በጥበቡ በለጠ
2006 ዓ.ም በሰንደቅ ጋዜጣ የታተመ
ነብዩ መሐመድ ለተከታዮቻቸው እንዲህ አሉ፡፡- “ወደ ሐበሻ ብትሄዱ በርሱ ጥላ ከለላ ሥር ያሉ ሰዎች የማይሰደዱበት ንጉሥ ታገኛላችሁ፡፡ የጽድቅ አገር ናት ስለዚህም እግዚአብሔር ከጭንቃችሁ ይታደጋችኋል፡፡”
ነብዩ፣ ሐበሻ እያሉ የጠሯትን አገር እኛ ልናጣጥለው አይገባም፡፡
ዛሬ በሕይወት የሌሉት ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ስለ አበሻነት እና ኢትዮጵያዊነት ብዙ እውቀት ሰጥተውናል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ታሪክ የተሰኘ ትምህርት ያስተምሩ ነበር፡፡ የግእዝ ቋንቋንም ያስምሩ ነበር፡፡ በሥነ-ጽሁፉ ትምህርት ስለ አበሻነትና ኢትየጵያዊነት አስተምረዋል፡፡ የዩነቨርሲቲ የሥነ-ጽሁፍ መማሪያ መጽሀፍም አዘጋጅተዋል፡፡ እኚህ ታላቅ የስነ-ጽሁፍ ሊቅ ሲናገሩ፤-እነዚህ ሁለት ስያሜዎች ለብዙዎቻችን ጎልተው አይታዩንም ይላሉ፡፡ ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ጊዜውን በውል ሰፍሮ ቆጥሮ መናገር ባይቻልም ከጥንት ጀምሮ በተለዋዋጭነት ለአገራችን መጠሪያ ስንገለገልባቸው ቆይተናል፡፡ የውጭ አገር ያገራችን ታሪክ ፀሐፍያን አንደኛው በተለዋዋጭነት ሲጠቀሙባቸው እናገኛለን፡፡ እንዲህም ሲያደርጉ በኢትዮጵያና በአበሻ መካከል ልዩነት እንዳለ አስበው አይደለም፡፡ በማለት ምሁሩ ጽሁፋቸውን ይገልጹታል፡፡ አክለውም የሚከተለውን ብለዋል፡-
ለምሳሌ ጀርመናዊው ሊቅ ኢያብ ሉዶልፍ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የጻፈውን መጽሐፍ ርዕስ “The History of Ethiopia or the kingdom of the Abessins” ብሎ ሰይሞታል፡፡ ሌላው ጀርመናዊ ደራሲ “Edward Ruppel” በአገራችን ውስጥ ስላደረገው ጉዞ ሲጽፍ “Reise nach Abyssinie’ ወደ አበሻ አገር ጉዞ በሚል ርእስ ጽፏል፡፡ ”Hayatt” የሚባለው ፀሐፊ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሲጽፍ ‘The Abyssininan Church’ በሚል ርዕስ ጽፏል፡፡ በሌላ በኩል የሄድን እንደሆን ስለኢትዮጵያ የጻፉ የአረብ ደራስያንን ስንመለከት በማንኛውም ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ ተጠቅመውበት እንደማያውቁ ዶ/ር አምሳሉ ይገልጻሉ፡፡ ለነሱ ኢትዮጵያ ማለት ሐበሻ ነበር፤ አሁንም በአብዛኛው ይኸው ነው፡፡ ለምሳሌ በአሕመድ ግራኝን በጦርነቶች ሁሉ ተከትሎት ይዞር የነበረው አረባዊው የታሪክ ሰው ስሓቡ ዲን ስለጦርነቱ በጻፈው ፉቱሕ አል ሐበሻ የአበሻ ወረራ በሚለው መጽሐፉ ለአገራችን የተጠቀመበት ስም ሐበሻ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ በማለት ዶ/ር አምሳሉ ይገልጻሉ፡፡ አክለውም፡-
በቅዱስ ቁርአንም የአገራችን ስም ሐበሻ እንጂ ኢትዮጵያ የሚል አንድም ቦታ አናገኝም፡፡ አንድ ምሳሌ እንጥቀስ፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ በጥሪያቸው መጀመሪያ ዘመን አለመግባባት ስለተፈጠረ ተከታዮቻቸውን ከአደጋ ለማዳን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሰደዱ ሲያዟቸው እንዲህ ብለዋቸዋል “ወደ ሐበሻ ብትሄዱ በርሱ ጥላ ከለላ ሥር ያሉ ሰዎች የማይሰደዱበት ንጉሥ ታገኛላችሁ፡፡ የጽድቅ አገር ናት ስለዚህም እግዚአብሔር ከጭንቃችሁ ይታደጋችኋል፡፡” ብለዋል፡፡
ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ስለዚሁ አበሻነት እና ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ለማብራራት አንድ የሕይወት ዘመን ገጠመኛቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ እንዲህም ይላሉ፡-
አንድ ትዝ የሚለኝ ግሩም አጋጣሚ አለ፡፡ ምናልባትም እዚህ ላስረዳ ለፈለኩት ሐሳብ ጠንካራና ተጨባጭ ማብራሪያ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ቋንቋና አፈታሪክ ታሪካዊ መረጃዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያጠራጥር ነገር አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሣ ነው ለአፋዊ ሥነ ጽሁፍ ዋጋ ሰጥተን በከፍተኛ ደረጃ የምናጠናቸው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው ሦስት የትምህርት ጓደኞቼና እኔ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኘተን ካይሮ ግብፅ ውስጥ እንማር በነበርንበት ጊዜ አንድ ቀን እራታችን በታወቀው የካይሮ አውራ ጎዳና በቫሪዐ ፉአድ በስተግራ በኩል ስንሸራሸር በዚሁ መንገድ በስተቀኝ በኩል የኛን አገር ሰዎች የሚመስሉ ወጣቶች እንደኛው በእግራቸው ሲንሸራሸሩ አየን፡፡ ወዲያው ከነሱ አንደኛው ከፍ ባለ ድምጽ ወደኛ እየጠቆመ እኒያ እማዶ ያሉት ልጆቸ አበሾች ናቸው አለ፡፡ ከዚያ በኋላ እነሱ መንገዱን ተሻግረው ወደኛ ሲመጡ እኛም የትራፊኩ መብራትና የእግር መንገደኞች ማቋረጫው መንገድ ወደኋላ ስለነበረ ወደኋላ ሄደን ጠበቅናቸውና ተገናኝን፡፡ ኋላ ስንተዋወቅ የኢትዮጽያ አየር መንገድ ሠራተኞች መሆናቸውን ተረዳን፡፡ እዚህ ላይ የአንባቢዎቼን አስተያየት ለመመለስ የምሻው ወደሚከተለው ቁም ነገር ነው፤ ያ ወጣት በግብፅ አውራ መንገድ አይቶን እኛን አበሾች ሲል እኛ የተለየን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መሆናችንን ማመልከቱ አልነበረም፡፡ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያውያን ማለቱ ነበር፡፡ ለዚህም ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው አበሾች ብሎ ከጠራን ውስጥ አንዱ ጉራጌ ሁለታችን አማሮችና ሌላኛው አራተኛው ኦሮሞ ነበር፡፡
ይህን ገጠመኛቸውን ሲያብራሩም፡-
ማንኛውም አጥርቶ አሳቢና ሁኔታዎችን ጥሩ አድርጎ ለመመልከት ለሚሻ ሰው ያ ወጣት አበሻ ባለበት ጊዜ በሕልሙም ሆነ በውኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለምንኖር የተለየን ሰዎች መናገሩ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ስለ አገሩ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያውያን መናገሩ ነበር፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከአያሌ ዘመናት በፊት ጀምረን ስለራሳችን እርስ በርሳችን ስንነጋገር አበሻ እያልን እንነጋገራለን እንጂ እኛ ስለሀገራችን በጽሑፍም ሆነ ይፋዊ መግለጫ ስንሰጥ ኢትዮጵያዊያን እንጂ አበሾች አንልም፡፡ በየጊዜው እርስ በርሳችን በምናካሂደው ውይይት ጨዋታ እኛ አበሾች፤ ያበሻ ነገር’ ያበሻ ልብስ’ ያበሻ ቀጠሮ’ ያበሻ ምግብ’ ስም ስናወጣ አበሻ ጣይ’ /አበሻ ፀሐይ/ አበሹ ያበሻው ንጉሥ እንላለን፡፡ እንዲህ በምንልበትም ጊዜ በአስተሳሰባችን ላይ የተለየ ብሔረሰብ ለማመልከት ብለን አይደለም፡፡
እንግዲህ ይህን የቋንቋ አጠቃቀም ጣጣ ወደጎን ትተን አበሻና ኢትዮጰያ የዚችው የኛው አንዲቱ አገር መጠሪያ መሆኑን እናስተውል፡፡
እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ማብራሪያ እንስጥ ይላሉ እኚህ ተወዳጅ መምህሬ፡፡
አበሻ ሐበሻ የሚለው ስያሜ የተገኘው ታሪክ እንደሚነግረን ከደቡብ ዐረቢያ ወደ አፍሪቃ ቀንድ ፈልሰው ከመጡ ብዙ የደቡብ ዐረቢያ ነገዶች ካንዱ መጠሪያ ነው፡፡ የዚህ ነገድ ስም ኋላ በምሥራቁ ዓለም ለመላዋ አገራችን መጠሪያ እየሆነ ሄዷል፡፡ ለምሳሌ ይህ ስም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገናና በነበረው የአክሱም ንጉሥ በዔዛና የደንጊያ ጽሑፎች ላይ ተቀርፆ ይገኛል፡፡ ይህ ንጉሥ የሸፈቱበትን ያካባቢውን ግዛቶቹን አሸንፎ ማስገበሩን ሲናገር ስለ ስም ማዕረጉ እንዲህ ብሎ ይጽፋል፡-
ዔዛና የአክሱም የሕምያርም የካሱና የሐበሸትም የረይዳንም የሰልሔንም የጽያሞም ንጉሠ ነገሥት፤ የማሕረም ልጅ በጠላቶቹ የማይሸነፍ!
እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን የሚከተለውን ታሪካዊ ሐቅ ነው፡ ይህ የአክሱም ጽሑፍ ልሳነ ሦስት ሲሆን የተጻፈባቸውም ቋንቋዎች በሳብኛ በጥንቱ ግዕዝና በግሪክኛ ነው፡፡ በግሪኩ ጽሑፍ ላይ በሐበሸት ፋንታ ኢትዮጵያ በሚል ተተክቶ እናገኛለን፡፡ ይህን ካልን ዘንዳና ስለ ሐበሻ አመጣጥ እንደተናገርነው ሁሉ ስለ ኢትዮጵያም አመጣጥ ባጭሩ እንናገር፡፡
ስመ ጥሩ የግሪክ ባለ ታሪክ ሆሜር ከግብጽ በስተደቡብ ያሉትን የአፍሪቃ አገሮች ሁሉ በደምሳሳው ኢትዮጵያ ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡ ይህም ከጊዜ ብዛት የሌሎችም የአፍሪቃ አገሮች መጠሪያ መሆኑን አቁሞ የኢትዮጵያ ብቻ እየሆነ ሄዷል፡፡ አብዛኞቹ አውሮጳውያንም የሆሜርን ፈለግ በመከተላቸው፤ አገራችንን ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከሐበሻ ይልቅ ወደ ኋላ ጊዜ በብዛት እየገነነ የመጣ ይመስላል፡፡ ይህም አገራችን ከምዕራባዊው ዓለም ጋር ይበልጥ ግንኙነት ማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ከብዙ ምእተ ዓመታት ጀምሮ ሁለቱም ስያሜዎች ያገራችን መጠሪያዎች መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ነው አንዳንድ የኢትዮጵያ ነገሥታትና መሪዎች ለአውሮጳ አቻዎቻቸው መሪዎች በሚጽፏቸው ደብዳቤዎች በሐበሻ ፋንታ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ብለው ሲጽፉ የነበረው፡፡ በአንጻሩ ግን ለምሥራቅ መሪዎች በሚጽፉበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከሚለው ስያሜ ይልቅ አበሻ/ሐበሻ የሚለውን ይመርጡ ነበር፡፡
ይህን ሐሳብ ለማብራራት የሚከተለውን ሁኔታ እንይ ይላሉ ዛሬ በሕይወት የሌሉት ታላቁ መምህር ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ፤
ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ አራተኛ ለማንኛውም የዓለም መሪ በጻፏቸው ደብዳቤዎች በሳቸው ጊዜ ኦፊሴላዊ የነበረውን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ከማዕረጋቸው ጋር ሲጠቅሱ በማኅተማቸው ላይ ግን ዐረብኛም ስለነበረው ሐበሻ የሚለውንም ስያሜ ጨምረው ይጽፉ ነበር፡፡ ለምሳሌ የደብዳቤዎቻቸው መግቢያ እንዲህ የሚል ነው፡፡
ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ካሉ በኋላ በማኅተማቸውም ላይ ይኸው ይደገምና ነገር ግን በዐረብኛ ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን እንዳለ ሆኖ፣ ንጉሠ ነገሥት ከሚለው ቀጥሉ በ ዘኢትዮጵያ ፋንታ የሐበሻ የሚል ይገኝበታል፡፡ እንዲህ ማድረጋቸውም የምዕራቡንም የምሥራቁንም ርዕስ ብሔሮች በሚያውቁት ቋንቋ ለማስተናገድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ዶ/ር አምሳሉ የአበሻንና የኢትዮጵያዊነትን ጉዳይ እንዲጽፉ ያደረጋቸውን ምክንያትም አስቀምጠዋል፡-
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምዕራባውያን ፀሐፊዎች ሁለቱ ስያሜዎች ማለትም ሐበሻና ኢትዮጵያ የተወሰኑ የሀገራችን ክፍሎች መጠሪያ እንደሆኑ ያለሀፍረት ሊነግሩንና ሊያሳምኑን ይፈልጋሉ፡፡ እንደነሱ አባባል ሐበሻ ማለት በትግራይና /ኤርትራን ጨምሮ/ በአማራ ከፍተኛ ቦታዎች የሚኖሩ ሕዝቦች መጠርያ ስም ነው ይሉናል፡፡ ከዚህም በመነሳት ሐበሻ ነፍጠኛ ጦረኛና ጨቋኝ የገዥ መደብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ እንዳጋጣሚ እኔም በተካፈልኩበት አንድ ጥናታዊ ጉባኤ፣ አንድ የውጭ አገር ሰው ባቀረበው ወረቀት ላይ ይህን ሐሳብ ሲያስተጋባ ሰምቻለሁ፡፡ የሰውየውን ማንነት በወግ ስለማውቅ ብዙም አልተደነቅሁበትም፡፡ ግን ስለተናገረው ጉዳይ የጉባኤው ተሳታፊዎች ከነበሩት ብዙ ምሁራን ኢትዮጵያውያን ውስጥ ማንም ሰው አስተያየት አለመስጠቱ በጣም ደንቆኛል፣ ገርሞኛልም፡፡ ይህ ሰው ባቀረበው ወረቀት ባለማፈር ያበሻ ነፍጠኞች ባካሄዱት ወረራ የሚል አገላለጽም ነበረው፡፡ የአበሻ ነፍጠኛ ሲል ሰውየው የንጉሡ ወታደሮች ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እንግዲህ አበሻ የሚለው ትግሬውንና አማራውን ብቻ ማለት ከሆነ ሰውዬው ባልገባው ወይንም በማይገባው ጉዳይ ላይ ዘላብዷል ማለት ነው፡፡ ነፍጠኛ ማለት አንዳንድ የአመለካከት ድኅነት የሚያጠቃቸው ወገኖች እንደሚያምኑት ሳይሆን ጠመንጃ ይዞ የሚዋጋ ወታደር ከማለት በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ብሔረሰብን የሚገልጽ አባባል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት ወታደሮች ከእነዚህ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሰዎች ብቻ ነበሩ ማለት የኢትዮጵያን ታሪክ በወግ አለመረዳት ነው ይላሉ ዶ/ር አምሳሉ፡፡ ምሳሌም ጠቅሰው ያስረዳሉ፡-
በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነግሦ በነበረው በዐምደ ጽዮን ታሪክ ውስጥ ስለ ዐምደ ጽዮን ሠራዊት ቅንብር እንዲህ የሚል ታሪክ እናገኛለን፤ ሸሹም ስላችሁ ከፍርሐት የተነሣ ነው ብላችሁ አታድንቁ፤ ምክንያቱም የሸዋ፣ የዳሞት የጎዣም የትግሬና የብጉና የአምሐራ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ሠራዊት ሁሉ በመላ ቢሰበሰብ በእግዚአብሔር ኃይል ካልሆነ በስተቀር በፊታቸው ሊቆም ስለማይቻል ነው፡፡
ሌሎችም ተመሳሳይ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ነገሥታት ወታደሮች ከነዚህ ሁለት ብሔረሰቦች ብቻ የተውጣጡ ነበሩ ማለት ኢትዮጵያን በሃይማኖት ለመለያየትና ለማዳከም እንደሚሞክሩት ሁሉ በብሔረሰብም ለመከፋፈል የሚፈጥሩት ዘዴ ነው፡፡ ሁኔታዎችን ቀረብ ብለን ካየን የዚህ መሠሪ አከፋፈል ምንጭ የአውሮጳ ሚሲዮናዊያን ናቸው፡፡ የነዚህ ቡድኖች ዋና ዓላማ እምነታቸውን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ድብቅ ዓላማም አላቸው፡፡ ይኸውም ደካማ ኢትዮጵያን ፈጥሮ፣ እንዳሻቸው መግዛትና ማዘዝ እንዲያስችላቸው ማድረግ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
ወደዋናው ጉዳይ መለስ ይሉናም ያብራራሉ፡፡ ነፍጠኛ ማለት ማንኛውም ንጉሡን ወይም የጦር መሪውን ተከትሎ ጦር ሜዳ የሚገኝ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ከሁሉም ብሔረሰብ እየተውጣጣ ይመሠረት እንደነበረ ማስረጃ ማቅረብ አያሻም፡፡ አንቱ የተባሉትም የጦር መሪዎች የልዩ ልዩ ብሔረሰብ ወገን እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙያቸውና በአገር ወዳድነታቸው ሲያገለግሉ የነበሩትን እነ ባልቻ አባ ነፍሶን፣ እነ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን፣ እነ ጎበና ዳጨን፣ እነ ገረሱ ዱኪን፣ እነ አበበ አረጋይን፣ እነ አበበ ዳምጠውን እና እነ ደሰታ ዳምጠውን ሌሎችም በጣም ብዙዎች ከየትኛው ክፍል ልንመድባቸው ይሆን? አበሻ ወይስ ኢትዮጵያ? ብለው ዶክተሩ ይጠይቃሉ፡፡
ጥያቄው እንግዲህ እንዲህ ያለው ችግር ለምን ተፈጠረ በሚለው ላይ ነው፡፡ አመዛዛኝ አእምሮ ያለው ሰው ይህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ እንዳለው ፈጥኖ ይረዳል፡፡ ችግሩ ያለው ሐቁን ሸፋፍነው ሌላ የራሳቸውን ወይንም የፈረንጆችን ሕልም እውን ለማድረግ በሚሞክሩት ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ ዋናውን ጉዳይ ጉልህ አድርገን ማቅረብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምንድን ነው ምዕራብያውን በአበሻና በኢትዮጵያ መሀከል ልዩነት ፈጥረው ልብወለድ ታሪክ የሚነግሩንና እንድናምንላቸው የሚፈልጉን ለሚለው ዋናና መሠረታዊ ጥያቄ መልሱ ይህ ነው፡፡ የወደፊት ተስፋቸውን በጣሉባት ገና ባልተበላችውና በድንግሏ የውስጥ አፍሪቃ አህጉር ጠንካራና አይበገሬ መንግሥት እንዲነሣ አይሹም፡፡ ከዚህም የተነሣ የተከፋፈለችና ደካማ ኢትዮጵያ /ወይንም ሌላ የአፍሪቃ አገር/ ለሕልማቸው ማስፈፀሚያ ጥሩ መስክ ሆና ያገኙዋታል፡፡ አንዲት ጠንካራ ሀገር እምቢ ይህ መብቴ ነው ከናንተ ጋር የምዋዋለው እና የምደራደረው ጥቅሜንና መብቴን አስጠብቄ እንጂ የናንተን ፈቃድ ብቻ ለመፈፀም አይደለም፡፡ ግንኙነታችን ሁሉ በኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት እንድትላቸው አይሹም፡፡ እነርሱ በርካሽ ያመረቱትን የፋብካዎቻቸውን ምርት በውድ ዋጋ ለኛ ሸጠው፣ የኛን የእርሻ ውጤት ባልባሌ ዋጋ ሊቀሙን ይሻሉ፡፡ ይህም ዓይኑን ያፈጠጠ ዝርፊያ መሆኑን ማንም አስተዋይ አይስተውም፡፡ እንዲህ ያለውን የሽንገላ ዘዴያቸውን ባለፈው ምእተ አመት ተጠቅመውበታል፤ ባሁኑ ጊዜ ግን ፈጽሞ የማይታለም እየሆነባቸው ነው የሄደው፡፡ ስለዚህም ሌላ ዘዴ መፈለጉ አማራጭ ያልነበረው መንገድ ነበር፡ ይህም የከፋፍለህ ግዛ ማኪያቬሊዊ ፍልስፍና ለዕድላቸው መፈተኛ እያረጉ ስለኢትዮጵያ በሚናገሩበት መድረኮች ሁሉ ደጋግመው እያነሱት ነው፡፡ እንዲህ ባለውም ዓይኑን ባፈጠጠ የሽንገላ ዘዴያቸው ሊያታልሉን የሚችሉት የሚሉንን አምነን የተከፋፈልንላቸው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡
ምዕራባውያን አፍሪቃን ሲቀራመቱ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ዕጣ እንድትሆን ወስነው ነበር፡፡ ይህም ከግፍና ከአመጽ የተነሣ እንጂ ሌላ ምክንያት አልነበረውም፡፡ በሁለቱም አገሮች መካከል የብዙ ሺ ኪሎ ሜትር የርቀት ልዩነት አለ፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያንና ኢጣልያንን የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት የመልከኣ ምድር ጉርብትና የለም፡፡ ሆኖም ግን ኢጣልያ ኢትዮጵያን በላቀ የጦር ኃይል አሸንፋለሁ በማለት የዐድዋን ጦርነት አካሄደች፡፡ በዚያን ጊዜ እንደማንኛውም ወቅት ሁሉ ጠንካራና አይበገሬ ኢትዮጵያ ግንባሯን ሳታጥፍ የኢጣልያ ሽንፈት ለአውሮጳ ትልቅ ውርደት ነበር፡፡
አንባቢ ሆይ አስተውል እንግዲህ በጦርነት ያልቀናውን ዕድል በሌላ ዘዴ መሞከሩ ጥሩ ብልሃት መሰሎ ለምዕራባውያን ስለታያቸው ምሁሮቻቸው #አበሻ$ ና #ኢትዮጵያ$ የሚለውን የቆየ ስያሜ አዛብተው መጠቀም ጀመሩ፡፡ የሚገርመው አንዳንድ ወገኖቻችን ይህን ውስጠ መርዝ አከፋፈል ሳይመረምሩ እያስተጋቡ ነው፡፡ አንዳንዶቹ እንደዚህ ያለውን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ ለምን እንደተጠነሰሰ ቢያውቁትም በዚህ አማልክቶቻቸው ባወጡላቸው የከፋፍለህ ግዛ ዘዴ በመጠቀም አገርን ገንጥሎ /እንደ ኤርትራ/ ለመግዛት ያላቸውን ምኞች እውን ለማድረግ እንደሚረዳቸው ስለሚያምኑና እስልጣን ኮርቻ ላይ ለመንጠላጠል ስለሚፈልጉ ከማንም ይበልጥ ያናፍሱታል፡፡ ነገር ግን ካለፉትና ከቅርብ ታሪካችን አለመማር ነው እንጂ በቅርቡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት ትምህርት ቢወስዱ ኖሮ አበሻና ኢትዮጵያ እያሉ አገራቸውን ከመከፋፈል ቢቆጠቡ ጥሩ ነበር፡፡ በዚህ ግጭት ይህ የአበሻ ነፍጠኞች ጣጣ ነው ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ እጁን አጣምሮ አልተቀመጠም፡፡ ጢስ እንደገባበት ንብ ሆ ብሎ ተነሥቶ ተዋድቆና ደሙን አፍስሶ አገርን ከወራሪ ታደጋት፡፡
ይህን ካልኩ በኋላ የኢትዮጵያ ችግር እምኑ ላይ ነው ወደሚለው ጥያቄ ሊሂድና አንዳንድ ሐሳብ ልሰንዝር፤ ኢትዮጵያ በአበሻና በኢትዮጵያ የመከፋፈሉ ዓላማ አገሪቱን ለማዳከምና ያሏትን አሜን ብላ የምትቀበል ደካማና ጥገኛ አገር ለመፍጠር መሆኑን በመጠኑም ቢሆን ተገንዝበናል፡፡ የዚህ አከፋፈል ውጤትም ጨቋኝና ተጭቋኝ የሚለውን መደብ ፈጥሮ እርስ በርስ ለማቃቃርና ለማጫረስ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ችግር ያለው በገዥና በተገዥ መደብ መካከል ባለው ቅራኔ እንደሆነ ማንም አስተዋይና በኢትዮጵያዊነቱ/ በአበሻነቱ የሚያምን ዜጋ ጥሩ አድርጎ ይረዳዋል፡፡ በማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ውስጥ ጨቋኝም ተጭቋኝም የኅብረተሰብ ክፍል ነበር፤ አሁንም ይኖራል፡፡/ሶሻሊስት ሆኜ ሳይሆን ሐሳቤን በወግ ሊገልጽልኝ ስለቻለ ብቻ ነው፡፡/ የኢትዮጵያ ችግር እዚህ ላይ ነው እንጂ ሌላ ሐተታ እየፈለጉ ማሳዘኑ የትም አያደርስም፡፡ ለአንዱ ብሔረሰብ ልዩ ስም እየሰጡ ጨቋኝ፣ ሌላውን ተጨቋኝ ማድረግ ከተጨባጩ እውነታ ጋር ስለማይሄድ የትም አያደርሰንም፤ ከአእውነታው እየራቅን ትዝብት ላይ ከመውደቅ በስተቀር፡፡
ይህ የጨቋኝና የተጨቋኝ ፍትህ አልባ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈታ የሚችለው በኔ እምነት በበጎ የማያስቡልን ወገኖች እንደሚያላዝኑት ሳይሆን ወደፊት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል በሚቋቋመው ፍትሕና ርትዕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርአተ ማህበር ሲነግሥ ብቻ ነው፡፡
ይህም እውን የሚሆነው እያንዳንዱ ዜጋ ያለተጽእኖ እንደራሴውን ወክሎ መርጦ እሱን ወክሎ በሚያቋቁመው የወኪሎች ሸንጎ አማካኝነት ነው፡፡ በሕዝብ ምርጫ የሚቋቋመውም ሕዝባዊ ሸንጎ የሚሾመው የአገር መሪ ለተወሰነለት ጊዜ ብቻ አገልግሎ ሥልጣኑን ለተተኪው በማስረከብ ምንምና ማንንም ሳይፈራ የኅብረተሰቡ አባል ሆኖ መኖር የሚችል መሆን ያለበት ሲሆንና ሥልጣን በያዘቡት ዘመን ዓይነ ውሀው ካላማረ ወዲያው ከሥልጣን ወርዶ ላደረገውም ጥፋት ተጠያቂ የሚሆንበት ሥርዓት ሲቋቋም ነው፡፡
በኔ እምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊታገልለት ሊያቋቁመው የሚገባው እንዲህ ያለውን ሥርዐት ማኅበር ነው፡፡ የተለቀቀ ገንዘብ ሌብነትን ያስተምራል እንደሚባለው ሁሉ የተለቀቀ ሥልጣንም እንዲሁ ያባልጋል መረንም ይለቃል፡፡ ልጓም የሌለው ፈረስ እንደልቡ እንደሚፏልል ሁሉ ቁጥጥር ያነሰውና በሕዝብ እውነተኛ የበላይነት የማያምን መሪ እንዲሁ እንዳሻኝ ልሁን ይላል፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ ችግር ያለው በጨቋኝና በተጨቋኝ የኅብረተሰብ አባላት መካከል ካለው ቅራኔ የተነሣ እንጂ አበሻ’ ኢትዮጵያ ነፍጠኛ’ ትምክሕተኛ እየተባለ ሕዝብን ለመበታተን ‘ለማቃቃርና ለማፋጀት ከሚደረገው ሙከራ የመነጨ አይደለም፡፡
አስተዋይ አዕምሮ ያለውን ልጠይቅ፤ ለመሆኑ ጨቋኝና ነፍጠኛ እያሉ የሚጠሩት ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ የተለየ ምን ጥቅም አግኝቶ ይሆን? ይህን ያህልስ ጥላቻ የሚሰነዝርበት?
በመጨረሻም የአበሻንና የኢትዮጵያን ስያሜ ጉዳይ በጥንቃቄ መመርመር፣ ማየትና ዓላማውም ምን እንደሆነ ዓይነ ኅሊናችንን ከፍተን ማየት ይኖርብናል፡፡ በአገራችን ህልውና ላይ የተሰነዘረ የጠላቶቻችን ለያይተህ እና የአዳክመህ ግዛ መሣሪያም መሆኑን በወግ እንረዳ፡፡ እስከመቸስ እየተታለልን እንኖራለን? በማለት የዩኒቨርሲቲ መምህሬ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ትውልድን የሚያስተምር ጽሁፍ ሰጥተውን አልፈዋል፡፡ ታለቅ መምህራችን ነበሩና ዛሬም እንማርባቸው ዘንድ ነው ዘለግ ያለውን መጣጥፋቸውን ያቀረብኩት፡፡