥላው ብትሄድም ኦርኬስትራው ሙዚቃውን እየተጫወተ ስለነበር በቶሎ አሰገደች ካሳን ወደመድረኩ ልከው እሷም ሂሩትን ተክታ፣ ሂሩትን መስላ፣ የሃር ሸረሪት የተባለውን ዘፈን ሂሩት ካቋረጠችበት ዘፍና ጨረሰች፡፡ ጦር ሰራዊትም አሰገደች እንደጨረሰች በሂሩት ድርጊት ይቅርታ ሊጠይቁ ፈልገው ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ህዝቡ በአንድ ዘፈን ሁለት ዘፋኝ ማጫወት አዲስ ስልት መስሎት አድናቆታቸው በጭብጨባ ገለጹ፡፡
ፍራቻን ለመጥፋት
ሂሩት ጎበዝ ዘፋኝ መሆኗን ጦር ሰራዊት ያውቃል ግን ፍራቻዋ አስቸገረው፡፡ ህዝቡን እንዳትፈራ ማለማመድ ጀመረ ከማለማመዱ ጋር አያይዞ ማስጠንቀቂያም ጭምር እያከሉ ‹‹ከእንግዲህ ከመድረክ ጥለሽ ብትወርጂ ሌላ ችግር ሊገጥምሽ ይችላል›› በሚል አስጠንቅቋት ፍራቻዋን ለማጥፋት ብዙ አለማመዷት፡፡
ሴት ዘፋኝ ያስፈልገናል
ፖሊስ አንድ ዘፋኝ ነው ያላቸው፣ መስፍን ሐይሌ ይባላል፣ ኦርኬስትራው ተደራጅ ግን ሴት ዘፋኝ የለውም አባላቶቹ ውይይት ማድረግ ጀመሩ አንዱ የሌላውን ሀሳብ ሲጥል ሲያነሳ ቆይተው ነበር፡፡
አንዱ፡- ሴት ዘፋኝ በጣም ያስፈልገናል
ሌላው፡- እከሌ ብትመጣስ (ስም እየጠቀሱ)
አንዱ፡- እሷ ለኛ አትመጥንም
ሌላው፡- ብዙነሽ በቀለን ብናመጣስ
አንዱ፡- እሷን ማግኘት ይከብዳል
ሌላው፡- ለምን
አንዱ፡- ጦር መማዘዝ ያስፈልጋል በዚያ ላይ የኛ ሃላፊ ጄኔራል ጽጌ ዲቡና የክቡር ዘበኛ ኃላፊ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ በጣም ስለሚቀራረቡ መቃቃር ይፈጠራል ስለዚህ የብዙነሽ ነገር ይቅር
ሌላው፡- ሂሩትን እናምጣት
አንዱ፡- እዚያም ቢሆን ከወቴ ጋር ግጭት ይፈጠራል፡፡
ከብዙ ውይይት በኋላ ‹‹ብዙነሽ ክቡር ዘበኛ ውስጥ ቆያታለች ታውቃለች ሂሩት፣ ግን አዲስ ነች ገና አልታወቀችም እሷን አምጥተን አብረን እንደግ በማለት ይስማማሉ ሂሩትን ለማምጣት ዝግጅት ያረጋሉ እሷን የሚወስዱት በዘረፋ መልክ ነው፡፡
እንጥለፍ
ሂሩትን ለማምጣት በኦርኬስትራው ይወሰንና ለበላይ አለቆች ይቀርባል፣ ይሁንታም ያገኛል፡፡ ነገሩ በጥንቃቄ ይከናወን ተብሎ መመሪያ ይተላለፋል፡፡ የጠለፋ ስራው ለፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ይሰጥና ሂሩት ያለችበት አካባቢ ይነገራቸዋል፣ አፍኖ በመጥለፍ ወደ ስውር ቦታ ለመውሰድ ውሳኔ ላይ ይደረሳል፡፡ ጠለፋው እንዴት ይካሄድ የሚለው ውይይት ተካሄደበት፡፡
አንዱ፡- እንዴት እናምጣት
ሌላው፡- በጠለፋ
አንዱ፡- ከየት እንጥለፋት
ሌላው፡- ከቤቷ ስትወጣ
አንዱ፡- ግን ከመጥለፋችን በፊት እናነጋግራት ያለበለዚያ ችግር ይፈጠራል፡፡
መቶ ብር እንስጥሽ
አቶ ተስፋዬ አበበ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የድርሰትና ዝግጅት ኃላፊ ናቸው፡፡ ሻለቃ ወርቅነህ ደመቀ የኦርኬስትራው ኃላፊና የመድረክ አስተዋዋቂ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች ሂሩት ጋር ይሄዱና ያናግሯታል፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደዚህ ይላሉ ‹‹ሂሩትን አንድ አሳቻ ቦታ ጠብቀን አነጋገርናት በሌላ ቀንም እንደዚሁ ቀጠሮ ይዘን ጉዳዩን አወያየናት ስናነጋግራት በጣም ፈርታ ነበር እሺም እምቢም አላለችም›› በማለት ይናገራሉ፡፡ እነ አቶ ተስፋዬ ከመሄዳቸው በፊት የሂሩት ጓደኛ ሌሎች ሰዎች እሷ (ሂሩት) ወደ ፖሊስ ካልገባች ችግር እንደሚፈጥሩባት ስለተነገራት ስጋት ላይ ነች የነሻለቃ ወርቅነህ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማግባባቱ ቀጥሏል፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደዚህ ይላሉ ‹‹ሂሩትም አወያየናት ጦር ሰራዊት 60 ብር ይከፍላታል እኛ 100 ብር እንስጥሽ አልናት፣ ከገንዘቡ ይልቅ ያስጨነቃት ሌላ ጉዳይ ነበር›› ይላሉ፡፡ ያነጋገሯትና ያለችበት ክፍል ሁለቱም ወታደሮች መሆናቸው ነው ያስጨነቃት
አንቺ ብቻ ተዘጋጂ
ሻለቃ ወርቅነህና አቶ ተስፋዬ ተስፉ ሳይቆርጡ ሂሩትን ማግባባትና ፍራቻዋን በማስወገድ በቁርጥ ሀሳብ ወደ እነሱ እንድትገባ ለማድረግ እየታገሉ ናቸው፡፡
ሂሩት:- ግን እዴት ከጦር ሰራዊት እለቃለሁ
ሻለቃ ወርቅነህ:- ችግር የለውም አንቺ ብቻ እሺ በይ
ሂሩት፡- ነገሩ በጣም ያስፈራል ጦር ሰራዊት ችግር ቢፈጥርስ
ሻ/ወርቅነህ፡- እነሱ ችግር እንዳይፈጥሩ እናደርጋለን
ሒሩት፡- በምን መንገድ
ሻ/ወርቅነህ፡- ከላይ አለቆች እንዲጨርሱ እናደርጋለን፡፡ ከላይ እንጨርሳለን የሚባለው ነገር ለሂሩት የሚያሳምን አልሆነም በተለይ በእናቷ ላይ የሆነ ችግር እንዳይፈጠር ስጋት ነበራት ማግባባቱ እንደቀጠለ ነው፡፡
ሂሩት፡- ጦር ሰራዊት ችግር ይፈጥርብኛል እንዴት አደርጋለሁ
አቶ ተስፋዬ፡- እሱን ለእኛ ተይው አንቺ ብቻ ለእናትሽ ንገሪ
ሂሩት፡- ምን ብዬ
አቶ ተስፋዬ፡- መሄዴ ነው ብለሽ
ሂሩት፡- የት ነው የምትወስዱኝ
አቶ ተስፋዬ፡- ለአንቺ የተዘጋጀ ቦታ አለ
ሂሩት፡- የት
አቶ ተስፋዬ፡- አንቺ ብቻ ተዘጋጂ ቦታውን ቀኑ ሲደርስ እንነግርሻለን፡፡
ጦር ሰራዊት ተስፋ አደረገ
በ1952 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በኣል ጦር ሰራዊት በውድድሩ ላይ የበላይነት ይዞ ለመጨረስ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ባለፈው የውድድር ዓመት ክቡር ዘበኛ ለጥቂት አሸነፋቸው፣ አሸናፊውንም የሚወስነው ህዝቡ ነው፣ ጦር ሰራዊት የተሻለ ነበር፡፡ ሂሩት እየዘፈነች ከመድረኩ ጥላ ስለሄደች ቅሬታ ቢፈጠርም ኦርኬስትራው ግን ጥሩ ነበር፣ በ1952 ዓ.ም ግን ጦር ሰራዊት ከክቡር ዘበኛ በእጅጉ ተሽሎ ለመቅረብ በሰፊው እተጋጀ ነው፣ አሁንም ትልቅ ተስፋ የጣለው በሂሩት ነው፡፡ ለሂሩት ሶስት ምርጥ ዘፈኖች አዘጋጅቷል፡፡ በዘፈኑ ብቻ ሳይሆን በአልባሳት ጭምር ‹አይነግቡ› ሆና እንድትቀርብ ፋሽኑን የጠበቀ ልብስ አሰፍተውላታል፡፡ በዘመኑ ፋሽኑን የጠበቀጸጉር ቤት እንድትሰራ ቦታውን አመቻችተውላታል፣ ሂሩትን የማድመቁ ሥራ ቀጥሏል፡፡ የሰራዊቱም አባላት በሷ ጥሩ ዝና እንደሚያገኙ እየተማመኑ ነው፣ ሂሩትን ጨምሮ ሌሎች የሙዚቃ ክፍል አባላት ከበላይ አካላት ሞራል ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለሂሩትም እንዳለፈው ጊዜ ጥሩ ዘፈን ተጫውታ ትልቅ ስም እንደምታስገኝላቸው ደጋግመው እየነገሯት ነው፡፡ እሷም ተስማማች ፖሊስ ደግሞ ከጀርባ ሌላ ሥራ እየሰራ ነው፡፡
ቶሎ እንስረቅ
ፖሊስ ቤት አንድ ወሬ ተናፈሰ ‹‹ጦር ሰራዊት ሂሩትን እያግባባናት እንደሆነ ወሬ ሰምቷል ውድድሩ እስኪያልቅ ሊደብቃት ይችላል፡፡ እኛ ቶሎ እንስረቅ›› ተብሎ ስለተፈራ በአስቸኳይ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ሂሩት የምትኖረው አራተኛ ክፍለ ጦር ጀርባ ጨርቆስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነበር፡፡ ጠለፋውን ለሚያካሂዱት ለፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አካባቢው ተነግሯቸዋል፡፡ መውጪያ መግቢያውም ተጠና፡፡ሂሩት ማታ ቤት መግባቷ ተረጋገጠ፡፡ አቶ ተስፋዬ አበበ እንዲህ ይላሉ፡፡፡ ‹‹ሂሩትን ሄደን አነጋገርናት ለሊት እንደምንመጣ አስጠንቅቀናት እናቷም እንዳይደነግጡ እንድትነግራቸው አረግናት የት እንደምንወስዳት ጠየቀችን በእጃችን እስከምናስገባት ድረስ ቦታውን አልነገርናትም፡፡ ምክንያቱም እስከለሊት ድረስ የት እንደምንወስዳት ከታወቀና፣ ለአንድ ሰው ብትነግር እንኳን ቦታውን እንዳያውቁ በሚል ነው እሷ ብቻ እንድትዘጋጅ ነገርናት ያን ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ የተባለው በጣም የተፈራ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ በድንገት ከታዩ ሰው ይደነግጣል እነሱን አስከትለን ሄድን፣ የያዙት ኡዚ ጠመንጃ ነው ከመኪና ወረዱና በር አንኳኩ
ፖሊስ፡- ሂሩት ማለት አንቺ ነሽ
ሂሩት፡- አዎን
ፖሊስ፡- ትፈለጊያለሽ
ሂሩት፡- ማን ነው የሚፈልገኝ
ፖሊስ፡- ዝም ብለሽ ከኛ ጋር ነይ
በዚያ ጨለማ ፈጥኖ ደራሽ ሂሩትን አንከብክቦ ወደመኪናው ያመጣል አቶ ተስፋዬ እንደዚህ ይላሉ ‹‹ፖሊሶቹ ኡዚ ደግነው ሂሩትን ሲወስዷት እናትየውበጣም ደነገጡ በወንጀል የምትፈለግ ነው የመሰላቸው ለማነጋገር ፈልገው ነበር ግን በአካባቢው ከቆየን ሌላ ችግር ስለሚፈጠር ቶሎ ይዘናት ሄድን››
አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ
‹‹ጦር ሰራዊት ፍለጋ ስለሚጀምር መከራከሪያ ስለሚያስፈልገን አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስደን በእለት ሁኔታ ላይ በወንጀል ትፈለጋለች በሚል እንዲሰፍር አደረግን›› ይላሉ አቶ ተስፋዬ፡ ጦር ሰራዊት ፍለጋ ጀመረ በጠቋሚ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄዱ ስሟ መዝገብ ላይ ተገኘ፣ ፈላጊዎቹ ፖሊሶቹን ማነጋገር ጀመሩ
ፈላጊ፡- ሂሩትን ልናነጋግራት ነው
ፖሊስ፡- እዚህ የለችም
ፈላጊ፡- ስሟ መዝገብ ላይ አለ
ፖሊስ፡- ሌላ ቦታ ተወስዳለች
ፈላጊ፡- የት ነው ያለችው
ፖሊስ፡- አናውቅም

ዙሪያ ጥበቃ
ጦር ሰራዊት ሂሩት ላይ ብዙ ለፍቷል ደክሟል፡፡ በሚገባም አዘጋጅቷታል፣ ልብስ አሰፍቶላታል ጸጉሯንም አሰርቷታል የመጨረሻ ቀን ደግሞ በደንብ ፊቷንና ጸጉሯን ያስውቡላታል፣ በሷ ተስፋ እያደረጉ ጥቂት ቀን ሲቀረው ተሰረቀች የጦር ሰራዊት ኮማንዶ ሂሩትን እንዲያስመልስ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ዝግጅት አድርጓል ያለችበትንም አውቀዋል፣ የተደበቀችው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ግቢ ውስጥ ነው በድንገት ስትመጣ ወይም ስትገባ ጠብቆ ለመያዝ ነው፣ ፖሊስም ይሄ እንደሚመጣ አውቆ ዙሪያውን በሚሊተሪ ፖሊስ በንቃት እያስጠበቀ ነው፣ ጦር ሰራዊት ደግሞ‹በጣራም ቢሆን ቀደን ገብተን እናመጣታለን› በሚል እየዛቱ ነው፡፡
ኒልሰን ማንዴላ
ጦር ሰራዊት ለመልሶ ጠለፋ እየተዘጋጀ ነው፣ ሲቪል ልብስ የለበሱ በአካባቢው ያንዣብባሉ አቶ ተስፋዬ እንደዚህ ይላሉ፡፡ ‹‹ፈጥኖ ደራሽ ግቢ ፖሊስ መኮንኖች ክበብ ይገኛል፡፡ እዚያ ወስደን አስገባናት ወደውጪ አትወጣም፣ እሷን ያቆየንበት ቦታ ተፈላጊ ሰዎችን አቆይቶ ለመጠበቅ አመቺ ነው እንዲያውም ከዚያ በኋላ ኒልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ከለላ ሲሰጠው እዚያ ክፍል ሆኖ እየተጠበቀ ነው የቆየው ሂሩትንም የደበቅናት ማንዴላ የመሸገበት ቤት ውስጥ ነው›› ይላሉ፡፡
ቦዲ ጋርድ
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ዘፋኞች በከፍተኛ ቦዲ ጋርድ የተጠበቀችውና ታጅባ የሄደችው ሂሩት ብቻ ነች፡፡ ደመወዟ 100 ብር ሆኖ በብዙ ሺህ ብር ዋጋ ባላቸው ጋርዶች ነበር የምትጠበቀው፡፡ ሂሩት ከተጠለፈች በኋላ በልዩ ጥበቃ ታጅባ ለውድድሩ እየተዘጋጀች ነው፡፡ ሁለት ምርጥ ዘፈን ተዘጋጅቶላታል፡፡ ‹‹ፍቅር የሰላም አክሊል ነች›› እና ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚሉ ዘፈኖች ለ1953 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ይዛ ትገባለች፡፡ በዚህ ውድድር የሚቀርቡት ፖሊስ፣ ጦር ሰራዊት፣ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያና፣ ብሔራዊ ቲያትር ናቸው፡፡ ውድድሩ የሚዘጋጀው ብሔራዊ ትያትር አዳራሽ ነው፡፡ ፖሊስ ሂሩትን እዴት ይዞ ወደ መድረኩ ይቀርባል የሚለው አነጋጋሪ ሆነ አቶ ተስፋዬ አንደዚህ ይላሉ ‹‹ጦር ሰራዊት ሂሩትን ካየ አንደሚነጥቀን እንገምታለን አራት ቦዲ ጋርድ አዘጋጀን እነዚህ ቦዲ ጋርዶች እስራኤል ሀገር ሰልጥነው የመጡና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖችን የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ሂሩት አካባቢ አንድ ጸጉረ ልውጥ ሰው ከመጣና አተኩሮ ካያት ችግር ውስጥ ይገባል›› ይላሉ
የግቢ ውስጥ አሰሳ
ፖሊስ ሂሩትን ለሳንሱር ያስመዘገበው በሌላ ሰው ስም ነው ይሄም ለጥንቃቄ ሲባል ነው፡፡ ለውድድር የሚቀርቡ ቡድኖች ግቢ ውስጥ ቦታ ቦታ ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ ተራቸው ሲደርስ ይገባሉ፡፡ አንዱ ሲጨርስ ሌላው ይተካል፡፡ ጦር ሠራዊት የወጠነው ዘዴ ግቢ ውስጥ እንይዛታለን በሚል ተዘጋጅቷል፡፡ ቀደም ሲልም ያዘጋጁላት ዘፈን ስላለ ካገኟት ከነሱ ጋር ሊያስገቧት አስበዋል፡፡ እዚህ ግቢ ውስጥ ግን ሁለቱም (ፖሊስና ጦር ሠራዊት) ሂሩት የኔ ነች በሚል ግጭት እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል መጀመሪያ ግን ጦር ሰራዊት ሂሩትን በእጁ ማስገባት አለበት፡፡ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ግቢ ውስጥ ቦታውን ይዞ እየጠበቀ ነው፡፡ ሲቪል የለበሱ የጦር ሰራዊት ሰዎች ግቢ ውስጥ ማሰስ ጀመሩ፡፡ በክበቡ፣ በቢሮው፣ በአሳቻ ቦታ ሳይቀር ፈለጓት ሂሩት ግን ግቢው ውስጥ የለችም፡፡
ከመድረክ ለመጥለፍ
ጦር ሰራዊት ግቢ ውስጥ ፈለጓት የለችም፣ ግን አንድ ቦታ ትገኛለች በሚል ይጠብቃል ሂሩት እንደምትዘፍን ስለተረዱ መድረክ ላይ ስትወጣ ለመጥለፍ ተዘጋጁ ክቡር ዘበኛ ሰርቶ ወርዶ ብሔራዊ ትያትር ቀጠለ እነሱም ሰርተው ጨረሱ የፖሊስ ተራ ደረሰ ሂሩት በቀለ የለችም ግን ትዘፍናለች እስካሁን አላያትም የፖሊስ መድረክ አስተዋዋቂው ሻለቃ ወርቅነህ ‹ተወዳጇና ተስረቅራቂ ድምጽ ያላት ሂሩት በቀለ ፍቅር የሰላም አክሊል ናት የተባለውን ዘፈን ታቀርባለች›› ብሎ አስተዋወቀ ጦር ሰራዊት ግቢ ውስጥ ፈልጎ ያጣትን ሂሩትን ከሰማይ ላይ ሊያመጧት ነው ብለው ይጠብቃሉ፡፡
እንዴት ትግባ
የጦር ሰራዊት መልስ ምት ሊመጣ እንደሚችል ፖሊስ ስለተረዳ ሂሩትን ከኦርኬስትራው ነጥሎ እያስጠበቃት ነበር፡፡ ከቡድኑ ጋር ከገባች ጦር ሰራዊት ይወስዳታል ስለዚህ ተሸፋፍና ገንዘብ ከፍላ ከህዝቡ ጋር ትግባ ተባለች፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደዚህ ይላሉ፡፡ ‹‹አራት ቦዲ ጋርድ እንዲያጅባት አረግን ቀድሞ ቦታ ስለተያዘ እሷ ተቀመጠችና ሁለቱ ጋርዶች ግራና ቀኝ ሁለቱ ደግሞ ፊትና ኋላ የኛ ተራ እስኪደርስ እየተጠበቀች ቁጭ አለች›› ይላሉ፡፡
የኮማንዶ ጥበቃ
ሂሩት ከህዝቡ መሐል ወጥታ ወደ መድረክ ለመዝፈን ስትሄድ ተመልካቹ ግራ ተጋባ ምክንያቱም ሁሉም ዘፋኝ ከመድረኩ ጀርባ ሲወጣ እሷ ግን በአጃቢ ወደ መድረኩ ሄደች አቶ ተስፋዬ እንደዚህ ይላሉ፡፡ ‹‹ሂሩት እየዘፈነችም ከመድረክ ላይ ሊወስዷት ስለሚችሉ ከጀርባ ወደ መድረክ መግቢያ አለ ያንን ቦታ በሚሊቴሪ ፖሊስ አዘጋነው ሂሩት ዘፈን ሳትጨርስ ማንም መግባት አይችልም ብለን አገድን አንዱ ድምጻዊ ሁለት ወይ ሶስት ዘፈን ይኖረዋል፡፡ አንዱን ዘፈን ካቀረበ በኋላ አራትና አምስት ዘፈኖች ዘፍነው ተመልሶ ይመጣል፡፡ ሂሩት ግን አንድ ላይ ዘፈኖቿን ጨረሰች›› ይላሉ፡፡
የት ትሂድ
ሂሩት የመድረክ ፍራቻ አለባት ባለፈው አመት ከጦር ሰራዊት ጋር ሆና ህዝቡ ሲያጨበጭብላት ተደናግጣ ዘፈኗን ጥላ ሄዳለች አሁንም ባቀረበቸው ዘፈን ጭብጨባና ከፍተኛ አድናቆት አገኘች ተደናግጣለች ግን ምን ታደርጋለች እንደበፊቱ ሸሽታ እንዳትሄድ ጦር ሰራዊት ይቀልባታል አሁን ካገኟ ደግሞ ችግር ነው ምክንያቱም ለፖሊስ አስጨብጭባለች እንደፈራች መሄጃ አጥታ ደንግጣ ቆመች የት ትሂድ?
መብራት ጠፋ
ሂሩት ያለችበት ታውቋል ጦር ሰራዊት ባዘጋጀው ኮማንዶ ለመልሶ ጠለፋ ይጠብቃል ይሄ እንደሚከሰት ፖሊስ ያውቃል ግን በየት በኩል ይዘዋት ይውጡ? መጀመሪያ ግርግር ፈጠሩ ሂሩትን የምትመስል በሌላ ሰው አሳጅበው ሊያስወጡ አዘጋጁ ያንን ጦር ሰራዊት ሲከታተል ሂሩትን ደብቀው ሊወስዷት ነው አቶ ተስፋዬ እንደዚህ ይላሉ ‹‹በሂሩት ፖሊስ ትልቅ አድናቆት አገኘ ሁላችንም ተደሰትን ግን በየት በኩል ይዘናት እንውጣ? መቼም ፖሊስ ጋር ዘዴ አይጠፋምና የኛ ሰዎች ከጀርባ ገብተው መብራት አጠፉ ‹‹ይቅርታ መብራት ኃይል ነው ያጠፋው ስልክ ደውለናል፡፡ ጥቂት ጠብቁ አልን በዚህ መሀል ጋርዶቹ ግርግዳ እየታከኩ ጨለማ ውስጥ በዋናው በር አድርገው ወጡ ያኔ ይሄን ሁሉ ያደረግነው በወቅቱ ለሙዚቃ ባለን ፍቅር ነው›› ይላሉ፡፡
ግብ ግብ
ሂሩት ስትወጣ በር ላይ ያያት አንድ ሰው ስሟን ጠርቶ ተጠጋት ግን አጠገቧ ሳይደርስ ጋርዶቹ መትተውት ጣሉት ምክንያቱም የጦር ሰራዊት ሰው ነው በሚል ነበር፡፡ ጋርዶቹ እሷን አንከብክበው ወደ ውጪ ሲወጡ ወዲያውኑ መሳሪያ በፓትሮል መኪና ላይ ጠምዶ የነበረ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አንከብክቦ መኪና ላይ ካወጣት በኋላ እያቆራረጡ ወደ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ ይዘዋት ሄዱ፣ በሩ ላይ የተመታው ሰው ግን የጦር ሰራዊት አባል ሳይሆን ለአድናቆት ሰላምታ ሊሰጣት የመጣ ሰው ነበር፡፡ መብራቱ እንደበራ የጦር ሰራዊት ኮማንዶዎች ሂሩትን ፈለጓት እሷ ግን አልነበረችም፡፡
በሂሩት ሰበብ ጥላሁን
ጦር ሰራዊት በመሰረቁና በመበለጡ ቅር ተሰኘ፡፡ ይሄ የፖሊስ ስራ ሳይሆን ክ/ዘበኛ እኛን ለመብለጥ ጥሩ ዘፋኛችንን አስወስዷል በሚል ታመነ፡፡ ጦር ሰራዊት ግቢ ውስጥ ምክክር ተጀመረ ክ/ዘበኛ ከኛ ሂሩትን ካስወሰደ እኛ ለምን ጥላሁንን አንወስድም የሚል ጥንሰሳ ተጀመረ፡፡ ጥላሁንንም ማግባባት ተጀመረ ነገር ግን ከጥቂት ወራት በኋላ ጄኔራል መንግስቱ የመሩት መፈንቅለ መንግስት ተካሄደና ጦር ሰራዊትና ክ/ዘበኛ የከረረ መቃቃር ውስጥ ገቡ ጥላሁንም ‹‹ውሃ ባንድ ኮዳ;; በሚል ዘፍኖ ጦር ሰራዊትና ክቡር ዘበኛ ያላቸውን መቃቃር ይባስ አሰፋው፡፡
የሂሩት ገቢና
የፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ አባላት ሂሩትን ለብዙ ጊዜ እያስጠበቀ ቆየ የእሱ እንደሆነች ሲያውቅ ወደቤቷ መለሳት፡፡ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ አባላትን የሚያመላልስ መኪና አለ፣ ጥዋት ከቤታቸው ያመጣቸዋል ማታ ይመልሳቸዋል፡፡ መኪናው የጭነት ነው ብዙዎቹ እላይ ወጥተው ነው የሚሄዱት ገቢውና ሁለት ሰው ብቻ ነው የሚይዘው ያን ቦታ ሂሩትና አቶ ተስፋዬ አበበ ብቻ ናቸው የሚቀመጡት ሂሩት ጋቢና የምትገባው ለክብሯ ብቻ ሳይሆን ከጠለፋም ለመጠበቅ ነው፡
