ለባርነት የተሸጡት ኢትዮጵያዊ ጀኔራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል (1696-1781) አጭር ታሪክ

By ባይለይኝ ጣሰው (ዶ/ር) first published on June 23, 2020

ከዚህ በፊት ባቀረብኳቸው በአንደኛውና በሁለተኛው ክፍሎች የጀነራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል የገጠማቸውን ውጣውረድ የተሞላበት ትራጅክ የሕይወት ታሪክ ላይ በማተኮር ከመነሻው እስከመድረሻው ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ አንባብያንም እንደተደሰታችሁበት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ ሦስተኛው ክፍል ደግሞ ስለ ጋኒባል አሟሟትና ስላበረከቷቸው ትሩፋቶች በማውሳት ታሪኩን እንቋጫለን፡፡

የጀነራል አብርሃም ጋኒባል እረፍትና ትሩፋት

የሁለት ዓለም ሰው እንደሚባለው ዓይነት ጀነራል  አብርሃም  ሀኒባል፣  በአንድ በኩል፣  በታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ  ክርስትና  ተነስቶ፣  በፈረንሳይ  ተምሮ፣  በሩሲያ  መንግሥት  ተሀድሶ ተሳትፎና ትልቅ ድርሻ  አበርክቶ፣ ሩሲያዊ ሕይወት ኖሮ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዕድሜ ልኩን የትውልድ ሀገሩን እንደናፈቀ የሁለት ዓለም ሰው ሆኖ ነው የሞተ (አልክሳንደር ፑሽኪን)፡፡

የጀነራል አብርሃም ጋኒባል እረፍት፡- ጀነራል አብርሃም ጋኒባል ዕድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱና የጡረታ ዘመናቸው በመድረሱ በ1762 ዓ.ም. ከመንግሥት ሥራ በጡረታ ለመሰናበት አመለከቱ፡፡ እንዳመለከቱም የሙሉ ጀነራልነት ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡ የጡረታ መብታቸውም ተከበረ፡፡ ከዚህ በኋላ የሩሲያ መሥፍን (ኖብል) ተብለው የተሰጣቸውን ሰፊ የርስት መሬት በማሳረስ ሲጠቀሙ ቆዩ፡፡ ሆኖም ግን በተደራራቢ ምክንያቶች የጤንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መጣ፡፡ አንዱ የታላቁ ጴጥሮስ እና የንግሥት ኤልሳቤጥ ተከታትለው የመሞታቸው አጋጣሚ ያስከተለባቸው መሪር ሀዘን ነው፡፡ ሁለተኛው በልጅነታቸው የተጣለባቸው የባርነት ቀንበር ያደረሰባቸውን ስቃይ ሁሉ ተመልሰው በማብሰልሰል ከሀገራቸው እንደወጡ የመቅረታቸው ሁኔታ ነበር፡፡ ሦስተኛው በሥራ ዘመናቸው ውስጥ ከገጠማቸው ፈተናና እንግልት የተነሳ ያደረባቸው የፍርሀት ህምም ነው፡፡ በተለይም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደወል ድምፅ በሰሙ ቁጥር ሳይቤሪያ ውስጥ በግዞት ሳሉ ቶርቸር ያደረጓቸውና በስለላ መውጫ መግቢያ የነሷቸው የእነዚያ ጨካኞች ምስልና ድርጊት በእዝነ-ዓይነ-ኅሊናቸው እየተደቀነ መላ ስሜታቸውን በማወክ ነፍሳቸው በድንጋጤ እየተዋጠች ቅጥ ይጠፋቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም በሕይወት ዘመናቸው የመዘገቧው ያስቀመጧቸውን የግል ማስታዎሻዎች ሁሉ በመቅደድና በማቃጠል እንዳወደሟቸው የታሪክ ፀሐፍት በጸጸት ገልጸውታል፡፡

በዚህ ሁኔታ እንደነበሩ ጀነራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል በፈረንሳይ ውስጥ የውትድርና ትምህርት በመከታተል ላይ ሳሉ በ1719 ዓ.ም. ከፈረንሳይ ጦር ጋር ሆነው የስፔንን ጦር ባጠቁበት ውጊያ ከራሳቸው ላይ በጥይት ተመትተው ደርሶባቸው የነበረው ቁስል በጊዜ ሂደት ሳይታወቅ ወደ ነቀርሳነት ተቀይሮ ከባድ ህመም ከገጥማቸው በኋላ (እኤአ) ግንቦት 14 ቀን፣ 1781 ዓ.ም.፣ በ85 ዓመታቸው፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ቀብራቸውም በቅዱስ ፒተርስበርግ ተፈፀመ፡፡ ከመካነ ቀብራቸው ላይ እንደሚታየው እስከዛሬ ድረስ ተጠብቆ የሚገኝ ሲሆን፣ ሙሉ ስማቸው፡- አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል፣ የትውልድ አገራቸው፡- ኢትዮጵያ፣ ልዩ ሥፍራው፡- ምድሪ ባህሪ – ኤርትራ፣ የሞቱበት ቀንና ዓ.ም.፡- ግንቦት 14 ቀን፣ 1781፣ ቅዱስስ ፒተርስበርግ፣ ዜግነት፡- ሩሲያዊ፣ ተቀያሪ ስም፡- ሀኒባል፣ ፔትሮቭ፣ ፊርማቸውን ጨምሮ የተቀረፀበት የመታሰቢያ ሀውልት ቆሞላቸው ይገኛል፡፡

የጀነራል አብርሃም ጋኒባል ትሩፋቶች

ከጀነራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ትሩፋቶች መካከል፡- አንደኛ/ በቤተሰባቸው (በልጅ ልጆቻቸው) በኩል ለዓለም ያፈሩትና ያበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦ፣ ሁለተኛ/ በሩሲያ የዛሩ መንግሥት የተሀድሶ ለውጥ ሂደት ያደረጉት አርአያነት የተሞላበት ተሳትፎ፣ ሦስተኛ/ የወደቀባቸውን የባርነትን ቀንበር ሰብረው በዘመኑ ሰፍኖ የነበረውን ከንቱ የዘረኝነት አሰተሳሰብ፣ አድልኦና ድርጊት በመዋጋት በምሳሌነት ያወረሱት ትሩፋት፣ አራተኛ/ ለተለያዩ የሥነ-ጽሑፍና የሥነ-ጥበብ ውጤቶች ምንጭ በመሆን ማገልገላቸው እና አምስተኛ/ የየት-መጥ ታሪካቸው የፈጠራቸው አወዛጋቢ የሽሚያ ክርክሮች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ ወደ የቤተሳባቸውን ታሪክ ስንመለክት አብርሃም ጋኒባል ጋብቻ የፈጸሙት ሁለት ጊዜ ነበር፡፡ አንደኛው ፍሬ አልባ ሆነ፤ ሁለተኛው ግን ፍሬያማ ሆነላቸው፡፡

ፍሬ አልባው ጋብቻ፡- በሁለተኛው ክፍል እንደተገለጸው፣ በሩሲያ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ቀውጢ ጊዜ ጋኒባል ከነበሩበት ከሳይቤሪያ የግዞት ኑሮ የእሥራት ሰንሰለታቸውን አውልቀው፣ በራሳቸው ውሳኔ ተነስተው ወደ ፒተርስበርግ የመመለሳቸው አጋጣሚ በሕይወታቸው ውስጥ ወሳኝ እንዲያውም ታሪካዊ የሚሰኝ ምእራፍ ነበር የከፈተላቸው፡፡ ይህን የሚያሰኜውም በታህሳስ ወር 1730 ወደ ፒተርስበርግ ከተመለሱ በኋላ አንድሬ ዲዮፐር ከሚባል ግሪካዊ የመርከብ ካፒቴን ጋር ተዋወቁ፡፡ ትውውቁን በመካከላቸው እያጠናከሩ ከመጡ በኋላም በስም ኢቭዶኪያ ከምትባል ልጁ ጋር ተዋወቁ፡፡ በኋላም እሷን ለማግባት በመፈለግ ለአባቷ – ለዲዮፐር ጥያቄ አቀረቡለት፡፡ ልጅቱ ለሌላ ሰው ታጭታ ነበር፡፡ ሆኖም አባቷ አብርሃምን ብታገባ እንደሚሻል ሲመክራት “እሱን ለማግባት ብፈልግ እንኳን አራፕ ነው፤ የእኛ ዘር አይደለም” የሚል መልስ በመስጠት እሽ ልትል አልቻለችም፡፡ በኋላ ግን የቤተሰብ ጫና ተጨምሮበት በ1731 ጥር ወር ጋብቻው ተፈፀመ፡፡ ጋብቻው እንደተፈጸመ የትዳር ኑሯቸውን ለመቀጠል ወደ ፔርኖቭ ጓዝ ጠቅልለው ሄዱ፡፡ ሆኖም ትዳሩ ሳይውል ሳያድር ቅጥ እያጣ በመምጣት የጭቅጭቅ ኑሮ ሆነ፡፡ እየቆየም ሁኔታው እየተባባሰ ሄደ፡፡ ጋኒባል ባለቤታቸው ኢቭዶኪያ ነፍሷን የሳተች ቅንዝረኛና ምንዝር መሆኗን ተረዱ፡፡ ከዚህ ዐመሏ እንድትመለስ ቢመክሯትም የማትመለስና ከዚህም አልፎ በጥቁርነታቸው የምትሳለቅ መሆኗን ሲያውቁ ትዳሩ ትደር እንደማይሆን ተስፋ እየቆረጡ መጡ፡፡ እርሳቸው ተስፋ እየቆረጡ በመጡበት ጊዜ  ኢብዶኪያ በበኩሏ ከብዙ ወንዶች ጋር መዳራቷን ቀጠለችበት፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከውሽሞቿ ጋር በመመሳጠር ጋኒባልን መርዝ አብልታ ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ አደረገች፡፡

በዚህ ጥላቻ በተሞላበት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ አንዲት ልጅ ወለዱ፡፡ ልጅቷ ሀጫ በረዶ የመሰለች የነጭ ነጭ ሆነች፡፡ ስሟም ፖሊክስኒያ ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜ ጋኒባል “ይህች ልጅ ከእኔ የተወለደች አይደለችም” ብለው ለኢብዶኪያ በግልጽ ነገሯት፡፡ እርሷም “እንዴት ጥቁር ትወለዳለች ብለህ ትጠብቃለህ?” በማለት ተሳለቀች፡፡ በዚህ ዓይነት ትዳሩ ትዳር ሊሆን ባለመቻሉ ጋኒባል የፍች ደብዳቤ ለፍርድ ቤት አቀረቡ፡፡ የፍች ጥያቄው ግን እስከ መስከረም 9 ቀን፣ 1753 ዓ.ም ድረስ ውሳኔና ብይን ሳይሰጠው ለ21 ዓመታት ያህል ሲንከባለል ቆየ፡፡ ከሀያ አንድ ዓመት በኋላ ኢቭዶኪያን ጥፋተኛ፣ ጋኒባልን ነፃ ያደረገ ፍርድ ተሰጠ፡፡ ጋኒባል ነፃ ቢሆኑም መጠነኛ ገንዘብ እንዲከፍሏት ተደረገ፤ ሴትዮዋ ግን በቀሪ የሕይወት ዘመኗ ውስጥ ሌላ ባል ሳታገባ በምንኩስና እንድትኖር ተፈርዶባት ስትማቅቅ ኑራ ሞተች፡፡ ይህ ሲሆን ጋኒባል ልጅቱን አልሰጥም ብላው እንደ ልጅ በጥንቃቄ አሳድገው፣ በጥሩ ሁኔታ አስተምረው፣ ለቁም ነገር አብቅተዋታል፡፡

ፍሬያማው ጋብቻ፡- “ኋላ ከመናደድ እያዩ ነው መውደድ” እንዲሉ ጋኒባል በችኮላ ከፈፀሙት የመጀመሪያው ጋብቻ ካስከተለባቸው ጣጣ ትምህርት አግኝተዋል፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያውን ትዳር አስመልክቶ ያቀረቡት ክስ ፍርድ ሳይሰጠው እየተጓተተ በመሄዱ ሌላ ሚስት ለማግባት ወሰኑ፡፡ በመሆኑም ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በ1734 ዓ.ም. አንዲት ክሪስቲና ሪጂና ቮን ሾበርግ የተባለች ከመሳፍንት ወገን ከሚወለድ የስዊዳናዊ ካፒቴን ከምትወለድ አንዲት መልካም ጠባይ ካላት ሴት ጋር ተስማምተው በህጋዊ ሚስትነት አገቧት፡፡ ከክሪስቲና ሪጂና ጋርም ለሃምሳ ዓመታት በፍቅር፣ በደስታና በሰላም በትዳር በመኖር ልጆች መውለድና ማሳደግ ቻሉ፡፡ የሞቱትም በተመሳሳይ ዓመት በተከታታይ ወራት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ከእናቲቱ ጋር ቢፋቱም የመጀመሪያ ልጃቸው ፖሊክስኒያ ከእርሳቸው ጋር ትኖር ነበር፡፡

ጋኒባል ከክርስቲና ሪጅና አምስት ወንዶች፣ አምስት ሴቶች በአጠቃላይ 10 ልጆች ዋልደዋል፡፡[1] ከወንዶች፡- የመጀመሪያው ኢቫን፣ ሁለተኛው ኦሲፕ (ዮሴፍ) ሦስተኛው ፒተር፣ አራተኛው ያቆብ፣ አምስተኛው ይስሀቅ (ሳባ) ይባላሉ፡፡ ከሴቶች ደግሞ፡- አንደኛዋ አና አብርሃሞቫ፣ ሁለተኛዋ ኤልዛቤጥ አብርሃሞቫ፣ ሦስተኛዋ አግራፊና አብርሃሞቫ፣ አራተኛዋ እና አምስተኛዋ ሶፍያ አብርሃሞቫ ይባላሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በተለይም የኢቫንና የዮሴፍን (የኦሲፕን) ታሪክ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡   

ኢቫን አብርሃሞቪች – “‹የቻዝማው ጀግና›”  

አብርሃም ጋኒባል ልጆቻቸው ወደ ውትድርና ዓለም ወይም በቤተመንግሥት ውስጥ ሥራ እንዳይገቡ ምኞታቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም ችግር ይገጥማቸዋል የሚል ፍርሀት ስለነበራው ነው፡፡ ይሁንና የመጀመሪያው ልጃቸው ኢቫን ከምኞታቸው ውጭ ወደ ውትድርና ዓለም ገባ፡፡ የተዋጣለት የባህር ኀይል መኮንን ሆነ፡፡ እንደ አባቱ ለሙሉ ጀነራልነት በቅቶ በሩሲያ መንግሥት የመጨረሻው ሁለተኛው የነበረውን ወታደራዊ ደረጃ ማዕረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደርሶ፣ በተለይም፣ በ1770 በግሪክ አርቼፔላጎ (ደሴቶች) በተካሄደው ዘመቻ የሩሲያን ምድር ጦር በኮማንደርነት መርቶ የኦቶማን ቱርክን ግዙፍ ጦር ናቫሪኖ ላይ መደምሰስ በመቻሉ የጦር ሜዳ ጀብዱ መዳሊያ በብሔራዊ ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን በመብቃቱ በልዩ ክብር አገልግሏል፡፡ “የቱርክ ጦር ከደመሰሰ በኋላ አባቱን ‹ከፈቃድህ ውጭ ወታደር በመሆኔ ይቅርታ አድርግልኝ› ብሎ ተንበርክኮ ጠይቆ ይቅርታ አድርገውለታል፡፡”   

በዚያው ዓመት በቻዝማ ቤይ (ቸዝንስኪ) በተደረገው ጦርነት የባህር ኃይል አዋጊ (ኮማንደር) ሆኖ ድል ተቀዳጅቷል፡፡ በዚህም “የቻዝማው ጀግና” እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ “ኢቫነ ጋኒባል በስትራቴጂስትነት ብቻ የሚታወቅ አይደለም፡፡ አንዱ ታላቅ ጀግና ጭምር እንጂ፡፡ በግሪክ ጦርነት ዘመቻ በሩሲያ ባሕር ኃይል በመሳተፍ በ1770 በናቫሪን የቱርክን የጦር ምሽግ ተቆጣጥሯል፡፡ የቻዝማ ጦርነት ጀግና ነው፡፡ የአብርሃ ፔትሮቪች ልጅ ኢቫን አብርሃሞቪች ጋኒባል እጅግ በጣም ድንቅ ጀግና ነው፡፡  አብርሃሞቪች ጋኒባል በቻዝማ ጦርነት በተቀዳጀው ድል የቅዱስ ጊዮርጊስ የጀግንነት ክብር ተሸላሚ ነው፡፡ በፑሽኪን አገላለጽ በካቴሪን ሁለተኛዋ ዘመነ መንግሥት ያለ ምንም ጥያቄ እጅግ በጣም ከተከበሩት ባለ ማዕረጎች አንደኛው ነበር፡፡”

