“በዓድዋ እና በዓድዋችን ዋዜማ፤ የሁለት ውኃዎች ዐብይ ስትራቴጂ

በጋዜጠኛ መሀመድ ሀሰን (የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ)

እንኳን ለዛሬው ዓድዋ በሰላም አደረሳችሁ!

ቀኑን ተሳስቼ፣ የዐርበኛ እናቶቻችንና አባቶቻችንን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ቅዳሜ መሆኑን ዘንግቼ አይደለም፤ የኛን ዓድዋ አሰልቼ ነው። እጅጋየሁ ሽባባው ምስክር ናት! ትናንት ብቻም አይደለችም፣ ዓድዋ ዛሬም ናት! እንኳን አደረሰን!

ለ“ሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” ምርቃት የዛሬው ቀን እንዲሁ አልተመረጠም። በምክንያት የሚሰራ እና የሚራመድ ትውልድ ነንና መጽሐፉን በዛሬው እለት ለመመረቅ ማሰባችን፣ ለዓድዋችን በሰሞነ ዓድዋ የሰነድ መሰረት ለመጣል ነው። የቀደመውን የዓድዋ ድል እንኮራበታለን፤ ነገር ግን መኩራት እና መዘከር ብቻ ግን አይበቃም የበለጠ መመርመር፣ የበለጠ ማወቅ፣ ከዚያም የራሳችንን ዓድዋ ማዋጣት ግድ ነው! ያለዚያ እንደ ልጁ እንሆናለን።

ልጁ የታዋቂና የምሁር አካውንታንት ልጅ ነው። አባቱ የሂሳብ ስራ ሊቅ በመሆኑ የተነሳ የሱን ስም እየጠራ፣ ብዙ እድል እየተከፈተለት ለአቅመ ስራ ደረሰ። ስራ ሊቀጠር ፈተና ቀርቦ፣
ምን ትችላለህ ሲባል?
አባቴ ምሁር ነበር። ሲል
ምን ተምረሃል? ሲባል
አባቴ ፒኤች ዲ አለው ሲል፣
የስራ ልምድህ ሲባል?
አባቴ 10 ባንኮች መርቷል ሲል… ፈታኙ
“አንተ ፈተናውን ስለወደክ፣ ወደ ቤትህ ሂድ፣ አባትህ ግን ስላለፉ፣ ነገ መጥተው ስራ እንዲጀምሩ ንገራቸው!” እንደተባለው፣ ታላቁን ድላችንን በመዘከር ብቻ ካቆምን፣ የኛን ፈተና አባቶቻችሁ ተነስተው ይፈተኑላችሁ እንዳንባል፣ የገዛ ዓድዋችንን መስራት ግድ ነው።

እኛ በአባቶቻችን እንደኮራን፣ ልጆቻችን በእኛ መኩራት ይገባቸዋል። ለዚያም ነው፣ ከዚያን ጊዜው ዓድዋ፣ ወደ ዛሬው ዓድዋ መሻገር ያለብን።

ዓድዋ 2፣ የእኛ ዓድዋ ነው! ዓድዋ 2፣ የዛሬ ጉዳያችን ነው! ዓድዋችን፣ የአባቶቻችን ዓድዋ ተከታይ ነው! ዛሬ የገጠመን ፍልሚያ፣ ከቀደመው ዓድዋ ጋር የተያያዘ ነው! ለዚያ ነው፣ ዓድዋ አልተጠናቀቀም የምለው! የቀደመውን ለማስጠበቅም፣ ሙሉ ለማድረግም፣ የእኛን ዓድዋ ማጠናቀቅ ግዴታ ነው!

ዛሬ ይኸው ተጀምሯል! መሰረቱ ተጥሏል! ተባብረን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንጨርሰው። ዓድዋ 1 ሙሉ የሚሆነው፣ ዓድዋችንን ጨርሰን ስናስመርቅ ነው! እንደምናሳካው አልጠራጠርም!
የሁለቱ ውሀዎች ጉዳይ የምናውቀው የሚመስለን ግን ዝርዝሩን ጠልቀን የማናውቀው ጉዳይ ነው። ስለዓባይም ሆነ ቀይባህር በልብ ወለድ ድርሰቶች፣ በሙዚቃ፣ በተረትና ምሳሌ፣ ለዘመናት ብናነሳም፣ ብንቆጭም፣ ብንናፍቅም፣ ብንጠይቅም፣ ትክክለኛ ዋጋቸውን ተረድተን ነበር ለማለት አስቸጋሪ ይመስለኛል።

እንፈልጋቸዋለን ግን የምንፈልጋቸውን ለምን እንደሚያስፈልጉን ተንትነን አልተገነዘብንም። ድንገት ጥያቄ ቢነሳን መልሳችን እንደዚያች ሴት የሚሆን ይመስለኛል።

ሴትየዋ ለባሏ ሁሌ አሳ ጠብሳ ስታቀርብለት ጭራውን ቆርጣ ነው። በተደጋጋሚ ጭራው የተቆረጠ አሳ ስታቀርብለት ያየው ባለቤቷ፣ ለምን እንደምትቆርጠው ሲጠይቃት
«እናቴ ስትቆርጥ አይቼ ነው» አለችው። ምክንያቱ ስላጓጓው እናቷ ጋር ደወለ። እናትየውም “እኔም እናቴ ስትቆርጥ አይቼ ነው” አሉ ። አያት ጋር ተደወለላቸው።
«ለምንድነው የአሳውን ጭራ የሚቆርጡት?» ሲባሉ…
የነበረችኝ መጥበሻ ትንሽዬ ስለሆነች ለመጥበስ ስለማትበቃኝ ነው ቆርጬ የማቀርበው አሉ።

አንድ ትውልድ በችግር ምክንያት ያመጣው መፍትሄ ጠያቂና አሳቢ ትውልድ ካልተፈጠረ ሙያ መስሎ ይኖራል። የሚያስፈልጉን ለምን እንደሚያስፈልጉን፣ የተውናቸውን ለምን እንደተውናቸው ተንትነን ካልተረዳን ወደፊት መራመድ አንችልም። ስለዚህ የወረስናቸውን ድሎች፣ ፈተናዎች፣ እድሎች፣ ሽንፈቶች፣ ጥያቄዎችና መልሶች ሁሉ መርምረንና ተረድተን ካልተቀበልን የኛን አሻራ ለማኖርም ሆነ የኛን ፈተና ለመሻገር አንችልም።

ለዚያ ነው በዓባይም ሆነ በቀይባህር በኩል እንደሀገር ትልቅ እርምጃ ስንራመድ፣ ቀድመው በኪነጥበብም ሆነ በስነጽሁፍ ሲናፍቁና ሲያስናፍቁን የኖሩት አንዳንድ ደራሲያንና ከያኒያን ድምጻቸው የሚጠፋው ብሎም ለተቃውሞ የሚነሱት። ለዚያ ነው ያኔ አጣን ብለው ያላቀሱን፣ ዛሬ አገኘን ስንል የሚከሱን።

በመሆኑም፣ ስሜት-መር ከሆኑ ምኞቶችና ናፍቆቶች አንድ እርምጃ ተራምደን፣ አንገብጋቢ ጥያቄዎቻችንን በአግባቡ ሰንደን ማኖር ይገባናል። የሁለቱን ውሃዎችም ጉዳይ፤ ልሂቃን እንዲወያዩበት፣ አጥኚዎች እንዲያዳብሩት፣ ዲፕሎማቶች እንዲሟገቱበት መምህራን እንዲያስተምሩበት፣ ትውልዱ በእውቀት እንዲቆጭበት… ዐቢይ ስትራቴጂ ማዘጋጀት ተገቢ ነበር። ይህ መጽሐፍም የተዘጋጀው በዚህና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች ነው። ይህም ለትውልዳችን ዓድዋ ወሳኝ መሰረት ነው።

እንደ አጋጣሚ ከ3 ቀን በፊት ከውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ጋር በቢሯቸው ቁጭ ብለን በውሃ ላይ በደንብ አወጋን… በእውቀትና በንቃት እየተሰራ መሆኑን አየሁ… በጣም ተደሰትኩ…። የመጀመሪያውና የጎደለን የሚያስፈልገንን በጥልቀት ማወቅ ስለሆነ።

ዛሬ የምናነሳው ጉዳይ የሰብዓዊ ህልውናችን መስረት የውሃ በመሆኑ ከውሃም የሀገራዊ ኅልውናችን መሰረት ስለሆኑ ሁለት ውሃዎች ነውና፥ አይመለከተኝም ሊል የሚችል አንድም ዜጋ የለም፡፡ ማንኛውም የማንነትና የአስተሳሰብ ልዩነት በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ አይመለከተኝም ብሎ ዝም ለማለት የሚያበቃ ሰበብ አይደለም። በጨውና በንፁህ ውሃ አስፈላጊነት ላይ መንግስትንም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ዓድዋ ድል በአንድ ወገን ከመቆም ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም። ምክንያቱም ይህ የኢትዮጵያ ጥቅም ነው።

እርግጥ፣ ትልቁ ጥቅማችን ባለበት ሁሉ፣ ከባዱ ጩኸትም ይኖራል! ኢትዮጵያ ትልቅ ስራ ለመስራት፣ ትልቅ እርምጃ ለመራመድ በተነሳች ቁጥር እጅግ ብርቱ ተቃውሞና እጅግ ብርቱ ፈተና ይገጥማታል።

የጥንቶቹን ትቼ፣ የቅርብ ጊዜዎቹን ብቻ ላንሳ።
የታላቁን ህዳሴ ግድብ መገንባት ኢትዮጵያን በብዙ መንገድ ይቀይራል። ግድቡ ለልጆቿ ስራ ነው። ለዜጎቿ መብራት እና ኃይል ነው። መብራቱ አገር ከመጥቀም አልፎ ለጎረቤቶች ተሽጦ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል። ከአካባቢው አገራት እና ህዝቦች ጋር ያለንን ትስስር ያጠናክራል፤ ኢትዮጵያን ያበለጽጋል፣ በትልቁ ያራምዳል… ብለን ተነሳን። ግን ትልቁ ጥቅማችን ባለበት ትልቅ ጩኸት አለ፤ ግድቡን ስንገነባ፣ ከግራ ከቀኝ ተነሱብን!
ብድር ተከለከልን!
ግብጽ ፎከረች!
ሱዳን ተቃወመች! አሜሪካ፣ ኢትዮጵያን ደብድቡ አለች። አገራችን ተከሳ፣ መንግስታቱ ደርጅት ፊት ቀረበች!
ሚኒስትራችን ተከሰው ቀረቡ።

አንድ ሺሕ ድርደር ተደረገ። ከሳሾቻችን ለያዥ፣ ለገናዥ አስቸገሩ!
ቀጠልንና ሀገራችንን አረንጓዴ እናልብሳት ብለን ተነሳን። አረንጓዴ ልማታችን፣ ኢትዮጵያን ይለውጣል። አሳሳቢውን የከባቢ አየር ብልሽት ያክማል። አገራችንን ብቻ ሳይሆን፣ አካባቢያችንን፣ ከኢትዮጵያም አልፎ ዓለምን ይጠቅማል። እሱም እንደ ግድቡ ለልጆቻችን ስራ ነው። ለህዝባችን አረንጓዴ ሀብት ነው፣ ትልቅ ምንዳ ነው… ብለን ተነሳን።

ግን ትልቅ ምንዳችን ባለበት ግን ኃይለኛ ተቃውሞ አለ። ኢትዮጵያ መናፈሻ ቸገራት ወይ? ተባለ! ዛፍ ዳቦ ነው እንዴ እስከዚህ ተባለ! በአረንጓዴ ቅጠል ምትክ፣ ነጭ እንጀራ ስጡን ተባለ። ገበታ፣ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ የሌማት ትሩፋት፣ ሁሉም ትላልቆቹ እርምጃዎቻችን፣ ታላላቅ የተቃውሞ አሸን ፈላባቸው። በመጨረሻስ ምን ሆነ?

ትላልቅ ተቃውሞዎች የተነሱበት፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እነሆ እያለቀ ነው። ልክ ንደታሰበው፣ ለልጆቻችን ስራ፣ ለአገራችን ሀብት፣ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እየሆነ ነው። ያ ሁሉ ተቃውሞ የተነሳበት፣ አረንጓዴ ልማታችን፣ በርካታ ቢሊዮን ዛፎችን ለዓለም አበርክቶ፣ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ለሽልማት አብቅቶ፣ ልምዱ በሌሎችም አገራት አረንጓዴ ዘመቻዎች እየወለደ ነው። ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ የበጋ ስንዴ እና የመሳሰሉት አገራችንን እየለወጧት ነው!

አሁን ተራው፣ የውሀ እና የባህር በር ጉዳይ ሆኗል። ኢትዮጵያ፣ ውሀዎቿን ብትጠቀም እና የባህር በር ብታገኝ፣ ታድጋለች፣ በኃይለኛው ትጠቀማለች። ኃይለኛ ጥቅማችን ባለበት ደግሞ፣ እንደተለመደው ኃያል ጩኸት ይኖራል። ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿን ልትወር ነው እየተባለ ነው። ከሶማሌ ጋር ጦርነት ከፈተች እየተባለ ነው። እነ እንትና እየፎከሩ ነው!

እነ እንቶኔ፣ ፉከራውን እያስተጋቡ ነው። ጥቅማችን ባለበት፣ ጩኸታቸው ይኖራል። እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ እንደ አረንጓዴው አሻራ፣ እንደ በጋው ስንዴ፣ ህልማችንን አሳክተን፣ የኢትዮጵያ እርምጃ ይቀጥላል፡፡
ጪኸቱ ይኖራል፣ እርምጃችን ግን አይቆምም!
ይቀጥላል… !

ከላይ ስነሳ ይህ ዓድዋ ቁጥር ሁለት ነው ብዬ ነበር። የሁለቱ ውሃ ጉዳይ በዓድዋ ዋዜማ መነሳቱ በምክንያት ነው። ምክንያቱም የትናንቱን ድል ስንመረምረው የምንደርሰው ወደዛው እውነት ነውና። ድል ያደረግነው ጠላት የመጣብን ለውሃና በውሃ በኩል ነበር። የትናንት ማሸነፋችን የድሉ ጅማሬ እንጂ ማጠናቀቂያው አልነበረም። የዛሬው ዓድዋችን የትናንቱ ቅጥያ ነውና፣ የድሉ ፍፃሜ ነው። የቀደመውን ለማስጠበቅና ሙሉ ለማድረግም ለዛሬውን ዓድዋችን መሰረት መጣል ግዴታ ነው።

ስለዚህ በአንድነት መቆምና መተባበር ይገባናል። ዓድዋ ህብረት ነውና፣ ዓድዋ የበኩሉን ማዋጣት ነውና፣ ዓድዋ ልዩነትን ትቶ ለወል አጀንዳ መቆም ነውና በሁለቱ ውሃዎች ጉዳይ በአንድ ልብ ሆነን ለዐቢይ ስትራቴጂው ተግባራዊነት እንድንጋደል አደራ እላለሁ!

ስለዚህ አቅማችሁ የፈቀደ ሁሉ ዓላማችንን ተረድታችሁ አግዙን፡፡ መጽሐፉም በመቶ ሺዎች መታተም ያለበት የዘመኑ የትውልዱ ስንቅ ነውና በድጋሚ አደራ እላለሁ፡፡ እኛም እንደተቋም አደራውን በስያሜያችን ተቀብለናል።

አዲስ ዋልታ የአንድ ተቋም ስም አይደለም። የአዲሱ ትውልድ ራዕይ ነው። የአዲሱ ትውልድ ህብረት ነው። የአዲሱ ትውልድ መገለጫ ነው። ተቋማችን በዓድዋ መንፈስ ያምናልና፣ በዚህ ሰነድ ውስጥ በመሳተፋችን ራሳችንን እንደ እድለኞች እንቆጥራለን። ምክንያቱም “ለኢትዮጵያ በአፍሪካ አድማስ” ያልነውን የተቋማችንን መሪ ቃል በተግባር የገለጥንበትና ከተቋምና ከሀገር የተሻገረ አሻራ ለማኖር የታደልንበት ጭምር በመሆኑ ነው። በቀጣይም በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሌሎችን ጨምረን የምንሰራ መሆኑን እገልፃለሁ።

በመጨረሻም የዘመኑን ዓድዋ የምንፋለምበት ዋንኛው ግንባር ሚዲያ እንደመሆኑ፣ ለሚዲያዎችና ለወዳጆቼ የሚዲያ ኃላፊዎች እንደሁሌው ዛሬም በጋራ እንድንቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ። በተለይ እንደዛሬው ባለው ጉዳይ ከዓርማና ከስም የዘለለ ልዩነት የለንምና፣ ኑ ሁላችሁም ተቀላቀሉና እናፈርጥመው። በያዝነው መሳሪያ ተቋም አቅም ልክ ከሀገር ሰፈር መንደር ተሻግረን አጥር እንነቅንቅ በዓለም አደባባይ እንታይ፣ እንፋለም። ዓድዋ የጋራ ነው፤ ሳንጠባበቅ በህብረት እናዳብረው፣ እናጠናክረው፣ እንሞክርበት ባለቤት ሁኑ ብለን ጀምረናል፡፡ ቀጥሉበት… የሁሉም ኃላፊነት ነውና፡፡

አመሰግናለሁ! እንኳን አደረሳችሁ!

መሀመድ ሀሰን፣ የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories