የኢትዮጵያ የዉጭ ግንኙነት
መንደርደሪያ
የኢትዮጵያ የዉጭ ግንኙነት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከእየሩሳሌም ከህንድ ከቻይናና ከፋርስ (ወይም ከዛሬዋ ኢራን) ጋር ሲካሄድ የነበረ ነው። የኢትዮጵያን የቆየ ግንኙነት ለማየት ከ1521 አመቶች በፊት ነብዩ ሞሃምመድ ተከታዮቻቸው በችግር ላይ በነበሩበት ሰአት ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ማለታቸው ትልቅ ምስክር ነው። ከተራ ፖለቲካ ባለፈም ኢትዮጵያ የፍትህ ሃገር መሆኑዋን የመጀመሪያዎቹን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተቀብላ ህይማኖቱን ለማጥፋት ከተነሱ ሃይሎች ተከላክላ አድናለች። ብዙዎች የማያዉቁትና በጣም አስደናቂው ግን በኢትዮጵያና በዘመኑ የሃያሎች ሁሉ ሃያል በነበረችው በፖርቱጋል መካከል የተመሰረተው የመጀመሪያው ግንኙነትና ከዚያም አልፎ በአለማችን የመጀመሪያ የጦር ትብብር ነው። ይህም ገና እንዳሁኑ አሜሪካ ገና ሳትመሰረትና አፍሪካዉያን በባሪያ አሳዳሪ ባእዳን አስተዳደር ዉስጥ ሳይገቡ በ16 ክፍለ ዘመን ነበር:: ይህ የመጀመሪያው በሁለት ክፍለ አለማት መካከል የተመሰረተው ግንኙነት እስከ የጦር ትብብር የደረሰና የሃያሉን የኦቶማንን የግዛትና የሃይማኖት መስፋፋት አላማን የሰበረ ነው።
ሌላው አስገራሚ ነገር ፖርቱጋሎች ይዘዉት የመጡት የዘመኑ የመጀመሪያው መተኮሻ መሳሪያ ወይም ጠብመንጃ/ራይፍል (Rifle) ጥቂት በመሆኑና ግማሹም ክርስቶፈር ዳጋማም የመጀመሪያዉን ዉጊያ ሲያደርግ በመዘረፉ ኢትዮጵያዉያንና ፖርቱጋሎች በመተባበር ጠብ መንጃን ኢትዮጵያ ዉስጥ መስራትና ማባዛታቸው ታዉቆአል። ለዚህም ይሆናል ኢትዮጵያዉያን የመሳሪያውን ስም ጠብ መንጃ (የተጣላን ሰው ማባረሪያ) ብለው ስም ያወጡለት። አንዳንድ ሰዎች ግን ባለማወቅም ይሁን በሌላ ምክንያት ስሙን ያወጡትለት ፖርቱጋሎች ናቸው በማለት ብዥታን ይፈጥራሉ። ያው እንደተለመደው ላሊበላን የሰሩት አሮፓዉያን ናቸው እንደሚሉት የተዛባ ታሪክ እንዳይሆን ታሪክን ከስሩ መቅዳት አለብን!
በሀገሮች መካከል የመጀመሪያው የዘመነ ግንኙነት የተፈጠረው 1799 ሲሆን ኢትዮጵያው አለክሳንደር ፑሽኪን ሞስኮው ዉስጥ የተወለደው እኤአ በ1798 ነው። በሩሲያና በኢትዮጵያ መካከል ደሞ ዘመናዊ ግንኙነት የተመሰረተ ነው በ18ኛው ክፍለዘመን ነው።ይህ የሚያስተምረን ታሪክ እራሱን ስለ ሚደግምና ዲፕሎማቶች ታሪክን ካላወቁ ከሌሎች ሃገሮች ጋር ጥሩ መወዳጀትን ለመፍጠር እንደሚቸገሩ ነው። ወደፊት በዚህ ሃሳብ እንደምናየው ኢትዮጵያ የብዙ ሃገሮችን ልብና አስተሳሰብ የሚማርኩ ቀደም ሲል የተሰሩ መሰረቶች አሉአት::
የኢትዮጵያና የእንግሊዝ መንግስት ግንኙነት በንግስት ቪክቶሪያና በአጼ ቴዎድሮስ ዘመንም የነበረ ቢሆንም በደንብ ቅርጽ ይዞ የተመሰረተው በአጼ ምኒልክ ዘመን ነው። የአጼ ተዎድሮስ ልጅ (የልዑል አለማየሁ) ሃዉልትም ለማስታወሻ ያህል እዚሁ እንግሊዝ ሃገር ዉስጥ ይገኛል::
በ1902 አ/ም በራስ መኮንን ወልደሚካል የተመራው የመልእክተኞች ቡድን በለንደን
እንደ እኤአ በ1902 አጼ ምኒልክ በራስ መኮንን ወልደሚካኤል (የአጼ ሃይለስላሴ አባት) የሚመራ መልእክተኛ የኤድዋርድ ፯ኛውን ዘዉድ መድፋት ለመሳተፍ ለንደ መጥተው ነበር። ከራስ መኮንንጋር ፭ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መልእክተኞች መጥተው ነበር:: እነሱም:-
ፊታዉራሪ ሃይለስላሴ ዓባይደር
ከንቲማ ገብረዎልድ ደስታ
መምህር ገብረ እግዚአብሄር
ፊታዉራሪ አባታቦርና
ሚካኤል ብሩ ናቸው።
ራስ መኮንን ለንደን እንደገቡ የኤድዋርድ ፯ኛዉን መታመምና በዚያም የተነሳ የዘዉድ መድፋቱ ስነስርአት መተላለፉን እንዳወቁ ወደ ዌስት ሚንስተር አቤይ (ገዳም) በመሄድ ለጤንነታቸው ጸልየዉ የወርቅ መስቀል ስጦታም አበርክተዉላቸዋል። ራስ መኮንንና መልእክተኞቹ የአጼ ተዎድሮስን ልጅ የልኡል ዓለማየሁን መቃብርም ከመጎብኘታቸውም በላይ ከእንግሊዝ በተጨማሪ ፈረንሳይን ጀርመንን ጣሊያንን እና ቱርክን በመጎብኘት በኢትዮጵያና በነዚህ አገሮች መካከል ከፍተኛ መቀራረብን ፈጥረዋል። ንጉሰ ነገስት ኤድዋርድ ፯ኛ ከ፲፻፱፻፪ እስከ ፻፱፻፲ ድረስ የታላቁዋ ብሪታኒያና የህንድ ንጉስ ነበሩ።
ይህ የረጅም ዘመን ግንኙነት በአጼ ሃይለስላሴና በንግስት አልሳቤት ዘመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ንግስት ኤልሳቤት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴም በይፋ እንግሊዝን ከመጎብኘታቸውም በላይ በፋሽት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜ ንጉሰ ነገስቱ መኖሪያቸውን ለንደን በማድረግ በጄነቫና በሌሎች ሃገሮች በመዘዋረር በመጨረሻም ከእንግልዝ መንግስት ጋር ግምባር ፈጥረው የጣሊያን ጦር ከአፍሪካ ተጠራርጎ እንዲወጣ አድርገዋል። በፋሽት ወረራ ዘመን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ተሰልፈው የፋሽስቶችን ግፍ ለአለም በማሳወቅ ሲልቪያ ፓንክህርስት ትልቅ ሚና ተጫዉተዋል። ልጃቸው ሪቻርድ ባንክረስትና ቤተሰባቸው በሙሉ የኢትዮጵያን እዉነተና ታሪክ ሳይዛባ ለዓለም በማሳዎቅም ጭምር ባለዉለታ ናቸው።
ይሁን እንጂ በደርግና በወያኔ ዘመን ይሕንን የቆየ ግንኙነት ከማጠንከር ይልቅ አንዳንድ እፍራሽ ድርጊቶች በሁለቱም ሃገሮች በኩል ታይተዋል። በተለይ ወያኔ በኢትዮጵያ ስም ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ግንኙነቱን በሁለቱ ህዝቦች መካከል ከማድረግ ይልቅ ነገድን የተከተለ አድርጎታል።
በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዘር ማጥፋት የፈጸመዉን መለስ ዜናዊዉን አግኖ ፋዉንዴሽን መንገዶችን እና ህንጻዎችን በስሙ ለመሰየም የተደረጉት ጥረቶች በለንደን ኢትዮጵያዉያን ሊከሽፍ ችሎአል። በቅርቡም ወያኔ የኢትዮጵያን መከላከያ ጦር ወሮ በመላው ኢትዮጵያ ላይ ክህደት ሲፈጽም አንዳንድ የእንግሊዝ የፓርላማ አባል ነን የሚሉ ሰዎች “ትግሬ ነጻ ከወጣች የእንግሊዝ መንግስት ይወቃት” የሚል እጅግ አደገኛና የሁለቱን ወዳጅ ሃገሮች ግንኙንት አደጋ ላይ የሚጥል ሕገወጥ የሆነ ፕሮፓጋንዳ በትዩተርና በሌሎች የህዝብ መህገኛኛ አዉታሮች ሲያስተጋቡ በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ግለሰቦች በሁለቱ አገሮች መካከል ለዥም ጊዜ የቆየው ግንኙነት በጥቂት ታሪክን በማያዉቁ ሰዎች እንዳይበላሽ ትግል አድርገው ይህንን አደገኛ ተንኮል አክሽፈዋል። ለዚህ ነው ታሪክን ማወቅ ለዉጭ ግንኙነት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው የምንለው። እዚህ ላይ ማጤን ያለብን አምባሳደር ተብለው በየሃገሩ ከተቀመጡት ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋዮች በላይ በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባሎች የሃገራቸውን ጥቅምና ደህንነት ለመጥበቅ በበጎ ፈቃዳቸው መስራት እንደሚችሉ ነው። አሁን ባለንበት የዉስጥ መረብ ዘመን የኢምባሴዎች አስፈላጊነትም እየደበዘዘ በመሄድ ላይ ነው።
ዲፕሎማስይ ምንድነው?
ዲፕሎማስይ የሚለው ቃል ከግሪክ የተገኘ ነው። “ዲፕሎ” ማለት የታጠፈ የተደረበ ሲሆን “ማ” ደሞ ወረቀት ወይም ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል። ዲፕሎማሲይ የመደራርደርና የአገሮችን ግንኙነት በሰላም ተግባብቶ የመጠበቅ የጥበብ ሙያ ነው።
የዲፕሎማሲይ ግንኙነት የተለያየ ትርጉም ወይም ፍቺ ቢኖረዉም ሁሉም የሚስማሙበት (The art of dealing with people in a sensitive and tactful way) ዲፕሎማሲይ በሰዎች መካከል ያሉ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸዉን ጉዳዮችን በጥበብ መያዝ ነው። አንድ ዲፕሎማት በእዉቀት የላቀ ግርማ ሞገስ ያለውና ሃገር ወዳድ ከሆነ እራሱንም ሆነ የወከለዉን ህዝብ ያስከብራል::
የዲፕሎማስይ ጥቅም
የእንደራሴ ጽ/ቤትን (ኢምባሲይ) መክፈትና መልእክተኞችን (ዲፕሎማትን) የመሾም ዋናው አላማ ከሌሎች ሃገሮች ጋር ለመግባባት ለመወዳጀት ለመደራደር ዉሳኔዎችን ወደ ራስ ጥቅም ለማምጣት አጨቃጫቂ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የሃይል እርምጃ ከመዉሰድ ለመቆጠብና ነገሮች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ ነው።
በሃገሮች መካከል ለሚደረጉ ግንኙነቶች ጠቃሚ የዲፕሎማስይ መመሪያዎች
- ብሄራዊ ጥቅምን ማስቀደም
- አሳማኝ መሆን
- ነገሮችን ገልጾ ማስረዳት መቻል
- ነገሮችን በስፋትና በጥልቀት ማየት
- ሌሎች የሚሉትን በጥንቃቄ ማዳመጥና መረዳት
- ነቅቶ ነገሮችን ማስተዋልና መከታተል መቻል
- ችግሮችን በራስ ተማምኖና ጸንቶ መቁአቁዋም ናቸው።