በ1799 ዓ. ም. ከግሪክ ወደ ሩሲያ በመመለስ ዩክሬን ውስጥ ከርሶን ከተማን እንድትመሠረት አደረገ፡፡ የከተማዋ ገዥም ሆኖ ነበር፡፡ በመጨረሻ የደቡብ ሩሲያ ገዥ ከነበረው ከታላቋ ከቴሪን ባል ከካውንት ፖተምኪን ጋር ተጣላ፡፡ በእርግጥ ንግሥቷ ከኢቫን ጋኒባል ጎን ቆማ በመከላከል አሸናፊ ሆነ፡፡ ሆኖም ግን ኢቫን በራሱ ውሳኔ የመንግሥት ሥራ ትቶ የአባቱን ርስት እያሳረሰ በመኖር ላይ ሳለ በ1801 ሞተ፡፡

ጀነራል ኢቫን በሞተ ጊዜ ትንሽ ወንድሙ ኦሲፕ (ዮሴፍ) ጋኒባል የባህር ኃይል መኮነን ሆኖ በጥቁር ባህር ምድብ (ፍሊት) ይሠራ ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም ለበርካታ ዓመታት በሜድትራኒያን አካባቢ ቅኝት ሥምሪት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ኦሲፕ (ዮሴፍ) ቁንጅናዋ ከሁሉም የተውጣጣ ግን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ውሀዋ በይበልጥ የሚያደላ፣ የደም ገንቦ የምትባል እጅግ በጣም ውበት የረበበባት ልጅ ነበረችው፡፡ ሥሟ ነዲጃ ይባላል፡፡ ነዲጃ ሥራ ስትይዝ የቅርብ ተጠሪዋ አጎቷ ጀነራል ኢቫን ጋኒባል ነበር፡፡ የሩሲያውን መሥፍን (ባላባት) ሰርጌቪችን ስታገባም አባት ሆኖ ሠርጓን የደገሰላት (የደራት) እርሱ ነበር፡፡

ይህች ውቢቱ ነዲጃ ኦሲፕ ጋኒባል ነች እንግዲህ የአሌክሳንደር ፑሽኪን እናት!! ሶፍያ ኤ.ኬ. ሮትኪርክ (1746-1797) የተባለ ጀርመናዊ ፀሐፊና የታሪክ ተመራማሪ አግብታለች፡፡ ሮትኪርክ የጀነራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባልን የሕይወት ታሪክ በጀርመንኛ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ ፅፎ አሳትሞታል፡፡ ሥራው በጀነራል ጋኒባል ቃለ-መጠይቅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመሆኑም ሥራው ፑሽኪን የታላቁ ጴጥሮስ ሙር (ባሪያ) (The Moor of Peter the Great) በሚል ርዕስ የፃፈውን ጨምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በተለያዩ መስኮች በሚገኙ ምሁራን ዘንድ በሠፊው በዋነኛ ዋቢ ምንጭነት እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ በስተቀር የሌሎቹ የጋኒባል ልጆች ታሪክ ብዙ አይታወቅም፡፡ ይሁንና

በብዙዎቹ የታሪክ መፃህፍትና የምርምር ሥራዎች ተጠቅሶ እንደሚገኜው ከጀነራል ጋኒባል አብራክ የወጡ የልጅ ልጆቻቸው በእንግሊዝ ሀገር፣ ለምሳሌ፡- ናታሊያ ግሮስቬነር፣ የዌስትማስተሯ ደችስና እህቷ፣ አሌክሳንደር ሀሚልተን፣ የአቤርኮሟ ደችስ፣ ጆርጅ ማውነትባተን፣ የንግሥት ኤልዛቤጥ 2ኛዋ አጎት የሚልፎርድ ሀቨን 4ኛው… ቀጥተኛ የዘር ሐረግ ተዋረድ ያላቸው መሆኑን አስፍረውት እናገኛለን፡፡

ጋኒባል የሩሲያን ዘመናዊ የጦር ኃይል በዘመናዊ የውትድርና ሳይንስ አንፀዋል፡፡ የሩሲያን ዘመናዊ የጦር ኃይል ሠፈሮች አንፀዋል፡፡ ሩሲያ በ18ኛው እና በ19ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ በተለያዩ ክፍሎች የነበሯትን ምርጥ የጦር መሪዎች ያስተማሩትና ያሰለጠኑት ጀኔራል አብርሃም ጋኒባል ናቸው፡፡

ጀነራል ጋኒባል በዘመናቸው የወጣቶችን ስሜትም በእጅጉ ማርከዋል፡፡ ይህ ወጣት የጎረቤታቸውና የተማሪያቸው የሜጀር ጀነራል ቫሲሌቪች ልጅ ነበር፡፡ መሉ ስሙ አሌክሳንደር ቫሲሌቪች ሱቮሮቭ ይባላል፡፡ ሱቮሮቭ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በውትድርና ሙያ መሠማራትን ይፈልግ ነበር፡፡ በሁሉም የትምህርት መስኮች ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡ ልጁ እጅግ በጣም አንባቢና ያነበበውን የላቀ የማስታወስ ችሎታው ሁሉንም በእጅጉ የሚያስደንቅ ተማሪ  ነበረ፡፡ በተለይም ወታደራዊ ነክ የሆኑ የታሪክና የእውቀት መፃሕፍትን አንብቧል፡፡ ሱቮሮቭ ለአባቱ “ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ወታደር እሆናለሁ” እያለ ምኞቱን ይገልጽ ነበር፡፡ አባቱ ግን የነበራቸው ፍላጎት ልጃቸው በውትድርና ሳይሆን በሲቪል ሙያና ሥራ እንዲሰማራ ስለነበር ከልጃቸው ጋር  ጭቅጭቅና አለመግባባት ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ አባትየው አብርሃም ጋኒባልን “ምን ባደርግ ይህን ምኞቱን ማስቆም እችላለሁ?” ብሎ ምክር ጠዬቃቸው፡፡

ጀነራል ጋኒባል ወጣት አሌክሳንደር ሱቮሮቭን ሲያነጋግሩ በአንድ ስዓሊ ምናብ በ1888 ዓ.ም. የተቀረፀ ምስል

ወጣቱ ሱቮሮቭም ለጀነራል አብርሃም የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ እርሳቸውም እንደ ጓደኛ ያዩት ነበር፡፡ የልጁን  ተሰጥኦና ፍላጎት በጥልቅ ያውቁ ነበር፡፡ ስለዚህ ለአባቱ “‹ምርጫውን አክብርለት፤ በቀር ሕይወቱን ታበላሻለህ›” ብለው ምክር ሰጡት፡፡ አባቱም ምክሩን ተቀበለ፡፡ ሱቮሮቭም ወደሚፈልገው ውትድርና ዓለም ተሰማራ፡፡ በ60 ጦርነቶች ተዋግቶ/አዋግቶ በሁሉም ድል ተቀዳጅቷል፡፡ የቱርክ ኦቶማንን ጦር ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ለአንዴም ለሁሌም እንዳይስፋፋ ቅስሙን ሰብሮት ቀርቷል፡፡ ሱቮሮቭ 14 የጦር ሜዳ ድል መዳሊያ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ በ18ኛው ምዕተ-ዓመት ተወዳዳሪ የሌለው የሩሲያ ብሔራዊ ጀግና ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ንጉሥ ሎዊስ 17ኛው ‹የሩሲያው ጎራዴ› (‘The sword of Russia’) ሲል ሰይሞታል፡፡ የሱቮሮቭ ታሪክ ሲነሳ የጀኔራል አብርሃም ጋኒባል ለአባቱ “‹ምርጫውን አክብርለት፤ በቀር ሕይወቱን ታበላሻለህ›” ብለው ምክር የሰጡት እንደ ትእምርተ-ምሳሌ ዘወትር ይጠቀሳል፡፡ 

በተለይም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንዳንድ ‹ምሁራን› በታሪክ ሽሚያ ውስጥ ግብተው ይታያሉ፡፡ “ጋኒባል ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ የካሜሩን ተወላጅ ናቸው” የሚል መከራከሪያ ነጥብ አድርገው በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንድ ሱልጣንና ሽማግሎች “የሌባ ዓይነ ደረቅ” እንዲሉ “የእኛ ደም ጠብታ፣ የእኛ ሥጋ ቁራጭ፣ የእኛ አጥንት ፈላጭ” ነው በሚል መልክ ምሥክርነት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ አንዱ ነው፡፡ ሌላዋ N. K. Teletova 2006, 46) ዋነች፡፡ ሌላው በ1996 ምርምር አደረኩ የሚለው ዲዮዶኔ ግናማንኮ የተባለው ሲሆን “ጋኒባል ምን አልባትም በትክክል ከደቡብ ከቻድ ሀይቅ በስተደቡብ በካሜሩን ውስጥ በሎጊን ወንዝ ዳርቻ የሎጎን-በርኒ (Logone-Birni ) ሱልጣኔት ተወላጅ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ጋኒባል የሩሲያ የመሳፍንትነት (nobility) የማዕረግ ደረጃ እንዲሰጠው እና የዝሆን አርማ ያለው ወታደራዊ የደንብ ልብስ (ኮት ፍ አርምስ) የማግኜት መብት እንዲረጋገጥለት  በ1742 ዓ. ም. ለንግሥት ኤልዛቤጥ በፃፈውና ኦፊሴላዊ የማመልከቻ ደብዳቤ ሰነድ “FVMMO” በሚል የተቀረፀው ሚስጢር የተሞላበት ማህፀረ-ቃል ከኮቶኮ ቋንቋ የሚሰጠው ትርጉም “የትውል ሀገር (homeland)” የሚል ነው፡፡

ይህን ሀሳብ ራሱን ‹የታሪክ ምሁር ነኝ› የሚለው ሁግ ሳንደርስ ሲያቀነቅነው ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ጀነራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ከመረጡት የዝኆን ዓርማ ሥር ‹FVMMO› በሚል የተቀረፀው የላቲን ማህፀረ-ቃል በትእምርተ-ትርጉም የተጠቀሙበት አገላለፅ ከላይ በስህተት ከተገመተው ፍች በእጅጉ የተለየ መሆኑን እንዲህ ስትል አብራርታዋለች፡፡ ይህም፡- “ጋኒባል የተጠቀሙበት የላቲን ማህፀረ-ቃል፡- ‹Fortuna Vitam Meam Mutavit Oppido›” የሚለውን ሀሳብ የሚወክል ነው፡፡ ይህም በእንግሊዝኛው “Fortune has changed my life entirely” ማለት ሲሆን ወደ አማርኛ ሲተረጎም፡- “ዕድል ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ቀየረችው” እንደማለት ነው፡፡ ንግሥት ኤልዛቤጥን የወታደራዊ የጡረታ ደንብ ልብስ በጠየቁበት ደብዳቤም ጋኒባል ‹አፍሪካዊ› (‹ኢትዮጵያዊ›) መሆናቸውን የትውልድ ቀያቸውም ‹ሎጎን› የምትባል መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንም በተመሳሳይ በፔትሮቭስኮይ፣ በቅዱስ ፒተርስበርግ በሚገኜው የመታሰቢያ ሐውልታቸው ላይ በማያሻማ ሁኔታ፡- “ሙሉ ስማቸው፡- አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል፣ የትውል አገራቸው፡- ኢትዮጵያ፣ ልዩ ሥፍራው፡- ምድሪ ባህሪ – ኤርትራ፣ የሞቱበት ቀንና  ዓ.ም.፡- ግንቦት 14 ቀን፣ 1781፣ ቅዱስ ፒተርስበርግ፣ ዜግነት፡- ሩሲያዊ፣ ተቀያሪ ስም፡- ሀኒባል፣ ፔትሮቭ” በሚል ተቀርፆ በግልጽ የምናየው ሀቅ ነው፡፡ ይህን በሀውልታቸው ላይ ሩሲያውያን ሲቀርፁት ባለማወቅ ወይም በነሲብ አልነበረም፡፡ እነ ቮልቴርን፣ አሌክሳንደር ፑሽኪንና ኤ.ኬ. ን ጨምሮ የሕይወት ታሪካቸውን የፃፉት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ምሁራንና ተንታኞች ሁሉ የአብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል የየት-መጥ ታሪክ “ሰሜን ኢትዮጵያ ነው” ማለታቸው ከእውቀት እንጂ ከድንቁርና የመነጨ አይደለም፡፡ የሩሲያው ዛር ታላቁ ቀዳሚዊ ጴጥሮስ ክርስትና አንስቶ እንደ ልጅ ከቤተመንግሥቱ ያሳደጋቸው፣ ያስተማራቸው፣ በአካል እስቲደረጁና በአእምሮ እስቲበስሉ አብርሃምን በጉጉት ዓይን ዓይን ያያቸው የነበረው በታሪክ ከኦቶማን ቱርክ ተስፋፊ ኢምፓየር ወረራ ራሷን ስትከላከል ከነበረችው ኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግንኙነት ለመፍጠርና ለማጠናከር ከነበረው ሩቅ ዓላማ ጋርም የተሳሰረ እንደነበረ መዘንጋት የለበትም፡፡

በመጀመሪያው ክፍል ለመግለፅ እንደሞከርኩት ቀጥሎ በቀረበው እንግሊዛዊው ሄነሪ ሳልት በ1809 በሠራው ሠፊ ካርታ ላ(ሎ)ጎን ሳንድራ በኤርትራ ውስጥ በመረብ ወንዝ ዳርቻ በስም ተጠቅሳ ተመልክታለች፡፡

ማፕ፡- በሄንሪ ሳልት በ1810 ዓ.ም. የተዘጋጀ፡፡ ላጎን በኢትዮጵያ ውስጥ በዛሬይቱ ኤሪትራ ላጎ-ሳንድራ ተብላ ትጠራለች፡፡

ራሳቸውን በመጠየቅና ማስታወሻዎቻቸውንና ደብዳቤዎችን በመጠቀም በ1780ዎቹ የመጀመሪያውን የሕይወት ታሪካቸውን በጀርመንኛ ቋንቋ የፃፈውን የልጃቸው የሶፍያ ባል አዳም ካርፖቪች ሮትኪርክንና ፑሽኪንን ጨምሮ ከሁለት ምዕተ-ዓመታት በላይ የቁጥሩን ብዛት ከዚህ ላይ ለመዘርዘር የሚያዳግት የምሁራን ሥራዎች የአብርሃምን ኢትዮጵያዊነት አስረግጠው አስቀምጠውታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ማረጋገጫዎች እያሉ ነው እንግዲህ አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ካሜሩናዊ ናቸው ወደ መባል የተሄደው፡፡ ይህ ብቻ አይደልም፡፡ አብርሃም በወጣትነታቸው ወታደራዊ ሳይንስ በተማሩበት በፈረንሳይ፣ በፓሪስና በላፌረቴ በዲዮዶኔ ግናማንኮ እና በሁግ ብሪያን አጋፋሪነት የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትርና ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ምሁራንና ከተለያዩ ሀገሮች የተጋበዙ ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም የሎጎን-ቢርኒ አካባቢ የሙስሊም መሪና ሽማግሎች የተሳተፉበት ‹የእወቁልን› ዓይነት ዓላማ ያለው ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንስ በ2001 ዓ.ም. ያካሄዱት፡፡ በዚህ ጉባኤ የሩሲያ ዲፕሎማቶች አልተጋበዙም፡፡ የኢትዮጵያም እንደዚሁ፡፡ ለምን? ታሪኩ ውሸት (መሠረተ-ቢስ) ነውና መልሱ ግልፅ ነው – ከተቃውሞ ነፃ መሆን ነበረበት፡፡ በአጭሩ በቅርቡ (እኤአ) በ2006 ዓ. ም. ካቴሪን ኔፖምኒያ ሽቺ እና ሉድሚላ ኤ. ትሪጎን፡- “ሞስኮ ውስጥ በፓትሪስ ሉሙምባ ዩኒቨርሲቲ ያጠና ግናማኮ የተባለ የቤኒን ተወላጅ ምሁር እስከዛሬ ምሁራን እንዳረጋገጡት የአብርሃም ጋኒባል የየት-መጥ ታሪክ መነሻ አቢሲኒያ ወይም ኢትዮጵያ ሳትሆን ከመካከለኛው አፍሪካ የቻድን ሀይቅ ከምታዋን (በአሁኑ ጊዜ በካሜሩን ግዛት አካል ከሆነች) ቦታ መሆኑን ‹በምርምር ግኝት ደረስኩበት› የሚል ድፍት የሞላበት አቋም ይዟል፡፡ ይህ ዓይነቱ አቋም በልብወለድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ግኝቱ ዓይን አውጣ ቅሌት ይባላል፡፡ ይህ የጋኒባልን ኢትዮጵያዊ ታሪክ ደብዛ ለማጥፋት ሲባል ለግናማኮ የገንዘብ ምንጭ ያገለገለ የ‹ማፊያ› ሥራ ይመስላል” ሲሉ መታዘብ ብቻ ሳይሆን በኃይለ-ቃል አውግዘውታል፡፡ 

የአብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ስብዕና እና ውጣውረድ የተሞላበት የሕይወት ታሪክ ከሁለት ምዕተ ዓመታት በላይ የባህል ማለትም የታሪክ፣ የሥነፅሑፍ፣ የኪነጥበብ ሰዎችን ወይም የአያሌ የሕይወት ታሪክ ፀሐፍትን፣ የደራስያንን፣ የፀሐፌ-ተውኔትን፣ የፊልምና የብዙ ሰዓልያንን ምናባዊ ትኩረት አግኝቶ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ቋንቋዎች፣ በተለያዩ የጥበብ ሰዎች ግጥሞች፣ ልብወለዶች፣ የትራጀዲና የኮሜዲ ደራማዎች፣ ፊልሞች፣ ስዕሎች፣ ወዘተ፣ ቀርበዋል፤ ተዘጋጅተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ፑሽኪን የታላቁ ጴጥሮስ ባሪያ (1837) (Moor of Peter the Great) በሚል ርዕስ ያቀረበው ምፀታዊ የግጥም ድራማ ነው፡፡ ይህ ሥራ ለብዙ የጥበብ፣ የምርምርና የታሪክ ሥራዎች፣ ለፊልም መነባንቦች ዋና ምንጭ ሆኖ አገልግሏል/በማገልገል ላይም ይገኛል፡፡ ሩሲያውያን በርካታ ፊልሞችንና የኮሜዲ ድራማዎችን ሠርተውበታል፡፡ ከእነዚህ ወስጥ “ኅያው ፑሽኪን” የሚል ርዕስ የተሠራው ታሪካዊ ዶክሜንታሪ ፊልም ውስጥ “አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ወደ ሀገሩ ተመልሶ ገባ” የሚል ገቢር የያዘ የድርጊት መቼቱን በዋናነት በኢትዮጵያ ውስጥ ጎንደርን እና ባህርዳርን በማድረግ የቀረበው ታሪካዊ ዘጋቢ ፊልም አንዱ ነው፡፡

ጋኒባል የበርካታ ሰዐሊያንን ምናባዊ ዕይታም አግኝተው ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም በሙዚየሞች የተቀመጡ ብዙ የውሀ፣ የዘይት፣ ወዘተ. ስዕሎች ይገኛሉ፡፡ ከስዕሎቹ መካከልም በፈረንሳዊው ፔሬ-ዴኒስ ማርቲን የሌስናያ ጦርነት በሚል እና በአድርያን ስኩንቢክ የተሳሉት አብርሃም ጋኒባልን የሚያሳዩ የሸራ ስዕሎች እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን የጥበብ ሰዎች በኩል እስከ ዛሬ ድረስ የተሠራ ፊልም፣ ድራማ ወይም የልቦለድ መጽሐፍ ግን አናገኝም፡፡ ወደ ፊት የኢትዮጵያውያንን ትኩረት በእጅጉ ሊስብ ወይም ሊያገኝ ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በዲፕሎማሲው በኩልም ተመሳሳይ ድክመት ይታያል፡፡ ሩሲያውያን ለጀነራል ጋኒባል ያላቸው አመለካካት እጅግ በጣም አስደናቂ ነው፡፡ ምን አልባትም ይህን በምሳሌ ለመግለፅ ያህል፡- (እኢአ) በታኅሳስ ወር፣ 2012 ዓ.ም. ወደ ናዝሬት ለሥራ ሄጀ ሩሲያ ውስጥ ፒተርስበርግ ከተማ ከ30 ዓመታት በላይ ነዋሪ የሆኑ ዘመድ ጠይቀው ለመመለስ ከመጡ አንድ ኢትዮጵያዊ ጋር በጓደኛየ አማካይነት ተዋወቅሁ፡፡ ወግን ወግ ያመጣዋል ነውና በጨዋታ መሀል “ሩሲያውያን በሀገራቸው ለምትኖር ለእናንተ (ለኢትዮጵያውያን) ያላቸው አመለካከት ምን ይመስላል?” ብየ ጠየቅኳቸው፡፡ “ከሌላው ስደተኛ ይልቅ ለእኛ ኢትዮጵያውያን በጣም የተለየ አክብሮት አላቸው” ብለው መልስ ሰጡኝ፡፡ ከዚያ ፈራ ተባ እያልኩ (እየተጠራጠርኩ) “… ስለ ጀነራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ታሪክስ ያውቀሉ ወይ?” አልኳቸው፡፡ ከዚያ በፈገግታ ትኩር ብለው አዩኝና “የሚገርም ነው! ሩሲያውያን ለእኛ የሚሰጡን የተለየ አክብሮት ለጀነራል ጋኒባል ካላቸው አክብሮት የመነጨ ነው፡፡ የጀነራል ጋኒባልን ስብዕና፣ ባሕርይ፣ እንደ ተምሳሌት አድርገው ያዩታል፡፡ ጀነራሉን ሀቀኛ፣ እውነተኛ፣ ታማኝ፣ ጀግና፣ ከውሸት ከሙስና የራቁ አድርገው ያዩዋቸዋል፡፡ እኛንም የጋኒባል ዘሮች፣ የጋኒባል ሀገር ሰዎች፣ የፑሽኪን ዘመዶች፣ እንዲህ እያሉ እኛንም እንደ እውነታኛ፣ እንደ ታማኝ … ያዩናል” ብለው መለሱልኝ፡፡ ይህ አእምሯዊ ኢትዮጵያዊ ምስል (image) ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ላላት፣ ለወደፊትም ለሚኖራት፣ መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ስላለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲነገር የምንሰማው ጀነራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባልን ሳይሆን የልጅ ልጃቸውን አሌክሳንደር ፑሽኪንን እንደ ማስተሳሰሪያ ከመጥቀስ ያለፈ ሆኖ አለማግኜታችን ትልቅ ድክመት ያደርገዋል፡፡

በአጠቃላይ የአብርሃም ጋኒባልን ታሪክ ሩሲያዊው ዩሪ ታይናቭ (2006) “ዘ ጋኒባልስ” በሚል ርዕስ አስደናቂ በሆነ አገላለጽ ያሰፈረውን ጽሑፍ በይበልጥ መሠረት በማድረግ ለማጠቃለል እወዳለሁ፡፡ የአብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ታሪክ ከ17ኛ ምዕተ-ዓመት መጨረሻ እስከ 18ኛው ምዕተ-ዓመት መገባደጃ ድርስ የነበረውን የብዙ ሀገሮች ታሪክ የሚያወሳ ትርክት ያለው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ እንጀምር፡፡ አብርሃም በሰሜን ኢትዮጵያ በኤርትራ (በምድሪ ባህር)፣ በሀማሴን፣ በትግሬዎች ሀገር፣ በመረብ ወንዝ በስተጀርባ በምትገኝ ሎጎ (ዛሬ ሎጎ-ሳርዳ) በምትባል መንደር ከመሳፍንት፣ ከባላበት፣ ከአካባቢው ገዥ ቤተሰቦች፣ በ1796 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ በዚች ሎጎ-ሳርዳ መንደር በኢትዮጵያውያን ቀርቶ በአረብ እና በቱርክ ተጓዥ ነጋዴዎች ዘንድ የሚታወቅ አንድ እጅግ ግዙፍ የሆነ የሲንካሞር ዛፍ ነበረ፡፡ የዚህ ዛፍ ጥላ ወደ ጎን 36 ሜትር፣ ዙሪያውን ደግሞ 360 ሜትር የሚሸፍን ጥላ ነበረው፡፡ እንደ ዕፀ-ገነት የተፈጥሮ ሽቶ ይረጫል፡፡ እንደ ዕጣን አየሩን ያውድ ነበር፡፡  በዚህ ገነት ዛፍ ላይ በሽህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወርቃማ እርግቦች ይሰፍሩበት ነበር፡፡ ይዘምሩበት፣ ይደሰቱበት፣ ነበር፡፡ ተጓዡ ነጋዴ ሁሉ ይቀጣጠርበት፣ ያርፍበት፣ ያድርበት፣ ይመገብበት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ቱርኮች ኢትዮጵያን ወርረው በቁጥጥር ሥር ለማዋል ይቋምጡና ይጥሩም ነበር፡፡ በሽህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ሀገራቸውን ከወረራ ለማዳን በመሰብሰብ፣ በመታደም፣ ይበክሩ ይዘክሩና ስልት ያወጡበት ነበር፡፡ አብርሃም የተወለዱት ከዚህ ዝነኛ ዕፀ-ገነት ዛፍ ጥግ ከሚገኝ መንደር ስለነበር ከትልቅ ወንድማቸው፣ ከትልቅ እህታቸውና ከአንድ የጎረቤታቸው ልጅ ጋር ሲጫዎቱ የቱርክ ነጋዴዎች አፍነው በመውሰድ የባርነት ቀንበር ጫኑባቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ቱርኮች በተለያዩ ሀገራት የተስፋፉበት፣ በተለያዩ ሀገራት ሁሉ የሰውን ልጅ ባሪያ በማድረግ በመሸጥ በመለወጥ ሀብት ያጋብሱ ነበር፡፡ እነ አብርሃምንም አፍነው ወደ ምጽዋ ወሰዷቸው፡፡ ይህ የአብርሃም ታሪክ እንግዲህ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው፡፡

ቱርኮች እነ አብርሃምን ወደ ምጽዋ ከወሰዷቸው በኋላ በመርከብ ጭነው በስቃይና በመከራ በማጓዝ በዘመኑ የቱርክ ኦቶማን ኢምፓየር ዋና ከተማ ወደ ነበረችው ወደ ቆንስጣንጢኖፕል ወሰዷቸው፡፡ ይህ ታሪክ እንግዲህ በዘመኑ ተንሰራፍቶ የነበረው የቱርክ ኦቶማን ኢምፓየር የታሪክ አካል መሆኑ ነው፡፡

እነ አብርሃም ቱርክ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል በባርነት ሲማቅቁ ከቆዩ በኋላ በጊዜው ቆንስጣንጢኖፕል ይሰሩ በነበሩ የሩሲያ ዲፕሎማቶች አማካይነት በሚስጢር ታፍነው (ተሰርቀው) ወደ ሩሲያ – ወደ ሞስኮ ተወሰዱ፡፡ ከዚህ በኋላ የሩሲያው ዛሩ፣ የታለቁ ቀደማዊ ጴጥሮስ፣ ቤተኛ ሆነው፣ ከባርነት ቀንበር ተላቀው፣ ትምህርት የመቀጠላቸው ታሪክ የሩሲያን ታሪክ የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ከዓመታት በኋላም በፈረንሳይ ሀገር የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ለመማር የቆዩበት የወጣትነት ዘመን ገጠመኝ ከፈረንሳይ አልፎ የስፔንን ታሪክ ጭምር የሚጠቅስ ሆኖ እናገኛለን፡፡

አብርሃም ትምህታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሩሲያ ተመልሰው ያሳለፉት ድል የተሞላበት፣ የገነቡት ስብዕና፣ የገጠማቸውና ያለፉበት ውጣውረድ የተሞላበት የሕይወት ጎዳና፣ የዘረኝነትን ከንቱነት በማረጋገጥ ለዓለም ያበረከቱት ትሩፋት፣ በቤተሰብ በኩልም ያፈሯቸው ፍሬዎች፣ በተለይም ለዘመናዊው የሩሲያ ሥነ-ፅሑፍ መሠረት የጣለውንና ሁለንተናዊ የሰው ልጆች ሰብአዊነት ተሟጋች የአሌክሳንደር ፑሽኪንን ታሪክ ሁሉ አጣቅሶ በመያዝ የ18ኛውንና የ19ኛውን መጀመሪያ ምዕተ-ዓመታት የሩሲያን ታሪክ የሚያካትት ሆኖ ይገኛል፡፡  

ስዕል፡- አልክሳንድር ስረጌቪች ፑሽኪን – በ1827 በ ኦ.ኤ. ኪፕረንስካይ የተሳለ፡፡

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories