ቻይና ያደፈጠችው ነብር
ቻይና ተዓምራዊ በሚባል ፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝና በድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ከፍተኛ ድል ያስመዘገበች ጠንካራ ሀገር ናት። የኢኮኖሚ እድገቷን የተገነዘበው የመንግሥታቱ ድርጅት እኤአ በ2018 ባቀረበው ሪፖርት እንደገለጠው በዓለም የድህነት ቅነሳ ታሪክ 76 ከመቶ የሆነው ድል የተመዘገበው በቻይና ነው። ቻይና በነደፈችው መርሐ ግብር መሠረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ከፍ ወደ አለ የኑሮ ደረጃ በማሸጋገር ላይ ትገኛለች፡ በእኛ ሀገር ደረጃ የድህነት ቅነሳ መርሐ ግብር (Poverty Reduction) የተነደፈ ቢሆንም እንደ ቻይና መንግሥት ወደፊት ብዙ የተራመደ አይደለም። ቻይና ከአምስት ዓመት በፊት የነደፈችው ስትራቴጂያዊ እቅድ ‹‹ድህነትን መቀነስና የሕዝቡን ኑሮ ከፍ ወደ አለ የኑሮ ደረጃ ማድረስ (Poverty Alleviation)›› በመባል ይታወቃል።
በዓለፉት አምስት ዓመታት (እኤአ ከ2012- 2017) 66 ሚሊዮን ከሆኑት የገጠር ድሀ ነዋሪዎች ውስጥ የሁለት ሦስተኞቹ የገቢና የኑሮ ሁኔታ ተለውጧል። በቅርቡ ቤጂንግ ውስጥ በተካሄደ የጋዜጠኞች ሥልጠና ላይ በቻይና በዓለም የድህነት ቅነሳ ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ዶክተር ሁ ሊፒንግ «ድህነት ቅነሳ በቻይና ገጠሮች፤ ፖሊሲውና ተግባራዊነቱ» በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳስረዱት የቻይና መንግሥት ፖሊሲ በተጠና መልኩ ሥራ ላይ በመዋሉ ድህነትን ከቻይና ምድር ፈጽሞ ለማጥፋት በተደረገው ትግል አስተማማኝ ውጤት በመመዝገብ ላይ ይገኛል። ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ በተያዘው ዕቅድ መሠረት እኤአ ከ2011 ጀምሮ የቻይና መንግሥት በ30 ክፍላተ ሀገር ውስጥ ከገጠር ድሀ ቤተሰብ ለመጡና የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለሚማሩ ልጆች 16 ቢሊዮን ዩዋን በጀት መድቦ ምሳቸውን በነጻ እንዲመገቡ በማድረግ ላይ ሲሆን በተመሳሳይ እኤአ ከ2014 ጀምሮ በ30 ክፍላተ ሀገር ውስጥ በሚኖሩና በ134 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ 32 ሚሊዮን የገጠር ድሀ ተማሪዎች መንግሥት 47.2 ቢሊዮን ዩዋን መድቦ የዕለት ምግባቸውን እያገኙ እንዲማሩ አድርጓል ።
በዚህ መርሐግብር በሦስት ዓመት ውስጥ በተደረገ ክትትል ከ5-15 ዓመት እድሜ የሞላቸው ተማሪዎች በክብደትም፤ በቁመትም አስተማማኝ ለውጥ አምጥተዋል። በቻይና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ መሠረት ያልተማረው የሕዝብ ቁጥር እያነሰ ሄዷል። የሕፃናትና የእናቶች ሞት ቀንሷል፤ በሁሉም የገጠር መንደሮች መቶ በመቶ በሚባል ሁኔታ የአስፋልት መንገዶች ተሠርተዋል። ለዚህም የጉዋንግሂ፣ የዶንግሻሂና የሻንዶንግ ክፍላተ ሀገር፤ የጋንሱ፣ የፌንግ ቀበሌና የጂያንግሂ ገጠር የአስፋልት መንገዶች ተጠቃሾች ናቸው፤ አስቸጋሪና ለሕይወት አደገኛ የነበሩ የገጠር ቤቶች ሁሉ በዘመናዊ አሠራር ተቀይረዋል። ለዚህም የድሮውንና አሁን ያለውን ቤት በንጽጽር ማየት ይቻላል። እኤአ በ2020 ይደረስበታል ተብሎ የተያዘው ዕቅድ ተግባራዊ ሲሆን የምግብና የልብስ ዋስትና ይረጋገጣል፤ መሠረታዊ ትምህርት መቶ በመቶ ለሁሉም ይዳረሳል።
የሕክምናና የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ተግባራዊ ይሆናል።የድሀ አርሶ አደሮች ገቢ ከብሔራዊና ከማዕከላዊ ገቢ በበለጠ በድህነት በተጠቁ አካባቢዎች (ለምሳሌ ለም መሬት የሌላቸውና በተራራ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች) ሀብት ያድጋል፤በገጠር የሚኖሩትና በቁጥር 55.75 ሚሊዮን የሆኑትና በድህነት የተመቱት ድሀ አርሶ አደሮች ያካባቢያቸውን የድህነት ድባብ ያጠፋሉ። ይህ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ድህነት በቻይና ተረት ይሆናል ማለት ነው፤ ከዚህም በላይ እኤአ በ2025 ይደረስበታል ተብሎ የተነደፈው ዕቅድ ቻይና አሜሪካን በኢኮኖሚ ቀድማ ለመራመድ የሚያስችላት ነው። እኤአ ከ1996 ጀምሮ የቻይናን የኢኮኖሚ ልማትና እድገት በማፋጠን ላይ ያሉት በየቦታው የተቋቋሙትና በመንግሥት ምክር ቤት የድህነት ቅነሳና የኢኮኖሚ እድገት አመራር አባላት የሆኑት ባለሙያዎች ናቸው። የስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ዋና ዓላማም የድህነት ቅነሳ በየትኛውም ደረጃ ዋነኛ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እንዲተገበር መረባረብ ሲሆን በዚህም በድህነት ቅነሳ ላይ ያተኮረው የልማት ዕቅድ ግቡን ይመታል ተብሎ ይታመናል።
በተጨማሪም ስትራቴጂው እኤአ ከ1994- 2000 ድረስ ተግባራዊ እንዲሆን የተዘረጋው የዕድገት፤ የልማትና የድህነት ቅነሳ መርሐ ግብር፤ ‹‹የቻይና ብሔራዊ ዕቅድ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን እኤአ ከ2001-2010 እና ከ2011-2020 ድረስ የተተለመውን የገጠር የድህነት ቅነሳ ዕቅድ ያጠቃልላል። ይህም በድህነት የሚኖሩ የገጠር አካባቢዎችን ሁኔታ በትኩረት በማጥናት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። በድህነት ቅነሳ ስትራቴጂው መሠረት በድህነት የሚኖሩ ሰዎች በጥናት ይለያሉ፡፡
ፀረ ድህነት እቅድ ራሱን ችሎ ይወጣል፤ ባለሙያዎች በተለያዩ ቡድናቸው ይመደባሉ። ፕሮጀክት ይቀረጻል፤ በጀት ይመደባል፤ ከድህነት ለመውጣት የሚያስችለው ፀረ ድህነት ስልት ተግባራዊ ሲሆን ድህነትን ለማጥፋት የታለመው ዓላማ ግቡን ይመታል። ይህ ዓይነቱ አሠራር በድህነት ቅነሳ ማሳያ (ሞዴል) በሆነችው በጉይጆ ክፍለ ሀገር በዌይኒነግ ቀበሌ የሚኖሩ ድሆቹ ተለይተውና ተጠንተው፤ መንግሥት ቤት ሠርቶ በነጻ ሰጥቷቸዋል፤ የምግብ ችግራቸው ተፈትቶላቸዋል፤ ትምህርት ቤት ተገንብቶላቸዋል፤ የሥራ እድል እንዲያገኙም ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል። ዶክተር ሁ ሊፒንግ እንዳስረዱት ሌላዋ በድህነት አረንቋ ውስጥ ትኖር የነበረችው በጋንሱ ክፍለ ሀገር የምትገኘው ወይናን ከተማ ናት። በአስከፊ ድህነት ውስጥ የነበረችው ወይናን አሁን የተመቻቸ ትራንስፖርትና የመረጃ ግንኙነት አላት፤ ከዚያ ዘግናኝ ድህነት ተላቃ በአሁኑ ሰዓት ደረጃውን የጠበቀ የግብርና ምርት ለመላ ቻይና በማቅረብ ላይ ትገኛለች። ይህች ከተማ እኤአ ከ2015 ጀምሮ በድህነት ቅነሳ ትኩረት ተሰጥቷት ድህነትን ያጠፋች ሞዴል ከተማ ተደርጋ እንድትታይ ተደርጋለች።
እኤአ ከ2016 ጀምሮ 10 ሺህ የኦንላይን መደብሮችን አዘጋጅታ በ6.4 ቢሊዮን ዩዋን የግብርና ምርቶቿን ከመሸጧ በተጨማሪ ለ7.18 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ፈጥራለች። በ750 ቀበሌዎች 980 የኦንላይን መደብሮችን ከፍታ የ150 ሺህ ሰዎችን ገቢ ለማሳደግ ችላለች። በተመሳሳይ በሻንዶንግ ክፍለ ሀገር በሂዜ ከተማ ዙሪያ በዩቼንግ ቀበሌ129 መንደሮች በድህነት ዓለም ውስጥ ይኖሩ ነበር። አብዛኞቹ ወጣት አባወራዎች ሚስቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና በእርጅና ውስጥ የሚገኙ ወላጆቻቸውን ትተው ሥራ ፍለጋ በየቦታው ይንከራተቱ ነበር። በአጋጣሚ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ፀጉር፤ ወንበርና ሥጋጃ የመሥራትና ፈትል የመፍተል ባህል አላቸው። በመሆኑም እኤአ ከ2015 ጀምሮ በሄንዝ ከተማ1‚803 የድህነት ቅነሳ ማሠልጠኛ ማእከላትን፤ 383 ድርጅቶችን በማቋቋም ለ191‚341 ሰዎች የቤት ውስጥ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
በዚህ የተነሣ 57‚685 ሰዎች ድህነትን ተሰናብተው የሀብት ባለቤቶች ሆነዋል። ድህነትን በአስካርባ (በካልቾ) መትተው ከአባረሩት ሰዎች ውስጥ 49‚724 ሴቶች፤ 519 የአካል ጉዳተኞች፤ 8653 አረጋውያን፤ ከእነዚህ ውስጥ 69 የሆኑት ከ80 ዓመት በላይ እድሜ የሆናቸው ዜጎች ይገኙበታል። ቻይና በድህነት ቅነሳ መርሐ ግብሯ ምንም የሌላቸውንና በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን ዜጎች ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ባላት ፅኑዕ ምኞት የተነሣ በሻንጋይ ከተማ ዓለም አቀፍ የድህነት ቅነሳ ጉባዔ የሚካሄድበት ማዕከል (International Poverty Reduction Center) ከፍታለች። በተመሳሳይ እኤአ ከ1980 ጀምሮ በቻይና ስለታየው የኢኮኖሚ እድገት ገለጻ ያደረጉልን ባለሙያ ሸንግሃኦ ቹ ናቸው።
በእርሳቸው ገለጻ መሠረት የቻይና ኢኮኖሚ በያመቱ 9.4 ከመቶ (በቢሊዮን ዩዋን) በማደግ ላይ ይገኛል። ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ሲሆኑ የገጠር አካባቢዎችም ወደ ከተማነትና ወደ ኢንዱስትሪ ዞንነት በመቀየር ላይ ናቸው። ይህ የከተማ ዕድገትና መስፋፋት ከአሜሪካ ጋር ሲነጻጸር በቻይና 60፤ በአሜሪካ ደግሞ 80 ከመቶ ነው። ቹ እንደሚሉት የአሜሪካ ኢኮኖሚ አንጻራዊ በሆነ መልኩ 15 በመቶ በማደግ ላይ ሲሆን ኢኮኖሚዋ ለዓለም ሲከፋፈል ከቻይና 16 ጊዜ ይበልጣል። አሁን ባለው ሁኔታ የቻይና ዓመታዊ ጂዲፒ 94 ከመቶ ሲሆን ቻይና ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ ታበረታታለች፤ የመንግሥትን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግም የበጎ አድራጎት ሥራ ትሠራለች። የቻይና ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው ቤጂንግ በዓለም አቀፍ የንግድ ገበያ ስለምትካፈል፤ የውጭ አገር ገበያም የቻይናን ምርት ስለሚፈልገውና ተወዳዳሪም ስለሆነች ነው። ቻይና በራሷ ውስጥም ትልቅ የገበያ ትሥሥር አላት። በመሆኑም ቻይና ወደ ውጭ የምትልከው ሸቀጥ ከፍተኛ ሲሆን ወደ ሀገሯ የምታስገባው ግን ጥቂት ነው።
ከእዝ ኢኮኖሚ ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ ተሸጋግራለች። እኤአ ከ1992 ጀምሮ የግል ሀብት እያደገ ነው። የመንግሥትና የግል ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ እንደ አሊባባ የመሳሰሉ የግል ኩባንያዎች መፈጠራቸው ከዚሁ የተነሳ ነው። የገንዘብ ዝውውር ከሕዝቡ ተጠቃሚነት ጋር አድጓል፤ የዱቤ ግዥ ተስፋፍቷል፤ ሕዝቡ የፈለገውን ሸቀጥ ለመግዛት የገንዘብ ዐቅም ፈጥሯል። በቻይና አማካይ በሕይወት የመቆያ ጊዜ ወንድ 70፤ ሴት ደግሞ 60 ዓመት መሆኑንም ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ፈጣን የአውራ ጎዳናና፤ የባቡር የትራምና የትራሌቡስ፤ የአስፋልት መንገድ፤ መቶ በመቶ በሀገሪቱ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ተግባራዊ ሆኗል። የመንግሥት ፖሊሲው በንግድና በኢንዱስትሪ ላይ ያተኮረ ነው። የሀገሪቱ የካፒታል ክምችት ከፍተኛ ስለሆነ ከሀብታም አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ አስችሏታል።የዚህ ሁሉ የብልጽግና ምንጭ ደግሞ ሕዝቡ ለሕግና ለሥርዓት ተገዥ መሆኑ ነው።
የመንግሥት ገቢና ወጭ በተመጣጠነባት ቻይና በሀብታሙና በድሀው መካከል ያለው ልዩነት የተመጣጠነ ነው። በቻይና ማኅበራዊ ትስስር (ኔትዎርክ) በስፋት ተመሥርቷል። ሌላው ባለሙያ ሁዋንግዮ ውዪ “ቻይና፤ የብዙህነት አገር (China: a Country of Diversity)›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንደተናገሩት በቻይና ትልቅና ትንሽ፤ አሮጌና አዲስ፤ ድሀና ሀብታም፤ የሚደሰትና የማይደሰት ዜጋ ይኖራል። እርሳቸው እንደሚሉት 1.4 ቢሊዮን የሆነውን የቻይና ሕዝብ ለመመገብ እኤአ በ2020 700 ሚሊዮን ቶን ምግብ ያስፈልጋል። አሁን ያለው ምርት 600 ሚሊዮን ቶን ነው።
በያመቱ የምግብ ፍጆታው በ10 ሚሊዮን ቶን እየጨመረ የሚሄድ ነው። በዚህ ዓይነት ቻይና ገቢዋን ለማሳደግ በከፍተኛ ጥረት ላይ ትገኛለች። ገቢዋ ከቱሪዝምጋር የተያያዘ ሲሆን እኤአ በ2018 በነበሩት ብሔራዊ የበዓላት ቀናት ከ226 ሚሊዮን ጎብኚዎች (ቱሪስቶች) 86.5 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች። በተመሳሳይ እኤአ በፀደይ 2018 ፌስቲቫል ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 2.98 ቢሊዮን ዩዋን፤ ወደ ውጭ አገር ለጉብኝት ከተጓዙ ቻይናውያን 15 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። በተመሳሳይ ዓመት በድራጎን ጀልባ በባሕር ላይ በተከበረ ፌስቲቫል ከ89.1 ሚሊዮን ቱሪስቶች 36.2 ቢሊዮን ዩዋን 5.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
በአጠቃላይ የቻይና ምኞት በሦስት የተከፈለ ነው። ይኸውም ‹‹የበለጸገችና የጠነከረች ሀገር መገንባት፤ የሕዝቡን የተሐድሶ መንፈስ ማረጋገጥና ደስተኛ ሕዝብ መፍጠር›› የሚሉ ናቸው። በእድሜና በሕመም ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች መንግሥት የኮንደሚኒየም ቤት እየሠራ በነጻ ይሰጣል። ይህንንም ከቤጂንግ ወደ ደቡባዊይቱ ቻይና ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በቢይጆ ክፍለ ሀገር ለማየት ችለናል። በቻይና ውስጥ ከሚገኙት 56 ብሔር ብሔረ ሰቦች ውስጥ 17 ብሔር ብሔረ ሰቦችና በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ጎሳዎች በሚኖሩባት በጉይጆ ክፍለ ሀገር በቡጀ ወረዳ ተዘዋውረን እንደተመለከትነው መንግሥት በድህነት ቅነሳ ስትራቴጂው ለአርሶ አደሮች፤ ለድሆችና ዐቅመ ደካሞች የሚያደርገው የቸርነት ሥራ በእጅጉ የሚደነቅ ሆኖ አግኝተነዋል።
በዚያው በቡጀ ወረዳ በሺህያንግ ጥንታዊ ከተማ በዳፋንግ ቀበሌ በኩያንሂ መንደር መንግሥት የኮንደሚኒየም ቤት ሠርቶ ለ6000 ሺህ አባዎራዎች፤ ከነቤተሰባቸው 16‚000 ለሆኑ ድሀ ዜጎች፤ ዐቅመ ደካሞችና አረጋውያን በነጻ ሰጥቷል። ለእያንዳንዱ ቻይናዊ በነጻ የተሠጠው ዘመናዊ ቤት ሦስት መኝታ ክፍል፤ አንድ ሳሎን፤ አንድ ዕቃቤት፤ አንድ ማብሰያና አንድ የንጽሕና ክፍሎች ያሉት ነው።ውኃና መብራትም በነጻ ይጠቀማሉ። ሆኖም ቤቱን እስከነልጅ ልጆቻቸው ይኖሩበታል እንጂ መሸጥ፤ መለወጥ፤ ማውረስ አይችሉም። በዝቅተኛ ኑሮ ይኖሩ የነበሩትንና ዐቅም ያልነበራቸውን ዜጎች መንግሥት ከሌላ ቦታ አንሥቶ ወደ ቢጀ ዳፋንግ አካባቢ አምጥቶ፤ ዘመናዊ ቤት ሠርቶ በነጻ እንዲኖሩ ያደረገው ይኖሩበት የነበረው መሬታቸው ለም ስለአልሆነና ተራራማና እህል የማያበቅል አካባቢ ስለሆነ ነው።
ከአረጋውያኑና ከአረጋውያቱ ውስጥ ዐቅም ለአላቸው ሥልጠና ተሰጥቷቸው በግብርና፤ በፋብሪካ፤ በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፤ በምግብ ማደራጃ፤ በገበያና ሸቀጥ ማከፋፈያ ማዕከላት፤ በልብስ ስፌት፤ መንደር ውስጥ የሚውሉ እናቶች ደግሞ በልጅ አስተዳደግና በሞግዚትነት፤ በባልትና፤ ወንዶች በጥበቃ ሥራ ላይ ተሠማርተው የራሳቸውን ገቢ እየፈጠሩ በመኖር ላይ ናቸው። በአስተርጓሚ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ
አረጋውያንና አረጋውያት አሁን ያሉበት ኑሮ እርጅናን የሚያጠፋ የምድር ገነት እንደሆነ አውግተውኛል።
በድህነት ቅነሳ ስትራቴጂው መሠረት በልማትና እድገት አማካይነት የተሰባሰቡት 12‚000 ያህል ዜጎች በአሉበት በዳፋንግ -ሼይሃነግ አካባቢ መንግሥት ሦስት መዋዕለ ሕፃናት፤ አንድ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ አንድ የተግባረ እድ ኮሌጅ፤ አንድ የነጻ ሕክምና መስጫ ሆስፒታል፤ የነጻ ሕክምና መስጫ የነርሶች ቢሮ፤ ሕፃናት የሚቆዩበት ቦታ ገንብቶ ለኅብረተሰቡ በነፃ አስረክቧል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቻይና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂን በከፍተኛ ፍጥነት በመተግበር ላይ ባለቺው በጉይጆ ክፍለ ሀገር በቡጀ ወረዳ በዱጁዋን ምክትል ወረዳ በኩዋንሂ ቀበሌ የሚኖሩት የዳሂንግ ማኅበረሰብ አባላት እንቅስቃሴ በአርአያነት የሚታይ ነው።
ከዳሂንግ ማኅበረሰብ አባላት ከባዶ የተነሡና በልዩ ልዩ የሙያ ሥልጠና የታገዙ 4237 አርሶ አደሮችን የቻይና መንግሥት “የአዲሱ ዘመን የአርሶ አደሮች ማዕከል” በሚል በማኅበር አደራጅቶ ዘመናዊ ኑሮ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። በዓመት ከእርሻ ሰብል፤ ከተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፤ ከደን ልማት ማለት ጋራውንና ሸንተረሩን ደን በማልበስና አዝርዕት በመዝራት፤ ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፤ ከዓሣ ሀብት፤ ከአበባ፤ ከፍራፍሬ፤ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪ፤ ከከብትና ከአሳማ ርባታ (ከወተት፤ ቅቤ፤ ሥጋ፤ እርጎ፤ ፎርማጆ–) እና በባህል ጥበባት ከዕፀዋትና አትክልት ከሚዘጋጁ መድኃኒቶች ከፍተኛ ገቢ ስለሚያገኙ አርሶ አደሮቹ ድህነትን ‹‹ደኅና ሰንብት›› ብለውታል።
ይህ መርሐ ግብር በመላዋ ቻይና በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ሁሉ የሚካሄድ ሲሆን በቡጀ ቀበሌዎችና መንደሮች ውስጥ ተደራጅተው የመንግሥት እንክብካቤና ድጋፍ ሳይለያቸው የሚኖሩት አርሶ አደሮች ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት በዓመት ከ11 ሺህ እስከ 15 ሺህ ዩዋን ይቆጥባሉ። ከስድስተኛው የድህነት ቅነሳ መርሐ ግብር ጋር በተያያዘ በዚያው በዳፋንግ ቀበሌ በሊሎንግ ከተማ በሂአባ ቀበሌ የሥጋ ከብቶችን ከአውስትራሊያና ከሌሎች ሀገሮች እያስገባ በማድለብ ለገበያ የሚያቀርብ “ቢዝነስ ግሩፕ” የተባለ ድርጅትም አለ።
በሥጋ አቅራቢው ድርጅት ውስጥ በርካታ ዓባላት ሲኖሩ ዓባላቱ በዓመት ከ15ሺህ በላይ ዩዋን ይቆጥባሉ። በተጨማሪም በዚያው በጉይጆ ክፍለ ሀገር በሬንሃይ ከተማ በሞይታይ አካባቢ የሚገኘው የወይን ጠጅ ፋብሪካ፤ በሚታን የገጠር ከተማ በማኦ ዜዱንግ ጊዜ ቱሪዝምን መሠረት አድርጎ የተገነባው የሻይ ቅጠል ኢንዱስትሪ በቻይና የድህነት ቅነሳ ጥረት ውስጥ ታላቅ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው። በሻይ ቅጠል ልማት በማኅበር ተደራጅተው የሚኖሩት ሰዎች ምርታቸውን ለአሜሪካ፤ ለአውሮፓ፤ ለእስያና ለአፍሪካ ሀገሮች በመሸጥ ላይ ይገኛሉ። በተራራ ሥር በሚገኘው ዳገታማ ቦታና በሜዳው ላይ ጭምር አምሮ የሚታየው የሻይ ቅጠል ተክል በሥነ ኑረት ደረጃ ለጤና ተስማሚ የሆነ አየር የመፍጠር ኃይል አለው። ከተራራው ሥር መላውን የሻይ ቅጠል ተክል ለማየት የሚያስችልና ለቱሪዝም አገልግሎት የዋለ ሰገነት ሲኖር ሰገነቱ ላይ ሆኖ የሻይ ቅጠሉን ተክል ቁልቁል ሲመለከቱት ውበቱ በእጅጉ ይማርካል።
ከዚህ የተነሣ አካባቢው ለኑሮ የተመቸ ሲሆን አካባቢውን በጎበኘንበትና በኃላፊው ገለጻ በተደረገበት ወቅት እንደተረዳነው እያንዳንዱ አባል ባለፎቅ ቤትና ባለመኪና ነው። ገለጻ ያደረገልን ኃላፊ “ከዚህ ሁሉ ሀብታም አርሶ አደር አንዱ ብቻ መኪና ሳይገዛ ቀረ” ብሎ እየሣቀ ነግሮናል። ምክንያቱ ባይገባንም ‹‹ጠጭ ስለሆነ ይሆናል›› ለማለት ሞክረን ነበር። ነገር ግን በቻይና ጠጥቶ የሚወላገድና ራሱን የሚጎዳ ሰው ስላላየን ‹‹እግዜር ይቅር ይበለን›› ብለን ራሳችንን ከክፉ ሐሳብ ገትተነዋል።
በአጠቃላይ ቻይና 1.4 ቢሊዮን ሕዝቧን መግባ ማደሯ የጸረ ድህነት ፖሊሲዋን ትክክለኛነት፣ የመንግሥቷን ፅናትና የሕዝቧን ጠንካራ የሥራ ባህል በተግባር ያስመሰከረ በመሆኑ እንደ አገራችን፤ ለመላው አፍሪካና እንደእኛ በድህነት አረንቋ ውስጥ ለሚዛቅጡ የዓለም ድሀ አገሮች በመልካም ምሳሌነቱ የሚጠቀስ ነው፤ ቻይና ውጤቷ እንጂ ፕሮፓጋንዳዋ ጆሮ አያሰለችም፤ ቻይና ስትጥል እንጂ ስትተኩስ አትታይም፤ ችጋርን ብቻ ሳይሆን ጎጂ ባህሏን በሥራ ቀይራ ዓለምን ካስደነቀ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሳለች፤ ለዚህም ነው ‹‹ቻይና ያደፈጠችዋ ነብር›› ያልናት።
ዘመን ጥር 2011 ዓ.ም
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)