የኢትዮ-ሱዳን የደህንነት ተቋማት ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር ያለመ ምክክር አደረጉ

አዲስአበባ፡ የዓባይ፡ልጅ፣ መስከረም 4 2015

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የሱዳን ሪፐብሊክ አቻው ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር የሚያከናውኗቸውን ሥራዎችና ስምሪቶች  አጠናክረው ለመቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በሱዳን  ሪፐብሊክ ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  ዳይሬክተር ጀነራል ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል አሕመድ ኢብራሂም  ሙፋደል የተመራ የልዑክ ቡድን ዛሬ በተቋሙ ጉብኝት አድርጓል፡፡ ከጉብኝቱ በኋለ በነበረው መድረክም የሁለቱ ሀገራት እንዲሁም የቀጣናውን ወቅታዊ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች የሚመለከቱ አጀንዳዎች ተነስተው ምክክር ተደርጓል፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ተመሳሳይ ባህል፣ቋንቋ፣ ሃይማኖት እንዲሁም ሰፊ ድንበር የሚጋሩ በመሆናቸው የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ አድርጎታል፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኘውን ትሩፋት በጋራ በመቋደስም ትስስሩን ለማጠናከር  ይሠራል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት  ከሱዳን ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  ጋር መረጃ በመለዋወጥና በአቅም ግንባታ መስኮች የሚያደርገውን ትብብር  በማጠናከር ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች  እንዲሁም ሕገወጥ የገንዘብ፣ የመሣሪና የሰዎች ዝውውር የሚያስከትሉትን ተፅዕኖዎች ለመቀነስ በትብብር እንደንሚሠራ  አቶ ተመስገን  ገልጸዋል፡፡ በተለይ በቀጣናው ከፍተኛ ሥጋት የሆነውን ሽብርተኝነት ለመከላከል የሚካሄዱ የመረጃ ልውውጦችንና የጋራ ስምሪቶችን በማጠናከር በደም የተሳሰሩትን  የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ደኅንነት ለማረጋገጥና ተጠቃሚነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ  የትብብር አድማሶችን ለማስፋት ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡


ኢትዮጵያ የሱዳን ወሳኝ ስትራቴጂክ አጋር ሀገር ሆና እንደምትቀጥልመንግሥት በጽኑ እንደሚያምን ያነሱት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር  ጀነራል አቶ ተመስገን፤ በሁለቱ ሀገራት ብሎም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በመረጃና በጸጥታ ተቋማቶቻቸው መካከል የሚደረገውን ትብብር እና አጋርነት በማጠናከርም የጋራ የደኅንነት ሥጋቶችን ለማስወገድ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
የሱዳን ሪፐብሊክ ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል አሕመድ ኢብራሂም ሙፋደል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የመረጃና ደኅንነት ተቋም ያደረጉት ጉብኝት በሪፎርሙ ሂደት ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን በርካታ የሚጋሯቸው ጉዳዮች በመኖራቸው የሁለቱ ሀገራት የመረጃ ተቋማት የጋራ የደኅንነት ሥጋቶችን ለማስወገድ በትብብር መሥራታቸውን እንደሚያጠናክሩ የጠቆሙት ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል አሕመድ ኢብራሂም፤ በተለይ ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊም ሥጋት የሆነው ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚደረጉ የአጋርነት ሥራዎች  እና ኦፕሬሽኖች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡ የመረጃ ልውውጥም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚዋሰኑበት ድንበር ረጅም በመሆኑ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ጨምሮ የተለያዩ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን መከላከል እንደሚገባ በምክክሩ መነሳቱን የጠቆሙት ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል  አሕመድ ኢብራሂም፤ የወሰን አካባቢዎችን ሰላም በማረጋገጥ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር የሚገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የሱዳን ሪፐብሊክ አቻው ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  በቀጣይም ቋሚ የጋራ  መድረኮችን በማዘጋጀት ትብብራቸውንና አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የላከልን መረጃ ያመለክታል።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories