- እስሌማን ዓባይ
ሲ.አይ.ኤ በኃይማናት ሽፋን የተደራጁ ልዑኮችን ለስለላ የማሰማራት ታሪኩ ከምስረታው ጀምሮ አብሮት የቆዬ ነው። እንደውም ከCIA ምስረታ በፊት የደህንነት ተግባር ያከናውን በነበረው የአሜሪካ ስትራቴጂክ መስሪያ ቤት ጭምር ይህንኑ ሀይማኖት-ለበስ የስለላ ዘዴ አገልግሎት ላይ ያውል እንደነበር ጭምር መረጃዎች ያሳያሉ።
ዊሊያም ኤዲ ቁልፉ የሲአይኤ ሰውና መስራች ለዚህ አይነተኛ ባለታሪክ ነው። ሊባኖሳዊ ተወላጅ ነው። ከአሜሪካ እና ካይሮ ዩኒቨርሲቲዎች እስከ ፒኤችዲ ድረስ ተምሯል። የትውልድ አገሩ መካከለኛው ምስራቅ መሆኑና የአረብኛ ቋንቋ ችሎታ ያለው መሆኑን ከግምት በማስገባት በሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ በነበሩ ተልዕኮዎች ላይ በደምብ እንዲያገለግል ሆኗል።
በሁለተኛው አለም ጦርነት 1942 ላይ ወደ ሞርኮ የተላከ ሲሆን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ካቶሊክን ያስተምር ነበር። ለሲአይኤ የስለላ ስራው ወቅት በሚያጋጥሙት ስጋቶች ላይም የግድያ ርምጃን እንደ አማራጭ ሲጠቀም ነበር። ማህበረሰቡ ባልገመተው መንገድ ግድያዎችን ፈፅሞ አብሮ ይፀልይና ፍትሃት ያደርግም ነበር።
መንፈሳዊ በሆነው የሲአይኤ የስለላ ተልዕኮ በተለይም በሁለተኛው አለም ጦርነት ወቅት በስፋት ሰርተውበታል።
አለን ዱሌስ ከአሜሪካ ስትራቴጂክ ተቋም ጀምሮ በ CIA ከተተካም በኋላ በዚሁ ዘዴ ሰፊ አገልግሎት ሰጥቷል። በተለይም በህንዱ የካዳንኩላም የኑክለር ጣቢያ አመፅ እንዲቀሰቀስ ያደረገበት ተልዕኮ ተጠቃሽ ነው። የኑክለር ጣቢያው በሩሲያ እየተገነባ የነበረ ነው። ይህንን ለማስተጓጎልም ያካባቢው ማህበረሰብ የኑክለር ጣቢያውን ተቃውሞ እንዲነሳ ሆኗል። ይህ የተደረገውም በዚሁ በCIA ሰው መሪነት ነበር። ከ2012 ወዲህ የህንድ አንድ ምኒስትር ለአመፁ የርዳታ ድርጅቶችን እና ሲአይኤን ተጠያቂ አድርገው ነበር። የሩሲያ መንግስትም በተመሳሳይ ብጥብጡ በCIA መቀነባበሩን ገልጿል።
በ1975 ገደማ የአሜሪካ ሴናትሮች ጉዳዩን ደርሰውበት የህግ ጥሰት መሆኑን በመግለፅ ክስ ሁሉ ተመስርቶ ነበር። ከተከሳሽ ሰላዮች ኤዲ አንዱ ነበር። ኤዲ የሲአይኤ አመራር ሲሆን በሚሰማራበት አገር ለሚያደራጃቸው አባላቱ በአመት እስከ 11 ሺህ ዶላር ስለመክፈሉ የወቅቱ ምርመራዎች ይፋ አድርገውታል። ዊኪሊክስም ከጊዜያት በኋላ (Wikileaks cable 06MUMBAI1803_a) ይህንኑ ሀቅ ማውጣቱ ይታወሳል።
አሜሪካ ለ C.I.A ግልጋሎት የሚሰጡ ቅዱሳን ሰላዮችን ለመላክ ያልተቀደሰ ፕሮጀክት እንደምታከናውን ለመጠቆም ይህችን በጨለፍታ አጋራኋችሁ እንጂ በዚህ ዙሪያ የቃኘኋቸው ድርሳናት መፃህፍት የሚወጣቸው ናቸው።
እስሌማን ዓባይ
ዋቢ